ድንበራችንን እናስምርበት

ከዝግጂት ክፍላችን

ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በውጭ አገራት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ወይም በባለስልጣናቱ ጉብኝቶች ላይ የሚደረጉ የሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞዎችን በሚመለከት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት አመለካከታችንን ገልጸናል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የተቀደሱ ሆነው ሳሉ፤ ዋናውን እና አገዛዙን ከነሸንኮፉ ነቅለን የማስወገዱን የአገር ቤቱን ስራ ባልረሳ መልኩ መሰራት አለባቸው ብለናል። ያ እንዳለ ሆኖ ግን ዛሬ ደግሞ በስራዎቹ ቅድስና ላይ ያሰመረ ሃተታ ለማቅረብ ወደናል።

ከዚህ ቀደም ባቀረብናቸው ዘገባዎች እንደገለጽነው፥ ወያኔ በውጭ አገራት የሚኖሩ እና እስከዛሬ የእግር እሳት፣ የጭቃ ውስጥ እሾህ ወይም የብዙ ስቃይ ምንጭ የሆኑበትን ኢትዮጵያውያን በቁጥጥሩ ስር ለማዋል ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ነው። ማህበራዊ ተቋሞቻቸውን ሰርስሮ ለመግባት፤ በየቤተክርስቲያኖቻቸው ተደብቆ ገብቶ ክፍፍልን ለመፍጠር እና አገዛዙን በሚረዳ መልኩ የውጭውን ማህበረሰብ መሰነጣጠቅ እና በተቻለ መጠንም አገዛዙን የሚደግፉ ሰዎችን በጥቅም አባብሎ ማፍራት በእቅድነት ተይዞ ወደ ተግባር ከተገባ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ እቅድ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ፊት እየተገፋ ይገኛል።

ይህም በተለያዩ ከተሞች እራሱን እየገለጠ ይገኛል። ከአንድ ወር በፊት ያስተላለፍነው ዘገባ በሆላንድ አገር በአምስተርዳም ከተማ ኢትዮጵያውያን ባካሄዱት የእስፖርት ፌስቲቫል ላይ አንድ የወያኔ ቅጥረኛ ተገኝቶ ሊያስነሳ ስለሞከረው አተካራ ተናግረናል። በዚህ ሳምንት እሁድ እለት ደግሞ በሎስ አንጀለስ ከተማ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተዘጋጀ አመታዊ ፌስቲቫል ላይ፤ በዘጠኝ አመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የወያኔው ቆንስላ ድንኳን ተከራይቶ የዘረኛውን አገዛዝ ጥቅም ለማንሰራፋት ሲሰራ ተስተውሏል። ነገሩ አልሳካ ብሎ ጥቂት ደፋር ኢትዮጵያውያን የድንኳኑን በር ዘግተው ቆመው ለሚያልፈው ሰው ሁሉ የአገዛዙን ጨቋኝነት ሲያስረዱ ውለዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት፥ ዘረኛው አምባገነን በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ንግግር ያደርጋል። ኮሎምቢያ ዪኒቨርሲቲ፥ በነፃ ውይይት ስም ቢቻለው ሳጥናኤልንም ጭምር ሊጋብዝ የሚቃጣው ተቋም ይመስላል። ከዚህ ቀደም በገዛ አገሩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን የሚያካሄድ አገዛዝ መሪ የሆነውንና ዘረኛ አመለካከቶችን በመስበክ የሚታወቀውን የኢራኑን አህመዲነጃድ ለንግግር ጋብዞ ነበር። ስለዚህም መለስ ዜናዊን መጋበዙ የሚገርም ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ፥ በነፃ ውይይት ስም አንድን ዘረኛ አምባገነን መጋበዝ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ይህን አምባገነን ማሞጋገሱ ግን ሌላ ጉዳይ ነው።

የመለስን መምጣት አስመልክቶ በዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ላይ የወጣውን ማስታወቂያ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን የቁጣ መልክቶችን መላካቸውን ተረድተናል። ከዛ በኋላም ዩኒቨርሲቲው ሙገሳውን እንዳስወገደው ለመረዳት ችለናል። እኛም ጤንነታቸው ስለተመለሰላቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ልንላቸው እንወዳለን።

በኒው ዮርክ አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዘረኛው አምባገነን ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ እና ለተቋሙ ማህበረሰብ ወደ ግቢያቸው ስለሚመጣው ወንጀለኛ ለማስረዳት በስፍራው እንደሚሰባሰቡ ከአስተባባሪዎቹ የደረሰን መግለጫ ይጠቁማል። ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በተቻላቸው መጠን በስፍራው በመገኘት ሰልፉን እንዲቀላቀሉ ያበረታታል።

ከጥቂት አመታት ወዲህ በውጭ አገር የሚደረጉ ሰልፎች እና ጩኸቶች ምንም ጥቅም የላቸውም የሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት በውጭ አገሩ ማህበረሰብ ውስጥ እየተስፋፋ ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት፥ አንዳንዶች በውጭ አገራት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አገር ቤት በምናደርገው ዋና ትግል ላይ ሊኖረን የሚገባውን ትኩረት ይቀንሱታል ከሚል ስጋት ነው። ምንም እንኳ የአገር ቤቱ ትግል ከፍተኛውን ትኩረት እንደሚጠይቅ ብንስማማም፤ ነገር ግን ደግሞ እዚህ የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በትኩረት፣ በትጋት እና ስልታዊ በሆነ መንገድ ብንፈጽም እጅጉን ጠቃሚ እንደሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።

በሚቀጥለው ረቡእ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተገኝቶ መለስ ዜናዊን ማጋለጥ በአገራችን ያላገኘነውን እድል ይሰጠናል። ረቡእ በኒው ዮርክ፥ የዘረኛው አምባገነን እጆች የታሰሩ ይሆናሉ፤ ተኩስ የሚባል አጋዚ አይኖርም። መለስ ዜናዊ ቁጭ ብሎ ቀድሞ ያላጠናውን ጥያቄ ከህዝብ ለመቀበል ይገደዳል። ውድ ኢትዮጵያውያን፥ እናንተ ደግሞ በስብሰባው ላይ እንድትገኙ ከትምህርት ተቋሙ ግብዣ ተደርጎላችኋል። ረቡእ በኒው ዮርክ፥ መለስ ዜናዊ ተሾመ ቶጋን ይዞ መምጣት አይችልም። ዘረኛውን አምባገነን ጥያቄ ስትጠይቁት ቆጥ ላይ ቁጭ ብሎ ማይክራፎናችሁን የሚዘጋባችሁ “እሺ-ባይ” ሹመኛ አይኖርም። እባካችሁን በስፍራው ተገኙ፥ እድሉን ተጠቀሙበት እንላለን።

ዘረኛውን አምባገነን ከመጋፈጥ በተጨማሪ፥ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ ዝናውን ማንሰራፋትም አለብን። ይህ ብዙ ሺህ ዶላር የወጣበት ንጹፍ ሙሉ ልብስ የሚለብስ ሰው፤ ልብሱ ገለጥ ሲደረግ ሰውነቱ በንጹሃን ህጻናት እና እናቶች ደም የተለቀለቀ መሆኑን በራሪ ጽሑፎችን እና የጥቃቱ ሰለባዎችን ፎቶግራፎች ይዘን መገኘት አለብን። “ይኸው ኮሎምቢያ፥ ውድ እንግዳችሁ መለስ ዜናዊ [ፈረንጆቹ ራሳቸው ሲተርቱ እንደሚሉት] ከቁም ሳጥኑ ውስጥ የሰው አጽም የሞላበት ነው” ልንላቸው ይገባል።

ሰልፉ በውጭ አገር ያሉትንም ሆነ አገር ቤት ታፍነው ያሉትን ኢትዮጵያውያን ስሜት በሚገልጥ መልኩ በቁጣ እና በድፍረት የተሞላ ሊሆን ይገባዋል፤ ይሁን እንጂ ለሰው ልጅ ነፍስ ያለንን ክብርም ሊገልጽ ይገባዋል፤ እንደ መለስ ላሉ ሰው በላ አምባገነኖች እንኳ ሳይቀር የምንመኘው ነፃና ፍትሃዊ ፍርድን እንጂ ኢ-ፍትሃዊ ግድያን እንዳልሆነ ልናሳውቅ ይገባናል።

ባጠቃላይ፥ ከሃተታችን መጀመሪያ ላይ ልናስታውስ እንደሞክርነው፥ የወያኔን ቁንጮዎች እና ቅጥረኞች ኮቴ እየተከታተልን ድንበራችንን እናስምርበት፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ተቋሞቻቸውን ሊከፋፍሉ እንደማይችሉ እንንገራቸው፤ አለቃው ማን እንደሆነም እናስታውቃቸው እንላለን። የዚህኛው ጦርነት ጥያቄ፣ የራስ በሆነው ነገር ላይ ባለቤትነትን የማወጅ ወይም አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ነው።