ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የጣለውን ግብር ለመሰረዝ መገደዱ ታወቀ፣ ድርጊቱ የአገዛዙን የዘፈቀደ አሰራር የሚያሳይ ነው ተባለ

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ጥሎት የነበረው ከፍተኛ የሆነ ግብር በበርካታ የህብረተሰቡ ክፍሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት እንደቆየ የሚታወቀ ሲሆን፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ተወጣጥሮ የሚገኘው አገዛዝ የዘፈቀደ ውሳኔውን እንደገና እንዲቀለብስ መገደዱን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ሪፖርት ገለጸ።

እንደዘጋቢያችን ሪፖርት በቅርቡ ብሄራዊ ባንክ፤ ንግዱ ማህበረሰብና፤ የወያኔ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ባደረጉት ስብሰባ ነጋዴዎች የአገዛዙ የግብር አጣጣል ስርአት በህይወታቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጸዋ። ይሁን እንጂ የዘረኛው አገዛዝ ሆድ አደር ካድሬ ሬዲዋን ሃሰን ነጋዴው ግብር የመክፈል ፍላጎት የለውም፣ አሁን በግብር አሰባሰብ ላይ የሚነሱት ቅሬታዎች ነጋዴዎች ገቢያቸውንና ወጪያቸውን በትክክል ለማሳወቅ ፍላጎት ካለማያሳየት የመጣ ነው፣ አገሪቱ የተያያዘችው የህዳሴ ጉዞም ግቡን ሊመታ የሚችለው ነጋዴው ግብር ሲከፍል ብቻ ነው በማለት ለመከራከር መሞከሩ ታውቁአል።

ይሁን እንጂ በስብሰባው የተካፈሉት የንግዱ ማህበረሰብ አካላት አገዛዙ ከገቢው ጋር ያልተመጣጠነ ፕሮጀክቶችን በመዝርጋቱ የሚፈጠርበትን የገንዘብ እጥረት ለመሸፈን ሲል ያልተመጣጠነ ግብር ይጥላል፣ ያለምንም ጥናት የሚጥለው ይሄው ግብር የንግዱን እንቅስቃሴ እያቀዘቀዘው ይገኛል በማለት አበክረው መናገራቸውን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጹአል። በዚሁ ስብሰባ ከነጋዴዎች ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ አገዛዙ ነጋዴዎች አምና ይከፍሉት የነበረውን ግብር አምነው እንዲከፍሉ ከዚያ ውጭ የተጠየቁትን እንዳይከፍሉ ሲል ትእዛዝ ማስተላለፉ ታውቁአል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ የዘረኛው አገዛዝ ባለሙአል ያልተጠበቀ እርምጃ ያስገረማቸው ነጋዴዎች፣ ከዚህ ቀደም በግድ ክፈሉ ለተባሉት ግብር ማስያዣ የከፈሉት ገንዘብ እንዲመለስላቸውም መጠየቃቸው ታውቁአል።

ዘጋቢያችን የዚህን የግብር እዳ ስረዛ አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡት የጠየቃቸው አንድ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ነጋዴ እንደተናገሩት፣ እኔ በህይወቴ እንደ ወያኔ ያለ ቀልደኛ አገዛዝ ገጥሞኝ አያውቅም፣ ውሳኔ ሲወስን በዘፈቀደ መሆኑ ሲያስገርመኝ፣ ይህኑ ውሳኔውን ሲሰርዝ ደግሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በግዴለሽነት ነው ብለዋል። ቀጥለውም ባለፈው ጊዜ በምግብ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ድንገተኛ ውሳኔ አስተላለፈ፣ ይህ አልሳካ እንዳለ ሲረዳው ያለምንም ጥናት ውሳኔውን ሰረዘ:; እዚህ ላይ የሚገርመውና የሚያስደንቀው ነገር፣ ያኔ በምግብ ሸቀጦች ዋጋ ከጨመረ በሁአላ ውሳኔውን ሲሰርዝም ሆነ አሁንም በግብር ላይ ተመሳሳይ ድርጊትን ሲፈጽም ሁሉንም ነገር ያደረግሁት በጥናት ነው ማለቱ ነው በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል::