ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተያያዘውን የእስራት ዘመቻ ቀጥሉአል፣ በቅርቡ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አካላትን አሰረ

ህዝብን በማፈንና በጠመንጃ ሃይል በማስፈራራት እየገዛሁ እኖራለሁ በሚል ከንቱ ቅዠት የተዋጠው ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንጹሃን ዜጎች ላይ የጀመረውን እስራትና አፈና በተጠናከረ መልኩ በመቀጠል ሰሞኑን ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላትን ማሰሩን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ። እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት በዘረኛው አገዛዝ የታሰሩት ሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አካላት አንደኛው የኦሮሞ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፊዲን)ምክትል ሊቀመንበርና የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ሲሆኑ ሌለው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረሱ(ኦብኮ) ፤ አቶ ኦልባና ሌሊሳ መሆናቸው ታውቁአል።

እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ የታሰሩት፤ በቅርቡ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ሲሆን የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረሱ(ኦብኮ) የአቶ ኦልባና ሌሊሳ ክስ፤ ከሽብርተኘነት ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን ፤እስካሁን የተገለፀ ነገር ነገር አለመኖሩን ለማወቅ ተቺሉአል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ኦፊዲን) ዋና ፀሀፊ አቶ በቀለ ነገአ፤ የወያኔው አገዛዝ ሁለት የታቃዋሚ መሪዎችን በፈጠራ ክስ ማሰሩን በማውገዝ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመነሳት ይህን አገዛዝ “በቃ!”ሊለው ይገባል ሲሉ ጥሪ ማቅረባችውን ዘግቡአል።

እንደ ኢሳት ዘገባ ከውስጥ በህዝባዊ ብሶት ፤ከውጪ በዓረብ አገራት በተከሰተው አብዮት ከፍ ያለ ውጥረት ውስጥ የገባው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን፣ የኦጋዴ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄንና ግንቦት ሰባትን “በሽብርተኝነት” በመፈረጅ -በሀሳባቸው ለአገዛዙ ስጋት መስለው የሚታዩ ዜጎችን ሀሉ ከሶስቱ ድርጅቶች ከአንዱ ጋር በማገናኘት ማሰርን እንደ አቅጣጫ መያዙን፤ ውስጥ አዋቂዎች ገልጸዋል ብሉአል።

የወቅቱ የኦፊዲንና የመድረክ ሊቀመንበር ዶክተር ሞጋ ፈሪሳ ፤ የዘረኛው አገዛዝ በታሰሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ላይ የሚያሰማውን ክስ ያጣጣሉት ሲሆን፤ ሁለቱም የታሰሩት ከፓርቲዎቻቸው ባገኙት ውክልና መሰረት ከውጪ አካላት ጋር ግንኙነቶችን ያደርጉ ነበር ማለታቸውን ጠቅሱአል። በመቀጠልም በነዚህ ግንኙነታቸው በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ በርቀት በሚገኙ አካባቢዎች ስለተከሰቱ ድርቆች ተከታትለው የሚሰጧቸው መረጃዎች፤ በተደጋጋሚ ዘረኛው አገዛዝ ሲለው ከነበረው ጋር ይጋጩ እንደነበር ዶክተር ሞጋ ማስታወሳቸው ን ኢሳት ገልጹአል።

በተለይ አቶ በቀለ ገርባ- በቅርቡ “የኢትዮጵያ መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር የእርዳታ ገንዘብን የፖለቲካ መጠቀሚያ አድርጎታል”በማለት ቢቢሲ ይፋ ላደረገው ዘገባ ፦”መረጃ ሰጥታችሁዋል” ተብለው ስለታሰሩት ሰዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸውን ዶክተር ሞጋ የገለጹ ሲሆን በቢቢሲ የምርምራ ዘገባ ፤”ባለፈው ምርጫ ድምፃችሁን ለኢህአዴግ አልሰጣችሁም” የተባሉ ዜጎች እርዳታ ተከልክለው፤ በረሀብ አንጀታቸው ብሶታቸውን ሲያሰሙ መታዬታቸው፤ የብዙዎችን ስሜት መንካቱና የዓለማቀፉ ማህበረሰብ መነጋገሪያ እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን በየቀኑ በርሃብ አለንጋ እንደቅጠል እየረገፉ ባሉበት ሁኔታ ፦”በኢትዮጵያ ድርቅ እንጂ ርሀብ የለም” የሚለው የአረመኔው መለስ አገዛዝ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች፤ 200 ሺህ ብቻ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ቢናገርም፤ የአሜሪካ የእርዳታ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ወደ ስፍራው በመንቀሳቀስ ባደረጉት ቅኝት የተረጅዎች ቁጥር ከ 700 ሺህ እንደሚበልጥ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ላይ አስተያየታቸው የተካተተውን ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምንና ዶክተር መረራ ጉዲናን በአገር ክህደት በመወንጀል በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሀን ሳምንታት የዘለቀ ዘመቻ ከፍቶባቸው መቆየቱ በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።