ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው አለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን እንዲፈታ ጠየቀ
ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ለዘረኛው መለስ ዜናዊ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዳመለከተው ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ርእዮት አለሙና ውብሸት ታየ አስከፊ የእስር ጊዜ እያስተናገዱ ከመሆናቸውም በላይ ርእዮት አለሙ ጤናዋ አሳሳቢ መሆኑን፣ ውብሸት ደግሞ በእስርቤት ውስጥ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገልጿል።
ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ በደብዳቤው ጋዜጣኛ ውብሸት ታየ በእስር ቤት ውስጥ የተፈጸመበት ጥቃትና ድብደባ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ አጥፊዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቋል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታየና ርእዮት አለሙ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምረው በአሸባሪነት ተጠርጥረው በአሰቃቂነቱና በእሥረኞች ላይ በሚፈጸመው ሰቆቃ በአለም እውቅናን ባገኘው ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ወያኔ እተዳደርበታለሁ በሚለው እና ተቃዋሚዎች እንዲያከብሩለት አጥብቆ በሚወተውተው ህገ መንግስት ተብዬ ሠነድ እስረኞች ምንም አይነት ሰብአዊ ክብራቸውን የሚጎዳ ሰቆቃ እንዳይፈጸምባቸው ፤ በቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው እንዲጎበኙ፤ የህክምናና የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ፤ የሚደነግግ ቢሆንም ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሌሎች እስረኞች ላይ ሲፈጽም የቆየው አይነት ሰቆቃ በሁለቱም ጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ መሆኑን ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት ለተባለው የወያኔ ተቋም ፊት ሲቀርቡ እንደተናገሩ ታውቆአል።
የአረቡን አለም አምባገነኖች እያተረማመሰ የሚገኘው አብዮት ከፈነዳ ወዲህ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ከ300 ያላነሱ ኦሮሞዎችን ያለምንም ምክንያት አስሮ በ እስር ላይ እያሰቃየ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን በአገራችን እየከፋ የመጣው የፖለቲካ አፈናና የኑሮ ውድነቱ እያሳከተለ ያለው ችግር የህዝቡን ብሶት እንደ ኢሳተ ጎሞራ ሳይታሰብ አንድ ቀን ሊያፈነዳው ይችላል የሚል ስጋት አገዛዙን እረፍት ነስቶታል።