በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ተባብሰዋል፣ የተፈጠሩት ችግሮች የዘረኛውን አገዛዝ ውድቀት ያፋጥናሉ ተባለ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ ሁኔታ ላይ መድረሱና ለረጂም አመታት በትምህርት ላይ የቆዩ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ስራ አጥነት እጂግ መስፋፋት የዘረኛውን አገዛዝ ውድቀት ሊያፋጥኑት እንደሚችሉ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ በያዝነው አመት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን አጠናቀዋል ተብለው የተመረቁ ወጣቶች ቁጥር እጅግ በጣም ብዙና በመቶ ሺሆች የሚቆጠር መሆኑን የገለጸ ሲሆን ቀደም ብሎ ትምህርታቸውን ከተለያዩ ተቁዋማት ያጠናቀቁ ወጣቶች ለአራትና አምስት አመታት ለስራ አጥነት በተዳረጉበት ሃገር፣ብሎም የስራ እድል ባልተፈጠረበት ሁኔታ ይህን ያህል ወጣት ተመራቂ መጨመሩ በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስና አመጽን ሊያስነሳ እንደሚችል ተመራቂ ተማሪዎች አስተያየታቸውን የሰጡት መሆኑን ገልጻኡአል።

ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው አመት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ተማሪዎች ውስጥ የእንግሊዝኛ ቁአንቁአ ትምህርት የ2003 ዓም ምሩቅ የሆነች ስሙዋ እንዳይጠቀስ የጠየቀች ወጣት ወደፊት ተመራቂዎች ስለሚኖራቸው እጣ ፈንታ አስተያየት እንዲሰጣት ላቀረበላት ጥያቄ በሰጠቺው አስተያየት፣ “ቀደም ብለን ትምህርታችንን የጀመርን ምናልባት ፊደል በመቁጠራችን የተሻለ እድል ይኖረናል በሚል እምነት ነበር፣ ይሁን እንጂ አሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ላለፉት አራትና አምስት አመታት ስራ አጥ ሆነው የተቀመጡ ወጣት ተመራቂዎችን ባይናችን እያየን በመሆኑና የወደፊቱም የሃገሪቱዋ ወጣቶች እጣ ፈንታ ወደ ባሰ አዘቅት እያመራ በመሆኑ አንዱ እየተራበ፣ ሌላው በጥጋብ ሊኖር የሚችልበት ምክንያት የለምና ሃገሪቱ ያልታሰበ ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትቺል” ግምቱአን ገልጻለች።

በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪዉን የያዘና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ወጣት በሰጠው አስተያየት ከስራ አጥነቱ በተጨማሪ ባሁኑ ሰአት በሃገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነት የሞት የሽረት ቁዋፍ ላይ እንድንቀመጥ ስላደረገን፣ አይናችን እያየ እየተራብን ከመሞታችን በፊት፣ ችግሮች ሊወገዱ ለሚችሉበትና አገዛዙን ከጫንቃችን ላይ አሽቀንጥረን ለመጣል በሚደረገው ትግል የግንባር ቀደምትነቱን ድርሻ እንይዛለን በማለት ተናግሩዋል።

ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው ማን ነው ትላላችሁ በማለት ዘጋቢያችን ላቀረበው ጥያቄ ሁለቱም ወጣት ተመራቂዎች በሰጡት ምላሽ ተመራቂዎች ሥራ አጥተው ለረጅም ጊዜ የመንከራተታቸው ዋና መንሴና ተጠያቂውም አንድና አንድ ነው ይሄውም የወያኔው አገዛዝ ነው፣ ፣ ያሉብንን ችግሮች እንኩዋን ተነጋግረን መፍትሄ ለመፈለግ እንዳንረባረብ፣ ሃሳባችንን መግለጽ እንዳንችል ተቃውሞም እንዳናሰማ በተለያዩ ውስብስብ መንገዶች አፍኖን ይገኛል በማለት ገልጸዋል፣ ፣ በመጨረሻም፣ ይህ አገዛዝ በወጣት ኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍና በደል እንዲያበቃ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።