ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያዊያንን በጅምላ ማሰሩን ቀጠሉአል፤ ሰሞኑን በሽብርተኝነት ሥም 29 የኦሮሞ ተወላጆች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ
ህዝባዊ ተቃውሞ ሊቀሰቀስብኝ ይችላል በማለት እንቅልፍ እያጣ የመጣው የወያኔ አገዛዝ ሰሞኑን በዜጎች ላይ ጅምላ እስራት ማካሄዱን በመቀጠል የኦነግን የሽብር ዓላማ ያራምዳሉ በማለት 29 ሰዎች ማሰሩን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ አመለከተ።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት የዘረኛው ወያኔ ሰለባ ከሆኑት 29 ግለሰቦች መካከል የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግሬስ (አሕኮ)ና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፓርቲዎች አባል የሆኑ ዘጠኝ ግለሰቦች ይገኙበታል።
ጥላሸት በመቀባትና ያልሰሩትን ወንጀል ሰርቻለሁ ብለው እንዲቀበሉ በማሰቃየት ተግባሩ የሚታወቀው ዘረኛዉ አገዛዝ የአሁኖችን ታሳሪዎች “በኅቡዕ መዋቅሮች በመደራጀት ለሽብር ተግባር ተልዕኮ የሚውሉ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችንና ፈንጂዎችን በመያዝና ደብቆ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሙከራ” የተያዙ ናቸው በማለት የተለመደ ፕሮፓጋንዳውን በመንዛት ላይ እንደሆነ ተያይዞ የደረሰን መረጃ አመልክቱአል።
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የመድረክ አባላት የሆኑና በኦሮሚያ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አመራሮችንና አባላትን በገፍ በማሰር ላይ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ በደህንነትና በፖሊስ ግልጽ ክትትል እያስፈራሯቸው መሁኑን ምንጮች አስታወቁ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ኢሳት እስካሁን ከ50 በላይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) እና የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረንስ (ኦህኮ) ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በፌዴራል ማዕከላዊ ቢሮ ከየቤታቸውና ከየሥራ ገበታቸው ያለፍድ ቤት ትዕዛዝ ተይዘው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከሁለቱ ፓርቲዎች ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ዘግቦአል።
የወያኔ ፌዴራል ፖሊስ ባለፈው ዕሁድ በሰጠው መግለጫ በመድረክ ሥር የተሰባሰቡ 29 የኦፌዴንና የኦህኮ ፓርቲዎች አባላትን በሽብርተኝነት ተግባር ሲንቀሳቀሱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር አውያቸው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
የኦህኮ ፓርቲ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳ ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2003 ዓ.ም እንደወትሮው ስድስት ኪሎ አፍንጮ በር አካባቢ በሚገኘው በመድረክ ጽ/ቤት የፓርቲ ሥራቸውን እስከ ቀኑ 6፡30 ሲያከናውኑ ቆይተው ከቢሮ አቅራቢያቸው በሚገኘው ሱቅ ዕቃ በመግዛት ላይ ሳሉ በወያኔ ፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው መጀመሪያ ወደ ቅድስተማሪያም አካባቢ ከተወሰዱ በኋላ 40 ደረጃ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ቤታቸው እንደተበረበረና ወደ ማዕከላዊ እሥር ቤት ተወስደው እንደታሰሩ የመድረክ የሥራ ባልደረባቸው አቶ አለሙ ኮየራ ለኢሳት ሪፖርተር መናገራቸው ተዘግቦአል፡፡
የኢሳት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአቶ ኦልባና ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ የማታወርቅ መንገሻ በበኩላቸው ”ባለቤቴን ሊያሳስር የሚችል አንዳች ምክንያት ካለ ያው በሕጋዊ መንገድ በተቃዋሚ ፓርቲ እንቅስቃሴ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መንቀሳቀሱና መሳተፉ ነው” ያሉ ሲሆን እርሱ በቁጥጥር ሥር ሲውል እኔ ኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ የሥራ ገበታዬ ላይ ስለነበርኩ ቤቴን ሲበረብሩ ስላልነበርኩ ምን ዕቃ እና ዶኩመንት እንደወሰዱ እስካሁን አላወቅሁም ነገር ግን ማታ ቤቴ ስገባ እኔ ባለቤቴ ኦልባና እና አንድ የእርሱ ዘመድ በኦሮሞ የቦረና አባ ገዳ ባህላዊ አለባበስ የተነሳነውን የፎቶ ፍሬም ለምን እንደ ወሰዱት ግን አልገባኝም ማለታቸውን አስታውቆአል፡፡
የኦፌዴን ፓርቲ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ በቀለ ነጋ ኢህአዴግ ሀገሪቷን እንደ ግል እርስት ይዞ እንደፈለገው እያደረገ ሲሆን በተለይ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ኢሰብዓዊ ድርጊቱን የሚያጋልጡበትን ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞችና ፓርቲዎች ሆን ብሎ ለማጥፋት አበክሮ እየሰራ ነው ማለታቸውን የኢሳት ዘገባ አመልክቶአል፡፡
አቶ በቀለ «የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲው ዛሬ ኦሮሞ ላይ ዘምቷል፣ ነገ ደግሞ ሌላው ላይ መዝመቱ አይቀርም፣ ይህ ገዢው ፓርቲ ወደ አንድ ወጥ የአንድ ሰው አምባገነንነት መለወጡን የሚያሳይ ሲሆን ዛሬ ለአንተ በቢሮዬ በሰጠሁት መረጃ እኔም አሸባሪ ተብዬ ነገ ስላለመያዜ ምንም ማስተማመኛ የለኝም» ማለታቸውንም ኢሳት ዘግቦአል።
ሲፒጄ በመባል የሚታወቀው የጋዜጠኞች ጥበቃ ተቁዋም “ሽብርተኞች” ናችሁ ተብለው የታሰሩት የሁለት ጋዜጠኞች ጉዳይ እጅግ ያሳሰበው መሆኑን በመግለጽ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች በበኩሉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት ከዘረኛው የወያኔ አገዛዝ እስራት ነጻ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቡአል። በተመሳሳይ መልኩ አዲስ ነገር ኦን ላይን በመባል የሚታወቀው የመረጃ ድረ ገጽ ባወጣው ዘገባ የወርሐዊው “የሙስሊሞች ጉዳይ” መጽሔት አዘጋጅ የሱፍ ጌታቸው አደገኛ ማስፈራሪያ እንደደረሰው ሰሞኑን ለፍትሕ ጋዜጣ መናገሩም ታውቁአል።
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በተለይም በኢትዮጵያ ህዝባዊ አመጽ ይነሳል የሚል ፍራቻ ካደረበት ወዲህ ኢትዮጵያዊያንን ለማሸማቀቅና ለማስፈራራት ኢፍትሃዊ የሆነ እስራትና ሰቆቃ በዜጎች ላይ እየፈጸመ መሆኑን በስፋትና በተደጋጋሚ ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።