ዘረኛው አገዛዝ ታማኝና አገልጋዮቸ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸው ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚዉን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ የማድረግ ተግባሩን ቀጠሉአል፣ ስኩዋርን የማከፋፈል ድርሻ የምርጦቹ እንዲሆን ተወሰነ

ቀደም ብሎ በሃገር ውስጥ ስኳርን በጨረታ በመሸመት ለቸርቻሪ ነጋዴዎች በጨረታ የማከናወኑ አሰራር እንዲቀርና ጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ)፣ለሚመርጣቸው ነጋዴዎችና ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ብቻ እንዲሰጥ መወሰኑን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ፡፡

እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ቀደም ብሎ ስኳር ለገበያ ተጠቃሚዎችና ሸማቾች የሚቀርብበትን የጨረታ አሠራር በመሰረዝ፣ አዲስና ምርጦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር እንዲሰፍንም የተደረገው ነጋዴዎች ለራሳቸው ጥቅም ብቻ በማሰብ የስኳር ገበያውን እየረበሹና እጥረት እየፈጠሩ መጥተዋል በሚል ሰበብ መሆኑ ታውቁአል፡፡

ቀደም ብሎ ስኩዋርን በጨረታ ከማከፋፈያ በመግዛት ለቸርቻሪ ነጋዴዎች የማከፋፈል ስራን ሲያከናውኑ የቆዩ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነጋዴን ዘጋቢያችን አነጋግሮ በሰጡት አስተያየት ስኩዋር እንደስሙ ሁሉ ስኩዋር እየሆነ ከመጣ ዘመን አልፎታል፣ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ የሚግበሰበስበት የምግብ ፍጆታ ነው። የወያኔ አገዛዝ እንዲህ አይነት የፍጆታ እቃዎችንም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ የሆነ ገቢ የሚያስገኙ ተቁዋማትን በምንም መልኩ ከእጁ እንዲወጡ አይፈልግም፣ ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ ክልል ለመጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና ለወያኔ ደጋፊዎች የተለየ አገልግሎትና ጥቅምን በመስጠት እንደስኩዋር ያሉ ከፍተኛ ገቢንና ትርፍን የሚያመጡ ሸቀጦች ለነኝህ ግለሰቦች እንዲሰጥ የማድረግ ተግባር ከጀመረ ቆይቱአል። ወያኔ ደረጃ በደረጃ ጫካ ውስጥ ሲያልም የነበረውን የበላይነት እቅዱን ቀስ በቀስ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ልብ እያልን ነው። ባሁኑ ሰአት ከፍተኛ የሚባሉ የንግድ ተቁአማት ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ ሁላችንም እናውቃለን፣ ብለዋል። በመጨረሻም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የሆንን ሁሉ ይህንን በጥንቃቄ መገንዘብ ሳይረፍድብን ከወያኔ ጋር የመጋፈጫ ጊዚያችን አሁን ነው፣ አለዚያ ፍጹም ልናገግም ወደማንችልበት አዘቅት ውስጥ ስንገባ ይታየኛል በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።

በሌላም በኩል በሃገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ እየጣለባቸው ያለው ኢ ፍትሃዊ የግብር እዳ እጅግ እያስመረራቸው መሆኑን በዚህም ምክንያት ከአብዛኞቹ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት የወያኔው አገዛዝ በነጋዴዎች ላይ ጦርነት አውጁአል፣ በመሆኑም ነጋዴው የቱኒዝያና የግብጽ አይነት ንቅናቄ ካላሳየ በስተቀር፤ ባለፈው የዋጋ ተመን ላይ እንደተደረገው ነጋዴውን የማሰቃየት የረቀቀ ድርጊት፤ በተፋፋመ መልኩ መቀጠሉ አይቀሬ ነው በማለት በግልጽ እየተናገሩ መሆኑን ዘጋቢያችን በላከልን ሪፖርት ፤ላይ አመልክቱአል።

ዘጋቢያችን የዘረኛው አገዛዝ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ እየፈጸመ ያለውን በደል አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ውስጥ ያነጋገራቸው ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት፤ የወያኔ አገዛዝ ባለፈው አንድና ሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ40% በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ያተመ፣ ባለፉት ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ የብርን የመግዛት አቅም 50 % ያዳከመ፣ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን በማወሳሰብ እና መጠይቅን በማብዛት ነጋዴውን እያዳከመ ያለ፣ የተጋነነ ዋጋ ከደረሰኘ ውጭ በመተመን ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ፣ የውሸት ህግን ተገን ያደረገ ዘረፋ እያካሄደ ያለ፣ ያልሰሩትን ሰርተዋል በማለት፤ ነጋዴዎችን በግብር ከንግድ ውጭ እያደረገ ያለ፣ እንደ ቡና፣ የምግብ ዘይት የመሳሰሉት የምግብ ፍጆታዎችን በተለያየ ሰበብ ለራሱ ወይም ለአገዛዙ ቅርበት ላላቸው ድርጅቶች እያስተላለፈ ያለ፣ እንዲሁም ከግል ባንኮች ላይ በብድር ዘረፋን እያኪያሄደ ያለ አገዛዝ ነው። በመሆኑም እኛ ነጋዴዎች ህልውናችን ይጠበቅ ዘንድ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ መነሳት ያለብን አሁን ነው በማለት ገልጸዋል።

ከዚሁ ዘገባ ጋር ተያይዞ የመቀሌ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ማውጣት አልቻልንም በማለት እያማረሩ መሆኑን ባንጻሩ ደግሞ የዘረኛው አገዛዝ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ግብር መክፈል እያለባቸው ያልከፈሉ፣ ወደ ታክስ ሥርዓቱ ያልገቡ ‹‹ሕገወጦች›› በሚላቸው ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ሊወስድ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን ማስታወቁን ዘጋቢያችን ባስተላለፈልን ዘገባ ገልጹአል እንደዘጋቢያችን ሪፖርት የመቀሌ ከተማ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ወደሚመለከተው አካል ቢሄዱም፣ ፈቃድ መስጠት በመቆሙና መቼ እንደሚጀመር ባለመገለጹ ችግር ገጥሞናል ማለታቸውንና ፈቃድ መስጠቱ ግልጽ ባለመሆኑ ምክንያት መቋረጡ ብቻ ሳይሆን፣ የንግድ ፈቃድ ለማደስም ለሁለት ወራት እንዲጠብቁ መደረጉ በንግድ ሥራቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ሪፖርተር በመባል የሚታወቀው ለአገዛዙ ቅርበት ያለው ጋዜጣ መዘገቡንም አክሎ ገልጹአል።