ዊኪ ሊክስ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ምስጥራዊ ማስረጃ ወያኔ ህግ አድርጎ ያወጣው “የፀረ ሽብርተኝነት” አዋጅ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለመወንጀል በሥራ ላይ እንዳማይውል ለአሜሪካ መንግሥት ተገልጾ አንደነበር ይፋ ሆነ

የአሜሪካ ውጪጉዳይ ሚንስቴር በተለያዩ አገሮች ከሚሠሩ ዲፕሎማቶቹ ያሰባሰባቸውን ምስጥራዊ ሪፖርቶች ለህዝብ እይታ በማቅረብ ላይ የሚገኘው ዊኪሊክስ በመባል የሚታወቀው የመረጃ ድረገጽ፤ ባለፈው ሳምንት ሃሙስ እንደፈረንጆች አቆጣጠር ኦገስት 25 ያሰራጨው መረጃ ፤ ወያኔ ተቃዋሚዎቹን ለማስፈራራት ህግ አድርጎ ያወጣው “የጸረሽብርተኛነት” አዋጅ በፓርላማ ተብዬው የወያኔ ሸንጎ ከመጽደቁ በፊት አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜርካ ኤምባሲ ቀርቦ መግለጫ እንደነበር አመለከተ።

ዊኪ ሊኪስ ይፋ ባደረገው በዚህ መረጃ ስለ የጸረሽብር ረቂቅ አዋጁ ለወቅቱ የአሜሪካ አምባሳደረ አምባስደር ያማማቶ ማብራሪያ ለመስጠት የተላከው ዘረኛው መለስ ዜናዊ በጊዜያዊ ጥቅምና የሥልጣን ትርፍራፊ የራሱ ጄሌ ካደረጋቸው አንዱ የሆነው ብርሃኑ አዴሎ እንደሆነ ተገልጾአል። ብርሃኑ አዴሎ በመለስ ዜናዊ ጽ|ቤት ሃላፊና በምንስትርነት ማዕረግ የካቢኔ ሹም እንደነበር የገለጸው የአሜሪካ ኤምባሲ መልዕክት፤ የጸረ ሽብር አዋጁን ጨምሮ ከምርጫ 97 ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ የታወጁትን ሌሎች ተመሳሳይ አፋኝ ህጎች በሙሉ በማርቀቁ ሥራ ብርሃኑ አዴሎ ዋና ተዋናይ እንደነበረ በሪፖርቱ አካቶታል።

ስለ ረቂቅ ህጉ ለአሜሪካው አምባሳደር ያማማቶ መግለጫ መስጠቱ የተገለጸው ብርሃኑ አዴሎ፤ የጸረሽብርተኝነት ህጉ አገዛዙን የሚቃወሙትን የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለመከሰስ በተግባር ላይ የሚውል ሳይሆን በህዝብ ንብረትና ህይወት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱትን ሽብርተኞች ለመከላከል ነው ብሎአል። መንግሥትን በሃይል ከሥልጣን ለማውረድም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል የሚደረግ ማንኛውም አይነት በማስረጃ የተደገፈ ወንጀል በመደበኛው የወንጀል ህግ ያስጠይቅ እንደሆን እንጂ በአዲሱ የሽብርተኝነት አዋጅ አያስከሥስም ያለው ብርሃኑ አዴሎ በምርጫ 97 የአዲስ አበባ ተመራጭ ከንቲባ የነበሩት የዶ|ር ብርሃኑ ነጋን ሥም ጠቅሶ የርሳቸው ህዝብን በመንግሥት ላይ ለአመጽ ማነሳሳትም ሆነ መንግሥትን በሃይል ለመለወጥ የሚያደረጉት ሙከራ በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ሥር የሚፈረጅ አይደለም ማለቱም ተመዝግቦአል።

የጸረ ሽብርተኝነት ረቂቅ አዋጁ በፓርላማ ተብዬው የወያኔ ሸንጎ ቀርቦ ከመጽደቁ 4 ቀናት በፊት ለምን ለአሜሪካ ኤምባሲ ማቅረብ እንዳስፈለገ በሪፖርቱ ውስጥ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ አንዳንድ የምዕራባዊያን አገሮች ተወካዮችና የሰብ አዊ መብት ተሟጋቾች ረቂቁ ህጉን በግልጽ ቋንቋ ተቃውመውት ስለነበር የተነሳውን ተቃውሞ ለማመከን የአሜርካንን ድጋፍ ለማግኘት አስፈልጎአቸው እንደሆነ ግልጽ አድርጎታል።

የወያኔው ጀሌ ብርሃኑ አዴሎ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ የፖለቲካ ተቃውሞን ለመደፍጠጥ አይደለም ይበል እንጂ ዲሞክራሲን በአገሪቱ ለማስፈን ይቻል ዘንድ የመንግሥት ለውጥ ያስፈልጋል ብሎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ድርጅታችን ግንቦት 7ን ጨምሮ ኦነግንና ኦብነግን በሽብርተንነት መፈረጃቸው የአደባባይ ምስጥር ነው። አምባገነኖች መውደቂያቸው ሲቃረብ የሚቃወማቸውን ሁሉ በበሽብርተኝነት እንደሚከሱ ከቱኒዚያው ቤን አሊ ከግብጹ ሆሴን ሞባረክና ከሊቢያው ጋዳፊ የተመለከትነው ስለሆነ ህዝባችን የመለስ ዜናዊን ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ ከትክሻው ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚያደረገውን ትግል እስከመጨረሻው እንደሚገፋበት የግንቦት 7 እምነት ነዉ።