ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎችን ከኢትዮጵያ አባረረ
ከመቼውም ጊዜ በላይ በተለያዩ አስጨናቂ ህዝባዊ አጀንዳዎች ተወጥሮ የሚገኘው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ሰሞኑን እንደቆሰለ ጅብ እያረገው ሲሆን የተለያዩ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጣራት ላይ ይገኙ የነበሩ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎችን በ 24 ሰአት ጊዜ ውስጥ ከሃገር ማባረሩን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ።
እንደወያኔ በሥልጣን ላይ ለአሥርተ አመታት የቆዩትን አምባገነን የሰሜን አፍሪካንንና የአረብ አገራት ገዥዎችን እያርበደበደ ያለው አይነት ህዝባዊ አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል በማለት በስጋትና ፍርሃት የተጠመደው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ፤ ሰሞኑን በጀመረው አዲስ የእስር ዘመቻ የኦፊዲን ምክትል ሊቀ-መንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባናንና የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ አመራር አባል አቶ ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን በቁጥጥር ሥር ባደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ የአምንስቲ እንተርናሽናል ሰዎች ከአገራችን መባረር እየተፈጸመ ያለው መብት ጥሰት በአለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ እንዳይታወቅ ለመከላከል ካለው ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ተገምቶአል። ለዚህም እንደማስረጃ ሊቆጠር የሚችለው አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰው ከነበሩት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ልዑካን ቡድን ጋር ከተገናኙ ቦኋላ “የሽብርተኝነት ክስ ” በፈጠራ ተለጥፎባቸው እስር ቤት እንዲወርዱ መደረጋቸውን ኢሳት ታማኝ ምንጮቹን ጠቅሶ በመዘገቡ ነው።
እንደ ኢሳት ዘገባ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ለሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያቶች 24 ሰዓት ሙሉ በደህንነቶች ካሜራ ክትትል ስር የነበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጋር በመገናኘታቸው በ24 ሰዓት ውስጥ የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው እንዲወጡ ከዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሰረት ፤ ለ 12 ቀናት ሊያደርጉት የነበረውን ቆይታ አቋርጠው ለመመለስ መገደዳቸው ታውቁአል።
አቶ በቀለ እና አቶ ኦልባና የታሰሩት የአምነስቲ ሰዎች ከኢትዮጵያ መባረራቸውን ተከትሎ ሲሆን፤ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ልዑካን ጋር ሲወያዩ ደህንነቶች ያነሷቸው ፎቶዎች፤ በሽብርተኝነት ለተመሰረተባቸው ክስ እንደ አንድ ማስረጃ መቅረቡም ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቱአል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን ከጊንጭ ከተማ የተያዙት ሰባት የመድረክ አባላት ለምን እንደታሰሩ እስካሁን ያልተገለጸ ሲሆን ተመሳሳይ የሽብርተኝነት ታርጋ ይለጠፍባቸዋል የሚል ግምት እንዳላቸው፤ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት አቶ አንዷለም አራጌ ለኢሳት መናገራቸውን ኢሳት ዘግቡአል።
ኢሳት ረሀብ ክፉኛ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ምንም ዓይነት ፎቶግራፍ ማንሳት በኢትዮጵያው ዘረኛ አገዛዝ መከልከሉን የተባበሩት መንግስታት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ላይ መጠቆሙን አቶ አንዷለም መናገራቸውን ዘግቡአል። አቶ አንዷለምን በመጥቀስ እንደዘገበው፤ የመንግስታቱ ድርጅት ልዑካን ጥናታቸውን ሲጨርሱ ባወጡትና ለፓርቲያቸው በላኩላቸው ሪፖርት ላይ ፤በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሀብ ተከትሎ የተመድ ልዑካን ወደተለያዩ በረሀብ የተጠቁ አካባቢዎች ቅኝት ሲያደርጉ ምንም ዓይነት ፎቶ እንዳያነሱ መንግስት እገዳ እንደጣለባቸው ታውቁአል።
ቁጥራቸው ከ50 በላይ የሆኑ አባላቶቹ ያለአንዳች ማስረጃ መታሰራቸውን፣ ተከትሎ ፤የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፤ ቀደም ሲል በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች አባሎቹ መታሰራቸውን፣ መደብደባቸውንና ከሀገር እንዲሰደዱ መደረጋቸውን በማስታወስ፤ ዛሬም ይህ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ሴራ ሊቆም አልቻለም ሲል ገለጹአል።
የኦፌዴን ም/ ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ሃላፊ እንዲሁም የመድረክ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ለነፃነት በመታገላቸው ብቻ ፤በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት ከሚያገለግሉበትና የዶክትሬት (የፒኤችዲ) ጥናታቸውን ከሚያከናውኑበት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አቃቂ ካምፓስ ተይዘውና ወደ አዳማ ተወስደው ቤታቸው ከተበረበረ በኋላ፤ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጎ በፌዴራል ማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ መታሰራቸውን ዋና ፀሀፊው ገልጸዋል።
እንደ ዋና ጸሃፊው መግለጫ ”የወያኔ አገዛዝ አቶ በቀለን ለማሰር የተጠቀመበት ሴራ ዘወትር ኦሮሞ የሆነን ሰው ሲወነጅል እንደሚጠቀመው “ኦነግ “የሚል ካርድ በመምዘዝ ነው‘ ያሉ ሲሆን ” አቶ በቀለ ገርባ የታሰሩት ኦነግ ስለሆኑ አይደለም፤ ይልቁንም የኦፌዴን ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ፤ የገዢውን ፓርቲ ኢፍትሃዊና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፤ ሀገርና ዓለም በተጨባጭ እንዲያውቀው ተግተው በመሥራታቸውና በመድረክ ጥላ ሥር ለፓርቲዎች አንድነት አበክረው በመንቀሳቀሳቸው ነው‘ ብለዋል፡፡
ቀጥለውም “ገዢው ፓርቲ፤ አቶ በቀለን ያሰረው፤ ሌሎች ለመብታቸው የሚተጉ ዜጎችን ለማስፈራራት ነው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈራው ጽዋው እስኪ ሞላ ብቻ ነው። ህዝባችን ልክ እንደ ቱኒዚያ እና ግብፅ ሕዝብ ለነፃነቱ ይቆማል” ብለዋል።
ቀደም ብሎ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወደ ኢትዮጵያ ቱሪስት መስለው በመግባት ስላጠናቀሩት ዘገባ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በተደጋጋሚ ሲያስተባብልና፤ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ዘገባውን ሚዛናዊ ለማድረግ የአካባቢዎቹን መስተዳድሮች አስተያዬት ማካተት ነበረባቸው የሚል ኡ ኡ ታ ሲያሰማ የቆየ ሲሆን ይህን ኡ ኡ ታ ተከትሎ የኢትዮጵያን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለግንቦት ሰባት ዘጋቢ በሰጡት አስተያየት የቢቢሲ ጋዜጠኞች የዘረኛውን አገዛዝ ባህሪ ጠንቅቀው በማወቃቸው ዘገባቸውን በተገቢው መንገድ ለማጠናቀር የተጠቀሙት ስልት የሚያስመሰግናቸውና እሰየው የሚያሰኝ ነው ብለዋል።