የመለስ ዜናዊን ወደ አሜሪካን ሃገር መጓዝ በመቃወም ሰልፍ ሊደረግ ነው
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2003 ጀምሮ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚካሄደው የዓለም ሃገራት መሪዎች መድረክ በዚህ ዓመት በሚያደርገው ስብሰባ የዓለማችን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና ተጸኖው በሚል ርእስ መለስ ዜናዊ ጽሁፍ እንዲያቀርብ መጋበዙን የዩኒቨርሲቲው ድረገጽ አስታውቋል።
በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ፥ በዓለማችን ፈታኝ እየሆኑ በመጡ ወቅታዊ የፖለቲካ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ችግሮች ዙሪያ ውይይትና ክርክሮች የሚደረጉ ሲሆን ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የሚገኝበት ስብሰባ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሮቱንዳ ሎው ሊብራሪ ሴፕቴምበር 22 ቀን 2010 ከ 4 ፒኤም እስከ 5 ፒኤም እንደሆነ ታውቋል።
የዘረኛውን አምባገነን ወደ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መጋበዝ ተከትሎ በውጭ ሃገራት የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ካሁኑ ከፍተኛ ተቃውሞና ቁጣ በመግለጽ ላይ ያሉ ሲሆን ወደ ዩኒቨሪሲቲው በሚመጣበት ወቅትም የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል። በውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲን በተቃውሞ ኢሜይሎች፣ ስልክ ጥሪዎችና ደብዳቤዎች እያጨናነቁ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። ቀደም ሲል የመለስ ዜናዊን መምጣት ለማስተዋወቅ በድረ-ገጹ ላይ ባኖረው ጽሁፍ መለስ ዜናዊን ያሞገሰው ተቋምም በርካታ ተቃውሞዎችን ከተቀበለ በኋላ ሙገሳውን እንዳስወገደ ለመረዳት ችለናል።
በዚህ አጋጣሚ የግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ዘረኛና አምባገኑን መለስ ዜናዊን ለመቃወም በሚደረገው ሰልፍ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ፤ እንዲሁም በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ማህበረሰብ የሃገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲገነዘብ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪውን ያቀርባል።