ህዝባዊ አመጽ እንዳይነሳበት በፍርሃት የተጠመደው የወያኔ አገዛዝ በሰሜን ጎንደር የነዋሪዎችን ቤት ያለአግባብ መፈተሽ ጀመረ

ህዝብን በመሳሪያ ሃይል አንቀጥቅጦ እስከወዲያኛው የመግዛት ዕቅዱ እንደማይሳካ እየተረዳ የመጣው የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን ጎንደር የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በጥብቅ ከመከታተል አልፎ ባልተጠበቀ ሰዓት በሠላማዊ ዜጎች ቤት ዘው ብሎ በመግባት የመሳሪያ ፍትሻ ማካሄድ እንደጀመረ ዘጋቢያችን ከስፍራው በላከልን ዜና ገለጸ።

በአሁኑ ሰዓት በመላው አገሪቱ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት ህዝብ በአገዛዙ ላይ ያለው ጥላቻ ሊደበቅ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተደናገጡት የአገዛዙ ሹመኞች በቀጭን ትዕዛዝ የሚያሽከረክሩዋቸው ፍርድ ቤቶችን በክልሉ ለተጀመረው የነዋሪዎች ቤት ፍተሻ ተባባሪ በማድረግ የተፈላጊ ሰው ሥም ያልተጻፈበት ባዶ የቤት ፍተሻ ማዘዣ ለፖሊስ እንዲሰጡ እንዳደረጉዋቸው ታውቆአል። በዚህም ምክንያት ፖሊሶች ባሰኛቸው ቀንና ሰዓት የፈለጉትን ሰው ሥም በያዙት የፍርድ ቤት ማዘዣ ላይ እየሞሉ ያለምንም በቂ ምክንያት የግለሰቦችን ቤት እየፈተሹ ናቸው ተብሎአል።

ምክንያቱ በግልጽ ባልተነገራቸው ወንጀል ጥርጣሬ ቤታቸው የተፈተሸባቸው ሰዎች ለዘጋቢያችን እንደገለጹት፤ ቁጥራቸው እስከ 3 የሚደርስ ፈታሾች በያንዳንዳቸው ቤት በድንገት ዘው ብለው በመግባት መሳሪያና ሌላም ለመንግሥት ደህንነት የሚያሰጋ ነገር ቤታቸው ውስጥ አለመኖሩን ለማረጋገጥ እንደሚፈልጉ በመናገር በእጃቸው የያዙትን የፍርድቤት ማዘዣ ካሳዩ ቦኋላ ፍተሻ አካሂደው ወደመጡበት ይመለሳሉ።

እንደዘጋቢያችን መረጃ የፍተሻው ኢላማ የሆኑት ሰዎች እንደተቀረው የአገሪቱ ክልሎች በዞኑ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውደነቱ በአገዛዙ ላይ አመጽ ሊያስነሱ ይችላሉ ተብሎ የሚፈሩና የሚጠረጠሩ በአብዛኛው በወጣትነትና በጎልማሳነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገጙትን እንደሆነም ታውቆአል።

ይህ በዚህ እንዳለ በደቡብ ክልል በአገረ ማርያም ወረዳ የሚገኙ ለፋሽስቱ የወያኔ ፓርቲ ፍቅር እንደሌላቸው የሚጠረጠሩ ዜጎች ገዢውን ፓርቲ አትደግፉም በሚል ሰበብ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት እንደተከለከሉ ተዘገበ።

በከተማው ነዋሪ የሆኑና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሀጂ ኡመር ሀሰን የተባሉ ነጋዴ ሰሞኑን የስኳር ንግድ ፈቃድ ማውጣት እንደሚቻል በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ፈቃዱን ለማግኘት ወደ ፈቃድ ሰጪው መሥርያቤት ቢሄዱም “እርስዎ ተቃዋሚዎችን ይደግፋሉ” ተብለው መከልከላቸውን ኢሳት ዘጋቦአል። ከሀጂ ኡመር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስም እየተጠራላቸው ፤ የዚህ ፓርቲ ደጋፊ ስለሆንክ ፈቃድ አንሰጥም ተብሎ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሎአል።

በፍትህ ሚንሰቴር የሚሠሩ ዳኞች የወያኔ አባል ካልሆናችሁ በቀር የጥብቅና ፍቃድ አይሰጣችሁም መባላቸውን መዘገባችን ሲታወቅ ሰሞኑን ደግሞ የኢህአዴግ አባላት አንሆንም በማለታቸው ከስራ የተባረሩትን የመንግሥት ሠራተኞች ኢሳት እንዳነጋገረ ይታወሳል።