በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ ለማስወገድና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ኦነግ ከግንቦት7 እና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስታወቀ

ጥምረት ለፍትህ ለነጻነትና ለእኩልነት ባለፈው ቅዳሜ ጳጉሜ 3 ቀን በአሜሪካን አገር በዳላስ ከተማ አዘጋጅቶት በነበረው ስብሰባ ላይ ለተገኙት ኢትዮጵያዊያን ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ዋና ጸሃፊ ፤ ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በህዝባችን ላይ እያደረስ ያለውን ሰቆቃ ለማስቆምና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ኦነግ ከግንቦት7 እና ለዲሞክራሲ ከሚታገሉ ሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ውይይት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የኦነግ ዋና ጸሀፊ አቶ አሚን ጁንዲ ጥምረት በዳላስ ቴክሳስ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ከግንቦት7 ጋር በጋራ ለመስራት በመነጋገር ላይ እንደሆነ ገልጸው ለፍትህና ለነጻነት የሚታገሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደጎን ችላ አድርገው ሥልጣንን በሃይል ተቆጣጥሮ ባለው ዘረኛው ቡድን ላይ ብቻ እንዲያነጣጥሩ ጠይቀዋል።

በዚሁ ስብሰባ ኦነግ ኢትዮጵያንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ እንደማያውቅ የተናገሩት አቶ አሚን፣ በደርግና በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ኦነግ አሉታዊ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ስለተከፈተበት ምስሉ መበላሸቱን ከገለጹ ቦኋላ ኦነግ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተገንብቶ ማዬት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

የዘረኛው መለስ አገዛዝ እስከዛሬ በስልጣን ላይ ሊቆይ የቻለው ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ለመተባበር ባለመቻላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አሚን ኦነግ እስከዛሬ የተደረገውን ትግል ገምግሞ፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ቁርጠኛ ውሳኔ መወሰኑን ገልጸዋል።

ኦነግ በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ አስወግዶ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት የሚቻለው ትብብር በመመስረት ብቻ መሆኑን እንደሚያምን፣ ይህን ትብብር ለመመስረት ደግሞ ሁላችንም የግድ አንድ ቋንቋ፣ አንድ እምነትና አንድ አመለካከት መያዝ የለብንም ሲሉ ዋና ጸሀፊው ገልጸዋል።

በሌላም በኩል የግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው መተባበር ሳንችል ቀርተን፣ አገራችንን እንዲያወድም ከፈቀድን ማናችንም ከተጠያቂነት አንድንም፣ ታሪካችንን አውቀን፣ መጥፎ ታሪካችን እንዳይደገም ዘግተን፣ መጻኢውን ታሪክ እየጻፍን መጓዝ እንዳለብን ልንገነዘብ ይገባል በማለት ተናግረዋል። በመጨረሻም አቶ አንዳርጋቸው ከኦነግ ጋር የሚደረገው ንግግር ለሁሉም ኢትዮጵያ የምትመች አገር ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።