ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የቃሊቲ ማረሚያ ቤትን በታማኝ አገልጋዮቹ እያጨናነቀ ነው፣ ቀደም ብሎ በማረሚያ ቤት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ጠባቂዎችን በሙሉ ከኃላፊነታቸውና ከሥራ ገበታቸውም አነሳ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የራሱን ጥላ እየሸሸና ሁሉንም በጥርጣሬ አይን እየተመለከተ የሚገኘው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለረጂም አመታት ሲያገለግሉ የነበሩ በርካታ ጠባቂዎችንና ሃላፊዎችን ከስራ ገበታቸው ማንሳቱን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ።
እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት በግምገማ ሰበብ ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ከኃላፊነታቸውና ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉት የቃሊቲ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ፖሊሶች አብዛኛዎቹ ከ10 ዓመት በላይ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ ሲሆን በግምገማ ሰበብ አገዛዙ በድንገት ከሥራ ገበታቸው ያነሳቸው በሰራተኞቹ ላይ እምነት በማጣቱ እንደሆነ የውስጥ ምንጮችን በመጥቀስ በላከልን ዘገባ አመልክቱአል፡፡
እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ይህን ርምጃ የወሰደው ለረጂም ጊዚያት በማረሚያ ቤቱ ሲያገለግሉ የነበሩ ሰራተኞች በትውውቅ፣ በመግባባት፣ በጎሳ፣ በቸልተኝነትና በሙስና ወደ ማረሚያ ቤቱ ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ ቁሶችን ማለትም ስለታም ጩቤዎችንና ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን ጨምሮ፣ እንደ ጫት እና ሌሎች አነቃቂ እፆች በተለያዩ መንገዶች ለእስረኞች ያስገባሉ በሚል የሽፋን ግምገማ እንደሆነ ታውቁአል።
ይሁን እንጂ አንድ የወህኒ ቤቱ ሰራተኛ ለዘጋቢያችን እንደገለጹት እውነተኛው ምክንያት ፖሊሶቹ የኢህአዴግ ደጋፊ ተደርገው ባለመታየታቸውና ስጋት በመፍጠራቸው መሆኑን ፣ ከዚህም በተጨማሪ ተባራሪ ሰራተኞቹ ኑሮአቸውን ለመግፋት እየተቸገሩ በመምጣታቸው በዘረኛው አገዛዝ ላይ የሚያሰሙት ቅሬታ እየጨመረ በመምጣቱ የማራቅ እርምጃ መውሰድ ስለተጀመረ ነው በማለት መናገራቸው ታውቁአል።
ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በቃሊቲ እስር ቤት የጀመረው ይህ ዓይነቱ የጥበቃ ሠራተኞችን የማጥራትና በፌዴራል ፖሊስ የመተካት እንቅስቃሴ ወደ ሌሎቹም የክልልና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ እንዲሁም በተወሰኑ የአገዛዙ ተቋማት ውስጥም ሊቀጥል እንደሚችል ተያይዘው የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል::