ትናንሽ ነውጦች ታላቁን ማዕበል ያስነሳሉ!!!
የሰደድ እሳትም ሆነ የውቅያኖስ ማዕበል በቀላሉ አይነሳም፤ ከተነሳ ደግሞ በቀላሉ አይቆምም። ህዝብ ተባብሮ በተነሳ ጊዜም ደን ውስጥ እንደተነሳ ሰደድ እሳት ወይም እንደ ውቅያኖስ ማዕበል ነው፤ ከባድ ጉልበትና ኃይል አለው። በመንገዱ ላይ ያሉትን ሁሉ አቃጥሎም ሆነ ደረማምሶ ማለፍ ይችላል። ዛሬ ሊቢያ ውስጥ እየሆነ ያለውም ይህንን የሰደድ እሳት ወይም የውቅያኖስ ማዕበል የመሰለን ህዝባዊ ንቅናቄ ነው።
ኮሎኔል ጋዳፊ ለተራዘመ ጦርነት ራሱን ሲያዘጋጅ እንደነበረ የቆፈራቸው ዋሻዎች እና በየቦታው ያከማቻቸው የጦር መሣሪያዎች ዓይነትና ብዛት ማረጋገጫዎች ናቸው። ሆኖም ግን ህዝባዊው ማዕበሉ እነዚህም ደረማምሶ ማለፍ ችሏል። ተመሳሳይ ክስተቶችን በሶሪያና በየመንም እናይ ይሆናል።
አገራችን ኢትዮጵያም ይህ ህዝባዊ ማዕበል እንደሚጎበኛት ይጠበቃል። ህዝባዊ ማዕበሎች አንዴ ከተቀሰቀሱ በኋላ የሚቀላቀላቸው ብዙ ነው። ከውስጥም ከውጭም የማዕበሉ አካል ለመሆን የሚፈልገው ሰው ቁጥሩ ብዙ ነው። ትልቁ ችግር ያለው ማዕበሉን ማስነሳት ላይ ነው።
ሁሌም ህዝባዊ ማዕበል የሚቀሰቀሰው በጥቂት ሰዎች ነው። እነዚህ በታሪክ ውስጥ አሻራቸው በወፍራው ታትሞ እንዲቀር የታደሉ ጥቂቶች ከየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ሊወጡ ይችላሉ። የቱኒዚያው መሃመድ ቦዛዚ በታሪክ ስማቸው በጀግንነት እንዲነሳ ከታደሉት ወጣቶች አንዱ ነው። ሆኖም ግን እሱ የጫረውን እሳት ያቀጣጠሉ ሌሎች የአገሩ ዜጎች ባይኖሩ ኖሮ መላውን ሰሜን አፍሪካን ነፃ ያወጣው አብዮትን በአሁኑ ጊዜ ለማየት ባልተቻለ ነበር።
የአረብ ፀደይ የሚል ስያሜ የተሰጠውና በህዝብ ቀጥተኛ መሪነትና ተሳትፎ የተካሄደው የነፃነትና የማኅበራዊ ፍትህ አብዮት መዳረሻው የሁሉንም ዜጎች ክብርና መብት ማስከበር ቢሆንም በግንባር ቀደምትነት በወጣቶች የተመራና የተቀነባበረ ነው። ይህ አብዮት ለወጣቱ የወደፊት ህይወት ደንታ በሌላቸው ያረጁና ያፈጁ አምባገነን አገዛዞችና መሪዎች ላይ የገነፈለ ቁጣ ነው። በየሃገሩ የሚታየው ግብግብ ወደፊት በሚወለድ አዲስ የዴሞክራሲና የተስፋ ሥርዓት እና ባረጀና አንድ እግሩን ከመቃብር ጉድጓድ ከዶለ አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር በመሆኑ ወጣቱን በስፋትና በሁሉም ዘረፍ ማሳተፉ የግድ ነው።
ከሰሃራ በታች ባሉ አምባገነንት በደደረባቸው ሃገሮችም ተመሳሳይ አብዮት መፈንዳቱ አይቀርም። የአፍሪካው ፀደይ እንደ አረብ አቻው ሁሉ የወጣቱ አሻራ እንደሚያርፍበት አያጠራጥርም። መፃዒ እድሉን ለመወሰን፤ ጽልመቱን ለመግፈፍ፤ እልሁም፣ ቁርጥኛነቱም፣ እውቀቱም፣ ብልሃቱም በወጣቱ እጅ ውስጥ እንደሆነ በቱኒዚያ፣ በግብጽ፣ በሊብያና በሶሪያ እያየነው ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ወጣት ለዚህ ኃላፊነት ብቁ ነው ብሎ ያምናል። በመለስ ዜናዊ አገዛዝ የወጣቱን ያህል የተበደለ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ክፍል ማግኘት ይከብዳል።
መለስና እኩይ ቡድኑ የኢትዮጵያን ሃብት ተከፋፍለው ስለጨረሱት ለወጣቱ የተረፈው እዳ ብቻ ሆኗል። ለም መሬታችን ለባዕዳን በመሸጡ የገጠሩ ወጣት የሚያርሰው ቁራሽ መሬት እያጣ መሰደድ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ወጣት ገበሬዎች ደቡብ አፍሪካ ድረስ ለመሰደድ ከቀያቸው ነቅለው የተነሱት በመለስ የአገዛዝ ዘመን ብቻ ነው። በገጠርም በከተማም የሚገኙ ወጣት ሴቶች ወደ አረብ አገራት ለመሄድ በረሃ ማቋረጥ፤ ባህርን በታንኳ መሻገር የጀመሩት በዚሁ የግፍ አገዛዝ ዘመን ነው።
ዘመናዊ ትምህርት ያገኘው ወጣትም በተማረው ትምህርት አገሩንና ወገኑን የማገልገል ህልሙ ተጨናግፎ ስደት እጣ ፈንታው የሆነው በመለስ የአገዛዝ ዘመን ነው። ለከፍተኛ ትምህርት እድል በህዝብ የተጠሉት የወያኔ ድርጅቶች አባል መሆን በመመዘኛነት የቀረበው በመለስ አገዛዝ ነው።
ኢትዮጵያዊ ወጣት ክብሩንና ነፃነቱን ለገንዘብና ለተሻሉ የሥራና የትምህርት እድሎች ሲል አሳልፎ እንዲሰጥ ሲደለል ቆይቷል። በዚህም ምክንያት አንዳንዱ ወጣት በወያኔ ሎሌነት ተሰልፎ የማያምንበት እየሰበከና እያደረገ ከህሊናው ጋር እንዲጣላ ተደርጓል።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ወጣቱን በዘር በማደራጀት እርስ በርሱ እንዲጣላ መደረጉ ነው። በየጊዜው በሚፈለፈሉ “የወጣቶች ፎረሞች” አማካይነት የወጣቱ ወኔ ተሰልቦ አድርባይነትን እንዲለማመድ ተደርጓል። የጎንደሩ ለባሌ፤ የሸዋው ለአሩሲ፤ የትግራዩ ለባህርዳር፤ የሃረሩ ለጅጅጋው ባዕድ እንዲሆን፤ በጥርጣሬም እንዲጠባበቅ፤ በሰበብ አስባቡም እንዲቆራቆስ ተደርጓል።
ይህ ሁሉ ግን እየተቀየረ ነው። ወጣቱ “እኔ ምን አቅም አለኝ” የሚልበት ወቅት አልፏል። የወያኔ የአባልነት ደብተራቸውን የቀደዱ፤ “በፓርቲ ስብሰባ ላይ አንገኝም” ብለው መልዕክት የላኩ፤ የወያኔን “ድጎማ” አንቀበልም ያሉ፤ “ከዚህ በላይ ምን ይመጣብናል” በሚል ድፍረት የልባቸውን የተናገሩ ጀግኖች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እነዚህ ተናጠል የሚመስሉ እርምጃዎች እየተጠራቀሙ ህዝባዊውን ማዕበል ያስነሱታል።
ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ “የኔ ተሳትፎ ኢምንት ነው” ሳይል በተቻለው ሁሉ ትግሉን የሚያግዝበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብሎ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።
የእያንዳንዳችንን ትናንሽ ተሳትፎዎችንም እያቀናጀን በማጎልበት ወደህዝባዊ ማዕበልነት ማድረስ የሁላችንም ሥራ ነው። ትናንሽ ነውጦች ሲጠራቀሙ ታላቁን ማዕበል ያስነሳሉ ብሎ ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!