እስከ መቼ ከርሞ ጥጃነት?

ከሸንቃጣዉ ዘካሊፎርኒያ
ወያኔዎች ስልጣን ላይ ሲወጡ አብዮታዊ ዲሞክራሲንና ነጻ ገበያን በራሳቸዉ የፍልስፍና ፈለግና ርዕዮተ ዓለም አዋህደዉና አስታረቀዉ ለዓለም ህብረተሰብ የአመራር ችሎታቸዉንና አርቆ አስተዋይነታቸዉን ለማስመስከር ያልነፉት ጉራና ያልጎሰሙት ነጋሪት አልነበረም። ረሀብን እናጠፋለን፡ እንዲያዉም “…እህል ወደ ዉጭ አገር እንልካለን” እያሉ ነበር ሲመጻደቁ የነበሩት። እስከዛሬ ድረስ ወያኔዎች የለማኝ ቀምጥልነታቸዉ ሳያንስ ይባሱኑ ብለዉ እብሪት የተሞላበት ጥጋብ ተያይዟቸዋል። ወያኔዎች ብራዚልንና ቻይናን ምዕራባዉያን አገሮችን እንደማስፈራሪያ አድርገዋል ልክ ሁለቱ አገሮች ወያኔዎች በፈለጉበት ጊዜ የፈለጉትን ያህል የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ የሚያደርጉላቸዉ ይመስል። ይህ ሁሉ የፖለቲካ ዳንኪራ “ስለ እኛ ምንም አይነት የፖለቲካ ተቃዉሞ አታሳዩ” ለማለት ነዉ ምዕራባዉያን አገሮችን። ምክንያቱም ተቃዉሞ የሚያስከትለዉ የፖለቲካ ኩርፊያ ስለሚሆን “…ያ ደግሞ የፖሊሲ ለዉጥ ሊያስከትል ይችላልና” ነዉ መልእክቱ።

ድንቄም እቴ! “…ድህነትን በአምስት ዓመታት እናጠፋለን”፣ እንዲሁም “ኢትዮጵያ ከ2015 በሗላ የምግብ እርዳታ አያስፈልጋትም” የሚለዉ የአሁኑ የመለስ ዜናዊ ቀረርቶ የተመሰረተዉ በተነደፈዉ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ እድገት ፕላን መሰረት ሲሆን ይህም ፕላን ደግሞ መሰረት ያደረገዉ ገና ከምዕራባዉያን በልመና ከሚገኘዉ (ቁርጡ ባልታወቀዉ) ብድር ላይ ነዉ። “ሁለት አሀዝ ያለዉ የኢኮኖሚ እድገት አስቆጥረናል” እየተባለ ሲቦተለክ የተከረመዉን ጉራ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund) እንዲሁም ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ እና ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ዉድቅ አድርገዉታል። ገና ለገና ለሱማሌዉ ችግር ምዕራባዉያን እኔን ይፈልጉኛል ከሚል የፖለቲካ ቁማር የተነሳ “የፈለግሁትን ባደርግ ብድሩን አይከለክሉኝም” የሚል ልበ ደንዳናነት የተሞላበት አስተሳሰብ ያለዉ ይመስላል መለስ ዜናዊ። ከብድሩ ባሻገር በእድገት እርዳታ (development aid) ስም አገሪቱ የምታገኛቸዉ እርዳታዎች ብዙ መንግስታዊ ተቋማት እንደ ዩኒቨርስቲዎች፣ ሆስፒታሎችና የምርምር ተቋማት የመሳሰሉት የሚንቀሳቀሱት በዚሁ የእድገት እርዳታ ብርታት ነዉ። እንደነዚህ ያሉት የምዕራባዉያን እርዳታዎች ከተቋረጡ ቻይና ወይም ብራዚል ወጪዉን ለአገሪቱ አይሸፍኑም። ቻይናና ብራዚል ሊሰጡ የሚችሉት ብድር የኢንቨስትመንት ምላሽ (investment return) ሲኖር ብቻ ነዉ። የርዕዮተ ዓለም አጋሮቿ ለሆኑት ለሰሜን ኮሪያና ለኩባ እንኳን ቻይና የምትሰጠዉ ምላሽ የለሽ እርዳታ (non-returnable aid) እጅግ አናሳ ነዉ። እና የመለስ ዜናዊ በቻይናና በብራዚል እንደ ጉራ አድርጎ መመካት እሩቅ የሚያደርስ አይደለም። በሁለት ቢላ አሳምሮ መብላቱንና የህዝብ ግንኙነት ፖለቲካ ማካሄዱን መለስ ዜናዊ ጠንቅቆ ያወቀ አይመስልም። እብሪቱና ትምክህቱ ራዕዩን እንደ ጉም የጋረዱት ይመስላል።

የግንቦት ወር 2010 ምርጫ ዉጤትን ግግም ብሎ ተቀበሉ ይላል ጮሌዉ አያ ጅቦ መለስ ዜናዊ። ምዕራባዉያን አያዉቁብኝም የሚለዉ ፈሊጡ ጊዜዉ ያለፈበት መሆኑን ወይ አልተገነዘበም ወይንም ግድ የለዉም ቢነቃበት በይነቃበትም። እንደዉ በአጠቃላይ የፖለቲካ መሞላቀቅን የመረጠ ይመስላል። ለአገርና ለህዝብ ከሚበጀዉ ይልቅ የስልጣን እድሜዉን የሚያራዝመዉን ፖለቲካ ሙጥኝ ብሎ የተያያዘ መሆኑን መገመት አያዳግትም። ምዕራባዉያን በአሁኑ ወቅት ባሉበት የኢኮኖሚ ቀዉስ ሊሰጡ የሚችሉት የዉጭ እርዳታ ድሮ ከሚሰጡት እጅግ ያነሰ ነዉ። ሲሆን እንደ ብልህ መሪ ከአገር ዉስጥ ከተቃዋሚዎች ጋር እርቅ ፈጥሮ ከዉጭ አገሮች ጋር ደግሞ የዲፕሎማሲ መግባባትን ቢፈጥር የሚሰጠዉን የዉጪ አገሮች የእድገት እርዳታ ከፍ የማድረግ አጋጣሚን ይፈጥር ነበር። ምዕራባዉያን ከሰብአዊ እርዳታ ዉጪ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ብዙ የሚጨነቁ አይመስሉም።

በቅርቡ በብሄራዊ ባንክ የተወሰነዉ የዉጭ ምንዛሪ መጠን ማለትም ድሮ አንድ ዶላር በብር ሲመነዘር 13ብር ከ50 የነበረዉ አሁን ወደ 16 ብር ከ50 ሳንቲም መድረሱ ለአገሪቱ ጉዳት ነዉ እንጂ ጥቅም አያስገኝም። ዞሮ ዞሮ ዶላር ላለዉ ኢንቨስተር ጥሩ ነዉ። ሆኖም ግን የአገር ዉስጥ ከበርቴዎች (የወያኔ ተለጣፊ ያልሆኑት) እንደተኮረከሙ ይቆያሉ። የወያኔ ተለጣፊዎችና ጋሻ ጃግሮዎቻቸዉ ግን ይበለጽጋሉ። በዚህም የምንዛሪ ለዉጥ የመጀመሪያ ደስተኛነቱን የገለጸዉ አለም የገንዘብ ድርጅት መሆኑ በዜና ማሰራጫዎች ተዘግቧል።

ወያኔዎች ለትራንስናሽናል ኮርፖሬሽኖች መሬት እየሸጡ (የሚመረተዉ ምርት እንኳ አገር ዉስጥ ሳይሸጥ) አገሪቱን እንደ ጓተማላ (መካከለኛዉ አሜሪካ የምትገኝ አገር) 40% ምድርዋ የአሜሪካ ኮርፖሬሽን (ዩናይትድ ፍሩት ካምፓኒ) ንብረት እንደሆነዉ ሊያደርጓት ቆርጠዉ ተነስተዋል። ትግራይ ዉስጥ ካለዉ ለም መሬት አንድም ጋት መሬት ለዉጭ አገር ኮርፖራሽን አልተሸጠም። የአገር ዉስጥ ከበርቴዎች እንዳያድጉ በሰበብ በአስባቡ እየኮረከመ ወደ ሗላ ያስቀራል። የአገር ዉስጥ ከበርቴዎች መሬት ቢገዙ የተመረተዉን መጀመሪያ አገር ዉስጥ እንዲሸጡ ማስገደድ ይችላል። ሆኖም ለትራንስናሽናል ኮርፖሬሽኖች መሬት ተሽጦ የሚገኘዉ የዉጭ ምንዛሪ በጣም አናሳ መሆኑ እየታወቀ መሬት መሸጡ በምዕራባዉያን ዘንድ ድጋፍ ያስገኝልኛል ከሚል ግንዛቤ የተነሳ የተደረገ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም። ቢሆንም ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ በጣም ያመዝናል።

የዩናይትድ ስቴትስ ስቴት ዲፓርትመንት በ2010 ባወጣዉ አመታዊ የሰብአዊ መብት ሪፖርት የወያኔ/ኢህአዴግ አምባገነን መንግስት ብዙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን እንደፈጸመ አጋልጧል። ከሰብአዊ እርዳታ ዉጪ የዩናይትድ ሰቴትስ መንግስት ከወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ጋር ብዙ የፖለቲካ ወዳጅነት እንደማይኖረዉ በይፋ ከተገለጸ ሰንበት ብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አያ ጅቦ መለስ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ዲ ኤል ፒ ፓይፐር እየተባለ በሚታወቀዉ የሎቢይንግ ካምፓኒና የጆርጅ ቡሽ አማካሪ በነበሩ ግለሰቦች ደጅ ጠኝነት ኮሉምቢያ ዩኒቨርስቲ መስከረም 22 ቀን 2010 ንግግር እንዲያደርግ የዩኒቨርስቲዉ ፕረዚደንት መጋበዛቸዉ ዝንተ ዓለም ዋሺንግተን ዉስጥ የገንዘብ ሀይል የሚያደርገዉ የፖለቲካ ቧልት ዉጤት መሆኑ አዲስ ሊሆንብን አይገባም። በዩናይትድ ሰቴትስ ሴኔት የኦክላሆማ ሴኔተር የሆነዉ ወግ አጥባቂዉ ጀምስ ኢንሆፍና የዲ ኤል ፒ ፓይፐር የፖለቲካ ደላላ የሆነዉ ዲክ አርሜ (የቀድሞዉ ሪፐብሊካን ሃዉስ ማጆሪቲ መሪ) በጋራ ለመለስ ዜናዊ ትልቅ እዉቅናና ድጋፍ ከዩናይትድ ሰቴትስ መንግስት እንዲሰጥ ሁል ጊዜ እንደጣሩ ነዉ ያሉት። ይህ ሁሉ ጥረት እየጎደፈ ያለዉን የመለስ ዜናዊን ስምና ዝና ነፍስ ሊዘሩበት እንደሆነ ለመረዳት ምንም አያዳግትም። መለስ እንዲህ ያሉትን አጋጣሚዎች ሲጠቀም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች ደግሞ ሌት ተቀን እጅ እጅ የሚለዉን ቱልቱላቸዉን ይነዛሉ። በሚገኘዉ አጋጣሚና ቀዳዳ የመለስ ዜናዊ ስም እንዲንሰራራና አንዲገን ለማድረግ የሚወጣዉ የገንዘብ መጠን እጅግ በጣም ብዙ ነዉ።

እብሪትና ዘረኝነት የሌለበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካ አመራር ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ እልቂት፣ የፖለቲካ መካረርና ቀዉስ ባልተፈጠረም ነበር። እልክ፣ ማን አህሎኝነት፣ ጠባብ ብሔረተሰብነትና ራስ ወዳድነት ባይኖር ኖሮ እንደ ልደታ ቆሎ የተበታተኑት የኢትየጵያ ልጆች ወደ አገር ቤት ጎርፈዉ የአገር ግንባታቸዉን በጀመሩ ነበር። አምባገነንነት ቢያኖር ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነዉ። ስለወደፊቱ ደንታ ቢስነት ወደ ፊት የሚያስከትለዉ ጣጣ ብዙ ነዉ። ሆኖም ግን መለስ ዜናዊ ይረዳዋል ብዬ ለማመን በጣም እቸገራለሁ። ቢረዳዉም ደግሞ ደንታ የለዉም ማለት ነዉ ወደፊት እሱን ለሚጠብቀዉ ጣጣ። ወይም መዉጫዉን ከአሁኑ ጀምሮ አዘጋጅቷል ማለት ነዉ። መቼ ይሆን ብስለት የሚከሰተዉ? እስከ መቼስ ከርሞ ጥጃስ ይኮናል?

[email protected]