የዘረኛው አገዛዝ በትር፡ ታማኝ አገልጋዮቹንም እየገረፈ ነው፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ምክትል ፕሬዚዳንት ከኃላፊነቱ መነሳቱ ታወቀ
በኢትዮጵያዊያን ትከሻ ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የሚገኘው የዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት በስልጣናቸው ላይ ስጋት የሚፈጥርባቸውን ማናቸውንም ሃይል ከማጥፋት ወደሁአላ እንደማይሉ በተደጋጋሚ ያሳዩና ያስመሰከሩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የቤሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንትና የወያኔ አገልጋይ የነበረው ሰብስቤ ንሳጼ ጋስ በግምገማ ሰበብ ከስልጣን መወገዱን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ አመለከተ።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት የቤሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወያኔያዊ ግምገማን ካካሄደ በሁአላ ሰብስቤን ከነሐሴ 29 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ያደረገ መሆኑ ታውቁአል። በክልሉ ለወያኔው ዘረኛ አገዛዝ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ባለስልጣናት የማባረር ተግባር በዚሁ ሳያቆም የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ታዬ ሀብቴ፣ የክልሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ባይሳ ቤሴ ወንበርንና የክልሉ የማይክሮ ፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ ዘለዓለም መንገባ በኮዬ በዚሁ ግምገማ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቱአል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ የቆየው ሰብስቤ ንሳጼ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ቀደም ባሉት ዓመታትም የክልሉ የውኃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ፣ የክልሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚና በሌሎችም ኃላፊነቶች ላይ መሥራቱን ምንጮቹ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢያችን በባለስልጣናቱ ላይ ይህ ርምጃ የተወሰደበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲገልጹለት በክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ በኤክስፐርትነት በማገልገል ላይ የሚገኙ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ ባለሙያን በስልክ አነጋግሮ ባገኘው ምላሽ፤ በይፋ እየተነገረ ያለው በክልሉ ላይ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር እጦት እየተንሰራፋና ከፍተኛ ሙስና እየተፈጸመ በመምጣቱ ነው የሚል ሲሆን፣ ነገር ግን ስለመልካም አስተዳደር እጦትና ስለሙስና ካወራን የአሳ ግማቱ ክጭንቅላቱ እንደሚባለው የሃገሪቱን ስልጣን ተቆጣጥረው የሚገኙት ባለስልጣናት በሙስናም ሆነ መልካም አስተዳደርን ባለማስፈን ቀዳሚውን ስፍራ በያዙና ርምጃውም በነሱ በጀመረ ነበር ይሁን እንጂ ወያኔ ባሁኑ ሰአት የተያያዘው ስልት፣ በጥርጣሬ አይን የሚያያቸውን፣ ዘረኛነትን መሰረት ላደረገ አሰራሩ አመቺ ሆነው ያላገኛቸውን ባለስልጣናት ሰበብ አስባብ በመፈለግ ማባረር ነው። እናም ያሁኑ ርምጃ ምንም የሚያስገርም አይደለም፣ ወይንም የሚያሳዝንም አይደለም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተግባራዊ እየሆነ የመጣ የተለመደ አሰራር ነው ብለዋል።
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ለአገዛዙ ታማኝና ታዛዥ ናቸው የሚባሉ ሆድ አደሮችን ወይንም የስልጣን ሱሰኞችን ወደ ከፍተኛ ስልጣን በማምጣት፣ እንደፈለገው ሲያሽከረክር ይቆይና፣ አልመች ባሉት ጊዜ ከስልጣን እንደሚያባርርና ወደ እስር ቤቶችም እየወሰደ እንደሚያጉራቸው በተደጋጋሚ ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።