የኢትዮጵያ የብር ኖት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ ነው፣ የባለ 200 ብር ኖት ለማተም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታወቀ
በዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ የጉልበት አገዛዝ ስር የወደቀቺው ኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ መሄዱ በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በግብይት ላይ ከሚገኙ የብር ኖቶች ከፍተኛ ነው ከሚባለው ከባለመቶ ብር ኖት በተጨማሪ፣ የ200 ብር ኖት ገበያ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የውስጥ ምንጮቻችንን በመጥቀስ ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ።
እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት፣ የብር ምንዛሪ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መውረድ በገበያ ላይ ከፍተኛ የሆነ ግሽበትን ከማስከተሉ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ የሚባለው የአንድ መቶ ብር ኖት ዋጋ እያጣ በመምጣቱ ዘረኛው አገዛዝ የ200 መቶ ብር ኖት ለማተም ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ታውቁአል።
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያዊያንን ኑሮና የኑሮ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጨለመና የሰቆቃ ኑሮን እንዲገፉም እያደረገ ከመሆኑም በላይ አሁን ያለው የብር ኖት የመግዛት አቅም እጅግ እየወደቀ በመምጣቱ ባለ 200 ብር ኖት ገበያ ውስጥ ማስገባትን እንደምፍትሄ አድርጎ ማቅረቡ ታውቁአል።
የባለ 200 ብር ኖት ገንዘብ ህትመት በሃገሪቱ እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበት አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው አንድ የኢኮኖሚክስ ምሁር በሰጡን አስተያየት ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው ገደብ የለሽ የገንዘብ ህትመት ቁጥጥር እስካልተደረገበት ድረስ አሁንም ወደባሰ አዘቅት ከማምራት ውጪ መፍትሄ ሊሆን አይችልም:: ይህን እያደረገ ያለው የወያኔ አገዛዝ ደግሞ እንዲህ አይነቱ የሃገር ውድመት ምንም ስሜት የሚሰጣቸው ባለመሆኑ ምን ማድረግ እንደሚገባን ማሰብና መወሰን ያለብን እኛ እንጂ እሱ ሊሆን አይገባውም ብለዋል::
በቅርቡ የዓለም ባንክና ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ገንዘብ ማተሙን እንዲያቆም ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ በይፋ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።