የአደባባይ ምስጢሮች – የትኛው ጋዳፊ?

የትኛው ጋዳፊ?

አራት ኪሎ አካባቢ ቡና እየጠጣሁ ጋዜጣ እያነበብኩ እንዳለሁ አንድ ወጣት በኪራይ የሚነበብ ጋዜጦችን ይዞ ማንበብ ይጀምራል፡፡ ትንሽ እንዳነበበ ጋዜጣ አዟሪውን “አንተ! ጋዳፊ የት ገባ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ለጥያቄው ሳይሆን ለመልሱ በመጓጓት ሁላችንም ወደ ጋዜጣ አዟሪው ዐይኖቻችንን አፈጠጥን፡፡ አንዳዶች ደግሞ ወደ ጠያቂው አትኩረው በመገረም ይለመከቱ ጀመር፡፡ ምክንያቱም ጋዜጣ አዟሪው ጋዜጣ አዙሮ መሸጥ እንጂ ከኛ የተሻለ መረጃ እንደማይኖረው የታወቀ ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ ጋዜጣ አዟሪው ቀልቡ ከጋዜጣ ማዞሩ ላይ እንጂ የወጣቱን ጥያቄ አላደመጠም ነበር፡፡ በድጋሚ “አንተ ! ጋዳፊ የት ገባ” ሲል ጠየቀው፡፡ በዚህ ጊዜ ጋዜጣ አዟሪው፡- “የትኛው ጋዳፊ? !” ሲል ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል፡፡
“የሊቢያው ጋዳፊ ነዋ ! የኛማ ሕዝቡን ላምስት ዓመት ኮንትራት አስፈርሟል !” ሲል ሁላችንም ተሳሳቅን፡፡

“የጉግማንጉግ ዘመን”

አያቴን ከማስታውስበት አንዱ ዘወትር ፀሎቱን ሲያሳርግ “አምላኬ ሆይ በተደጋጋሚ “ከጉግማንጉግ ዘመን ጠብቀን” እያለ የሚያደርገው ፀሎት ነው፡፡ ቃሉን በተደጋጋሚ እሰማው ስለነበር አንድ ቀን የጉግማንጉግ ዘመን ማለት ምን ዓይነት ነው? ብዬ ጠየኩት፡፡ “ምን ያደርግልሃል ኤዲያ!” አለኝ በጥላቻና ሐዘኔታ በተደበላለቀ ስሜት እየተመለከተኝ፡፡ እንዴ እኔ እኮ ለማወቅ ነው? አባዬ ለምን አታስረዳኝም ብዬ በአይኔም አንገቴን ግራና ቀኝ እያዘዋወርኩት ተለማመጥኩት፡፡
“ምን መሰለህ ልጄ ክፉ ቀን አይጠቅምህም፤ መስማትም የለብህም ብዬ ነው፡፡ የዛሬ ዘመን ልጆች ሁሉንም ካለወቅን ትላላችሁ፡፡” አለኝና ቅር አለው ትንሽ አሰብ ካደረገ በኋላ ክፉ ቀን ይመጣ እንደሆነ እንደ ተኩላ በአንድ ጊዜ ፈሰው ያገኙትን ሁሉ ተረባርበው በልተውና አወድመው የሚሄዱ መንጋ ይመጣል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥፋትና መንጋ አገርን ወሮ ሲያጠፋ የጉግማንጉ ዘመን ይባላል፡፡ ጥፋትና ውድመት ከፈጸሙ በኃላ በነው ይጠፋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዘመን እንዳይመጣ ዘወትር መፀለይ ያስፈልጋል፡፡ ሁሌ ስትፀልይ እግዚአብሄር ሆይ የጉግማንጉግ ዘመን አታምጣብን እያልክ ፀልይ” አለኝ
በልመናና በአደራ ኑዛዜ መልክ እየተመለከተኝ፡፡ እኔም ሁልጊዜ ጉግማንጉ የሚል ቃል ከልጅነቴ ጀምሮ የጥላቻና የፍርሃት ስሜት ፈጥሮብኝ አደኩኝ፡፡ ቃሉንም አልወደውም፡፡ ዛሬ የጉግማንጉግ ዘመን አለን?

ፍኖተ ነጻነት እትም 6