የአፍሪቃ የመሬት ቅርምት የዉሃ እጥረት ሊያስከትል ስለሚችል ገደብ ሊደረግበት እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጠ
በአፍሪካ የሚደረገዉ የመሬት ቅርምት በተለይም በምግብ እጥረትና በረሃብ በሚጎዱት የአፍሪካ አገሮች ላይ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል አገሮች ለዉጭ ከበርቴዎች የሚሰጡት መሬት አስፈላጊዉ ገደብ ሊደረግበት እንደሚገባ በአንድ የባለሙያ አስተያየት ተገለፀ።
በአባይ ዉሃ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ በሆነችዉ በግብፅ ህልዉና ላይ ሊያስከትል የሚችለዉ አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያና ሱዳን የመሳሰሉት አገሮች በረዢም አመታት ዉል ለዉጭ ድርጅቶች የሚሰጧቸዉ መሬቶች ለአካባቢዉ ሰላምና መረጋጋት አደጋ ሊኖረዉ እንደሚችል በተጨማሪ ተጠቁሟል።
በዚህም ምክንያት በ1960ዎቹ በህንድና በፓኪስታን መካከል በተፈረመዉ የኢንደስ የዉሃ ስምምነት ላይ የአለም ባንክ እንደረዳዉ ሁሉ፤ በመሬት ቅርምቱ ስምምነት ላይም አለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት መኖሩ አስፈላጊ ነው ተብሎአል።
የምግብ ዋጋ ጭማሪ ፡ ድርቅና ረሃብ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ በደረሱበት ወቅት አበባ እና ሌሎች ለነዳጅ ዉጤት የሚዉሉ እፅዋትና ሰብሎችን ለማብቀል ለዉጭ ከበርቴዎች በሚሰጡ መሬቶች ላይ የሚደርሰዉ የከርሰ ምድር ዉሃ እጥረት ለአገሮቹ ለራሳቸዉ ከፍተኛ ችግር ሊሆን እንደሚችል በተለያየ ጊዜ በባለሙያዎች በመገለጽ ላይ እንዳለ ይታወቃል።