የአንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ ከአስካሉካ ኩባንያ ዝርፊያ በስተጀርባ እንዳለ ተገለጸ

ቀደም ብሎ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውን የአለም ዋንጫ ጨዋታ እናሳያችሁዋለን በሚል ምክንያት ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ እንደጠፋ ከተገለጸው አስካሉካ ኩባንያ ጀርባ አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት መኖራቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ዜና ማግኘቱን የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ኢሳት አስታውቋል።

ኢሳት በዘገባው በሀሌታ ማስታወቂያ ድርጅት ተቀናብሮ በሳምሶን አድቨርታይዚንግ የቀረበው ማስታወቂያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መቅረቡንና ተጓዦቹ 37 ሺ ብር በወጋገን ባንክ እንዲያስገቡ ተጠይቀው ከ 1ሺ በላይ ሰዎች ማስገባታቸውን ገልጸዋል ብሏል። በመቀጠልም የአስካሉካ ትሬዲንግ ባለቤት “መንግስት ህጋዊ ፈቃድ እንደሰጣቸው 3 ሺ የሚሆን ቪዛ እንደ ተፈቀደላቸው ” በሳምሶን አድቨርታይዚንግ በሚታተመው ኢትዮቻናል በተባለ ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ ቀርበው ከተናገሩ በሁዋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ 55 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ችለው ነበር ሲሉ ምንጮቹ መግለጻቸውን አስታውቋል።

አስካሉ ኩባንያ የመንግስትን ባለስልጣናትን ሽፋን አድርጎ ማጭበርበሩ እንደተደረሰበት ፣ ከ 1 ሺ 400 በላይ የወጋገን ባንክ ደረሰኞችን ዬያዙ ኢትዮጵያውያን ግንፍሌ አካባቢ በሚገኘው አስስካሉካ ትሬዲንግ ፊት ለፊት ተገኝተው ተቃውሞዋቸውን ለማሰማት ሞክረው ነበር። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቃውሞውን በስፍራው ተገኝቶ የዘገበ ቢሆንም፣ ዜናውን ይፋ እንዳያወጣው በመንግስት ባለስልጣናት መከልከሉን እንደገለጸላቸው በድርጊቱ የተሳተፉት ወገኖች መግለጻቸውን ኢሳት ዘግቧል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አስተያየት የተጠየቁ ተበዳዮች የአስካሉካ ትሬዲንግ ባለቤት በፖሊስ ታጅበው ከአገር እንዲወጡ ከተደረጉ በሁዋላ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አዘዣ ግለሰቡ እጃቸውን እንዲሰጡ በቴሌቪዥን ቀርበው የይስሙላ ንግግር አድርገዋል ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል። ተበዳዮቹ አስቀድመው ያቀረቡት የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ፣ በፖሊስ ከተደበደቡ ና የኩባንያው ባለቤት አገር ጥለው እንዲጠፉ ከተደረጉ በሁዋላ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ እንደተፈቀደላቸው ባለጉዳዮቹ ያማርራሉ።