ሾልከው ካመለጡ የአሜሪካ የዲፕሎማሲ ሰነዶች የምንማራቸው ሃቆች

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2005 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት  ውስጥ የአሜሪካ የዲፕሎማቲክ ሚስዮኖች ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የላኳቸው  መልዕክቶች ከአሜሪካ ቁጥጥር ውጭ በሆነ ቡድን እጅ ውስጥ ገብተው ሰሞኑን “ዊኪሊክስ” በተሰኘ ዓለም ዓቀፍ የመረጃ ድረገጽ ላይ ተዘርግፈዋል። በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ምስጢርና ጥንቃቄ የተላኩ መረጃዎች ለአደባባይ እይታ በቅተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ወደ አሜሪካ  የውጭ ጉዳይ መሥሪያ የተላኩ ከአራት ሺህ በላይ ሰነዶች ይገኛሉ።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እነዚህም መረጃዎች ሥርዓት ባለው መንገድ መመርመር ጠቃሚ ትምህርቶችን ይሰጣል፤ ለትግላችንም አስተዋጽኦ ይኖረው ይሆናል ብሎ ያምናል።

ሰነዶቹ በጥንቃቄ ከተጠኑ:-

  • በአምስቱ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ፓለቲካ በተመለከተ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች አተያይ ላይ የመጣው ለውጥ፣
  • ሰዎች ሲለዋወጡ በዲፕሎማሲው ላይ ያለው ተጽዕኖ፣
  • አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የፓሊሲ መሠረት ምንነት፣
  • የመለስ ዜናዌ  አገዛዝ በዲፕሎማቶቹ ዓይን ምን እንደሚመስል፣  እና

በመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ ዓይን ከፋች እውነታዎችን አንጥሮ ማውጣት ይቻላል ብሎ ግንቦት 7 ያምናል። ሆኖም መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ማንበብ፤ አንብቦም መረዳት እና ለትግላችን ያላቸውን እንድምታ መመዘን ጊዜ የሚፈጅ ጉዳይ ነው። ስለሆነም እስካሁን ከታዩ ሰነዶች የተገኙት አጠቃላይ ግንዛቤዎች የማስቀመጥ አስፈላጊና ወቅታዊነት ታምኖበታል።

በዚህም መሠረት አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዋሽግተን ወደሚገኘው የአሜሪካ የውጭ  ጉዳይ መ/ቤት ከላካቸው እና እስካሁን ከተዳሰሱት ሰነዶች አጠቃላይ ይዘት በመነሳት የሚከተሉትን ድምዳሜዎች  ላይ መድረስ ይቻላል።

I. ጥሬ ሃቆች

  1. የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘረኝነት፤ “ሁሉንም ጠቅላይ” አምባገነንነቱ እየጨመረ የመጣ መሆኑን እና በዚህም ምክንያት የሰላማዊው ፓለቲካ ሜዳ እየጠበበ መምጣቱን አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በደንብ ያውቃል፤ ይህንኑም ዋሽንግተን ለሚገኘው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሳውቋል።
  2. የመለስ ዜናዌ አገዛዝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን – በእስረኞች ላይ አሰቃቂ ሰቆቃዎችን (ቶርቸር) የሚፈጽም መሆኑን ጭምር – አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በደንብ ያውቃል፤ ይህንኑም ዋሽንግተን ለሚገኘው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሳውቋል።
  3. የመለስ አገዛዝ የሚደሰኩረው የኢኮኖሚ እድገት ውሸትነት፤ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና ሊያስከትላቸው ስለሚችሉ ፓለቲካዊ ውጤቶች አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በደንብ ያውቃል፤ ይህንኑም ዋሽንግተን ለሚገኘው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሳውቋል።
  4. ከመለስ ዜናዊ የቅርብ ባለሟሎች እንኳን ሳይቀር በሥርዓቱ የተማረሩ እና ተስፋ የቆረጡ መኖራቸው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መረጃ ደርሶታል ፤ ይህንኑም ዋሽንግተን ለሚገኘው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሳውቋል።

II. መራር እውነታ

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ፓሊሲ ላይ ይኸ ነው የሚባል ለውጥ አልታየም።

III. እንድምታ

ይህ ቢያንስ ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮችን  ያስጨብጠናል።

1. ፓለቲካ በንድፈሃሳብና በተግባር የቱን ያህል የተለያዩ እንደሆነ  እናይበታለን።

በመለስ ዜናዊ አገዛዝ እየደረሰበን ያለውን ግፍና መከራ ለኃያላን አገራት ማሳወቅ ጠቃሚ ቢሆንም እንኳን ማወቃቸው ፓሊሲያቸውን ለማስቀየር በቂ ላይሆን እንደሚችል ያረጋግጥልናል።  ይህ እንድምታ “መቼና ምን ሲሆን ነው ኃያላን አገሮች ከሌሎች አገራት ጋር ያላቸውን ፓሊሲ ለመመርመር ፈቃደኛ የሚሆኑት?” የሚለውን ጥያቄ  በጽኑ እንድናስብበት ያደርገናል።

2. የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ያለብን እኛው መሆናችን ያስገነዝበናል።

ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የምናደርገው ትግል የኃያላን አገራቱን ዲፕሎማቶችን ልቦና ቢማርክ እንኳን ተጨባጭ ድጋፍ የሚያደርጉበት ደረጃ ላይ አለመድረሳቸውን ሰነዶቹ ያረጋግጡልናል። ግንቦት 7 ከዚህ በፊትም ደጋግሞ እንደአስገነዘበው ሁሉ ለኢትዮጵያ መፍትሄ ማምጣት ያለብን እኛው ራሳችን ነን።

3. ድርጅታዊ ጥንካሬ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ያረጋግጥናል።

ለተሳካ የዲፕሎማሲ ሥራም የጠንካራ ድርጅት መኖር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ከሰነዶቹ  የምንረዳው እውነታ ነው።  የኃያል ሃገሮች ተጨባጭ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማግኘት  ጠንክሮ መገኝት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ  የሆነ መመዘኛ የመሆኑ ሃቅን ሰነዶቹ ይፈነጥቁልናል።

ስለሆነም ግንቦት 7 እንደትናትናው ሁሉ ዛሬም የዲፕሎማሲ ትግላችንን እናጠናክር፤  ሆኖም ግን የበለጠው ትኩረታችን ራሳችንን በማጠናከር ላይ ይዋል ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!