ህወሃት ባለፈው ሳምንት ያካሄደው ምርጫ በወያኔ ደጋፊዎች መካከል መከፋፈልን መፍጠሩ ታወቀ
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተጠናቀቀውን አስረኛው የህወሃት መደበኛ ጉባኤ ተከትሎ የተካሄደው ምርጫ በወያኔ ደጋፊዎች ዘንድ መከፋፈልን መፍጠሩ ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት (ወይም ኢሳት) በጉዳዩ ላይ ባቀረበው ዘገባ፥ “አዲሱን የስልጣን ሽግሽግ የሚደግፉት… በአቦይ ስብሀት ነጋና በዶ/ር ገብረአብ በርናባስ መወገድ ደስታቸውን ሲገልጹ፣ የስልጣን ሽግሽጉን የሚቃወሙት ደግሞ በወ/ሮ አዜብ መስፍንና አለቃ ጸጋየ በርሄ ወደ አመራር ቦታ መምጣትና በአቶ አርከበ እቁባይ መገለል የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፤” ብለዋል። አይጋ ፎረም በተባለው የወያኔ ድረ-ገጽ ላይ የተገለጹት እና ኢሳት የጠቀሳቸው አስተያየቶች፣ የዝግጅት ክፍላችን ይህንን ዘገባ ባጠናቀረበት ሰዓት ከድረ-ገጹ ላይ ተነስተዋል።
በኢሳት ዘገባ ላይ ከተጠቀሱት እና በወያኔ ደጋፊዎች ከተፃፉት አስተያየቶች ውስጥ አንዱ መለስ ዜናዊ የድርጅቱን ስልጣን በዘመዶቹ እና በጓደኞቹ እየሞላ ነው ሲል ከሷል። የዘረኛው አምባገነን ባለቤት አዜብ መስፍን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና መመረጧን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።
በተጨማሪም፥ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ለምሳሌ ጸጋየ በርሄ ብቃይ የሌለው ሰው ሆኖ ሳለ እንደ አርከበ እቁባይ ባሉ ሰዎች ፈንታ መመረጡ መለስ ፖሊት ቢሮውን በ”እሺ-ባዮቹ” ስለመሙላቱ ማረጋገጫዎች ናቸው ባዮች ናቸው። አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ በተሾመበት ወቅት በሰራው ስራ በህዝቡ ዘንድ ታዋቂነትን እያተረፈ በመምጣቱ በመለስ ዜናዊ እና በሚስቱ ጥርስ ውስጥ እንደገባ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት የህወሃት መሪ እና በድርጅቱ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረው፤ ባለፈው ሳምንት ግን ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነቱ እንኳ በእርጅና ስም የተወረወረው ስብሃት ነጋም አርከበ እቁባይ መለስ ዜናዊን እንዲተካ ደግፎ በመገኘቱ ከዘረኛው አምባገነን ጋር መጋጨቱ ይነገራል። ይህም ጉዳይ በስብሃት ነጋ እና በአዜብ መስፍን መካከል ካለው ሽኩቻ ጋር ተደማምሮ በወያኔ ቁንጮዎች መካከል ያለውን መቃቃር አባብሶታል።
ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚናገሩት፥ ባለፈው ሐሙስ በህወሃት ውስጥ የተካሄደው ምርጫ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፣ መለስ ዜናዊ እንደ ማንኛውም አምባገነን ሰው ያለማመን ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ ዙሪያውን በዘመድ አዝማድ እና ጓደኞች መሙላት መጀመሩን ነው።