በመለስ ዜናዊ “ሽብርተኛ” መባል የአርበኝነት ሜዳሊያ ሆኗል

ለገዛ ራስና ለሃገር ነፃነት አርበኛ መሆን በመለስ ዜናዊ እና እሱ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች “ሽብርተኛ” ያስብላል፤ ያስከስሳል፤ ያሳስራል።

አርበኝነት ክብር ነው። አርበኝነት የመልካም ዜግነት ከፍተኛው መገለጫ ነው። አርበኝነት የታላቅ ስብዕና መገለጫ ነው። በመለስ ዜናዊ እና እሱ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች “ሽብርተኛ” መባል የአንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም ኢትዮጵያዊ ድርጅት አርበኝነት ማሳያ ሆኗል። እናም በመለስ ዜናዊ “ሽብርተኛ” መባልና የሚያኮራና የሚያስደስት ነገር ሆኗል።

መለስ ዜናዊ “ሽብርተኛ” እያለ የሚጠራቸው ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች-

  1. ዘረኝነትን የሚቃመው፣
  2. ለሰብዓዊ መብቶች ልዕልና ጥብቅና የቆሙ፣
  3. ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና እድገት ብሩህ ራዕይ ያላቸው፣
  4. የህዝብ አመኔታና ፍቅር የተቸራቸው፣ እና
  5. በሙያቸውም የተከበሩ

ዜጎች መሆናቸው በተደጋጋሚ ታይቷል። በመለስ አንደበት “ሽብርተኛ” መባል የአንድን ኢትዮጵያዊ ታላቅነት ማሳያ ሆኗል።

ወጣቶቹ ጋዜጠኛች ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት ዓለሙ በለጋ እድሜዓቸው በመለስ ዜናዊ “ሽብርተኛ” የመባልን ክብር ተቀዳጅተዋል። በመለስ አገዛዝ “ሽብርተኛ” መባላቸው ብቻውን ስለ ውብሸትና ርዕዮት ታላቅነት ብዙ ይናገራል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በውብሸትና ርዕዮት መንፈሳዊ ቅናት አድሮባቸዋል።

አቶ በቀለ ድሪባ፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳ እና በርካታ ሌሎች ቆራጥ ኢትዮጵያዊያን ለመለስ ዜናዊ “የሽብርተኝነት”፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ  የአርበኝነት ኒሻን በቅተዋል።

ሰሞኑን ደግሞ አዛውንቱ አርቲስት ደበበ እሸቱ ለዚህ ታላቅ ክብር መብቃቱ መለስ ዜናዊ መስክሮለታል። ይህ ደግሞ  ለአርቲስቱ ቀድሞውኑ በነበረው ክብር ላይ ተጨማሪ ካባ ደርቦለታል።

በድርጅቶችም ቢሆን እንደዚያው ነው።

መለስና አሻንጉሊት ፓርላማው ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን እና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚመዝኑበት መለኪያ አንድ አይደለም። በመለስ ፓርላማ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት “በሽብርተኝነት” ተፈረጀ ማለት ድርጅቱ

  1. የመለስን አገዛዝ ስጋት ላይ ጥሎታል፣
  2. በርካታ ተከታዮች አሉት፣ እና
  3. ኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀሳል

ማለት ነው።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለዚህ እውቅና በቅቷል።

ግንቦት 7 አሁን ባገኘው እውቅና ሳይኩራራ መለስ ዜናዊንና መላውን አገዛዙን ከዚህም በላይ አስጨንቆና አስገድዶ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ለማውረድ ተግቶ ይሰራል።

የመለስ ዜናዊ “የፀረ-ሽብርተኝነት” አዋጅ የኢትዮጵያን ህዝብ ይበልጥ ያስቆጣል፤ ይበልጥ ያነሳሳል እንጂ ማስፈራራት አይችልም።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!