የግንቦት7 ንቅናቄ ዶር ብርሃኑ ነጋ አዲሱ አመት በስልጣን ላይ ያለው ዘረኛ ተወግዶ ነጻና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትገነባበት እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ
የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በራሳቸውና በድርጅታቸው በግንቦት 7 ሥም ለኢትዮጵያዊያን ባስተላለፉት የአዲስ አመት መልእክት በስልጣን ላይ ያለው ዘረኛ አገዛዝ ተወግዶ ነጻና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትገነባበት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ መልኩ አንድነት ፓርቲ 2004 የለውጥ አመት እንዲሆን፣ ወጣቱ በአንድነት ለነጻነቱ እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል።
አንድነት ባወጣው በዚሁ መግለጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የተነጠቀውን ነፃነቱን ለመቀዳጀት ዛሬውኑ ለትግል እንዲነሳ ጥሪ አቀርቡአል።ፓርቲው ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ወያኔ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖ እየገዛ የሚቀጥልበት አንዳች ሞራላዊ ምክንያት የሌለው በመሆኑ፣ ይኸን አገዛዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕጋዊና ሠላማዊ ትግል በማድረግ በቃህ ሊለው ሕዝቡም የስልጣኑ ባለቤት ሊሆን ይገባል፡ ብሎአል።
የ2ዐዐ4 ዓም እንዳለፉት ሃምሳ ዓመታት የጨለማ ዓመታት ሆኖ ሊቀጥል እንደማይገባው የገለጸው አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ነፃነት ሁሉን አቀፍ የነፃነት ትግል የሚደረግበት አመት ሊሆን እንደሚገባው አሳስቦአል። በመጨረሻም አንድነት ለህዝቡ ባቀረበው ጥሪ ፡ በአሁኑ ወቅት በአረቡ ዓለም እየተካሄደ ያለው የነፃነት ትግልና ውጤቱም ተግባራዊ ተሞክሮውን እንዳጠናከረለት ገልጾ፣ ሕዝቡ ነፃ አውጭዎችን ቁጭ ብሎ የሚጠብቅበት ጊዜ በማብቃቱ እያንዳንዱ ሰው የነፃነቱ ባቤት ለመሆን አበክሮ ሊታገል እንደሚገባ ገልጿል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መድረክ ረሀብን ማጋለጥ በሽብርተኝነት ሊያስወነጅል እንደማይገባ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ጳጉሜ 4 ባወጣው በዚሁ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በተለይም በደቡብ የሃገራችን ክፍል የረሀቡ የአስከፊነት ደረጃው እየጨመረ ነው ካለ በሁአላ በቀን ሶስት ጊዜ እንመግብሃለን ብለው ያማለሉት ሕዝብ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ አገዛዙ በጠኔና በረሃብ መሃከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት ሲዳክር መታየቱን አውግዟል። በመጨረሻም ወያኔ ኢሕአዴግ በወህኒ ያጎራቸውን የመድረክ አመራር አባላት፣ እንዲሁም ሌሎች የፖለተካ እስረኞችን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲፈታ፣ የወያኔው አገዛዝ በኢትዮጵያ የተከሰውን ድርቅና ረሃብ ደብቆ ለሌሎች ችግር ደራሽ ለመምሰል የሚያደርገውን የገፅታ ግንባታ ጥረት አቁመው እውነታውን ያላንዳች መሸፋፈን ለዓለም ሕብረተሰብ ይፋ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ|ር ብርሃኑ ነጋ ያስተላለፉት የአዲስ አመት መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ ላይ ይመልከቱ።