ሊቢያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ለኛም ትምህርት ሆናችሁ!!!!

የሊቢያ ህዝብ ለአርባ ሁለት ዓመታት የተጫነበትን የጋዳፊን አገዛዝ ከጫንቃው ለማውረድ ተቃርቧል። የነፃነት ታጋዮች የአገሪቱን ዋና ከተማ – ትሪፓሊ – አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥረዋል።

ኮሎኔል ጋዳፊ ደጋግሞ “ሊቢያ ቱኒዝያ ወይም ግብጽ አይደለችም” እያለ ሲፎክር ነበር። እውነታው ግን ሊቢያ ከቱኒዚያም ሆነ ግብጽ የባሰች ሆና መገኘቷ ነው። ጋዳፊ ከቤን ዓሊም ወይም ከሙባረክ የከፋ አምባገነን እንደነበረ ሁሉ እሱን ለማስወገድ እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነትም እጅግ ከፍ ያለ ሆነ። የጋዳፊ አምባገነንነት መክፋት እሱን ለማስወገድ የሚጠይቀው መስዋዕትን አበዛ እንጂ እሱ ራሱ ሶስተኛው ባለተራ ከመሆን አላዳነውም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከሊቢያ ልምድ የሚቀስማቸው በርካታ ቁምነገሮች ቢኖሩም ለጊዜው ሁለት ነጥቦች ላይ ብቻ እናትኩር።

1. ሰላማዊ ትግል ሰላማዊ ሆኖ ላይዘልቅ ይችላል

ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሰላማዊ ትግል ተመራጭነት የማያጠያይቅ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ሰላማዊ ትግል ስለተፈለገ ብቻ የሚገኝ ስልት አይደለም። ሰላማዊ ትግልን በሰላማዊነቱ እንዲዘልቅ አምባገነኑ ኃይል በመጠኑም ቢሆን ቁጥብ የሆነ፤ ይሉኝታ ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል። ጋዳፊ የጦር ሠራዊቱ አዛዥነትን በልጆቹና ቅርብ ዘመዶቹ አሲዞ፤ ነፃነት ናፋቂውን ህዝብ በአይጥና ውሻ መስሎ “ጨፍጭፏቸው” ብሎ ሲያዝ ህዝብ ራሱን ለመከላከል መሞከሩ ተገቢና ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው። ከሊቢያ የምንማረው አንድ ሃቅ ህዝብን በጅምላ ከመጨፍጨፍ የማይመለስ ሥርዓትን ለመለወጥ የተነሳ ሰላማዊ ትግል ወደ ራስ መከላከል ብሎም ወደማጥቃት ቢሸጋገር ተቀባይነት ያለው ተግባር መሆኑን ነው።

2. በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰለጠነ ጦርን መገዳደር የሚችል ህዝባዊ ሠራዊት መገንባት ይቻላል

ውትድርና ሰፊ ጊዜና ሥልጠና የሚሻ ጉዳይ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ቢሆንም ቆርጦ የተነሳ ህዝብ ራሱን በአጭር ጊዜ ማደራጀት የሚችል መሆኑ ከሊቢያ የምንማረው ሁለተኛው ቁም ነገር ነው። ከዛሬ ከስድስት ወራት በፊት መሣሪያ ይዘው የማያውቁ ሃኪሞች፣ ጠበቃዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች …. ዛሬ የጦር ቡድን መሪዎች ሆነው ለማየት ችለናል። አምባገነኖች የቱን ያህል የሰለጠነና የታጠቀ የጦር ኃይል ቢኖራቸውም እንኳን ህዝብ ለነፃነቱና ለመብቱ አምርሮ ሲነሳ፤ የሰለጠነው ወታደር ባልሰለጠነ ህዝባዊ ኃይል የሚሸነፍበት ሁኔታ መኖሩ በዓይኖቻችን አይተናል።

መማር የሚችል ከሆነ መለስ ዜናዊም ከሊቢያ ሊቀስማቸው የሚገቡ በርካታ ቁም ነገሮች አሉ። መለስ ዜናዊ በተለይም የሚከተሉትን ነጥቦች በአንክሮ እንዲያጤን እንመክራለን።

1. “ኢትዮጵያ ቱኒዝያ፣ ግብጽ ወይም ሊቢያ አይደለችም” ማለት አያዋጣም

ሙባረክን ጨምሮ ጀምሮ ተመሳሳይ ነገር ያላለ አምባገነን የለም። “እኔ የተለየሁ ነኝ፤ እዚያ የነደደው እኔ ዘንድ አይደርስም” ከማለት በጊዜ መፍትሄ መሻት ብልህነት ነው። መፍትሄው ደግሞ ቀላልና ግልጽ ነው – ሥልጣንን በጊዜ ለህዝብ ማስረከብ! ነው።

2. በሠራዊት መተማመን አያዋጣም

የቱኒዝያና የግብጽ የጦር ሠራዊቶች ለአደራጇቸው አምባነገነኖች አልሆኑም። በጋዳፊ ልጆቹና እጅግ ቅርብ በሆኑ የቤተሰቡ አባላት የሚመራው የሊቢያ የጦር ሠራዊትም ከመሪዎቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ የጦሩ አባላት አብረዋቸው አልቆሙም። በዚህም ምክንያት ነው ነብሰ-ገዳዮችን ከሌሎች አገራት ቀጥረው በህዝባቸው ላይ ማሰማራት ያስፈለጋቸው። ሆኖም ግን ይህ በቅጥረኖች የተሞላው ሠራዊት በስድስት ወራት ውስጥ በተደራጀ የነፃነት አርበኛ ጽኑ ትግል ተፈታ። መለስም ትከሻቸው ባበጠ ጄኔራሎቹ ላይ ስላለው እምነት ደጋግሞ እንዲያስብበት እንመክራለን። በቁርጥ ቀን እነሱም አብረውት ላይቆሙ ይችላሉ፤ ቢቆሙም ተከታዮች ከሌላቸው እጅግም የሚፈይዱት ነገር አይኖርም። አዲስ የተገዙት ሁለት መቶ ታንኮችም የሚፈይዱት ነገር የለም። ታንኮች ከተሜን የማስፈራራት አቅማቸው በ97 አልቋል።

3. ሥልጣን ላለመልቀቅ ማንገራገር መጨረሻን ያበላሻል

ቤን ዓሊ የልጅ ልጆቹ በልተው የማይጨርሱትን ሃብት ዘርፎ በጊዜ እብስ አለ። ሙባረክ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ሲችል በማን አለብኝነት በማንገራገሩ እነሆ በወሳንሳ ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ይገኛል። የጋዳፊ መጨረሻ ደግሞ ከሙባረክ እጅግ የከፋ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። መለስ ሆይ፤ መዘጋጂያ ጊዜህ አሁን ነው!!! የጋዳፊ መልክተኛ በመጨረሻው ሰዓት ያቀረበውን “የእንድራደር” ጥያቄን ያደመጠው ጆሮ አለመኖሩን ልብ በል።

4. ዓለም ተቀይሯል

የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ ህዝባዊ አብዮቶች የዓለምን አስተሳሰብ በእጅጉ ቀይረውታል። የገዛ ራሳቸውን ህዝብ የሚጨፈጭፉ አምባገነኖችን ዓለም በዝምታ አያያቸውም ። መለስ ሆይ ልብ በል!!! የእለት ጉርስህን ሳይቀር የምታገኘው ከእነርሱ ነውና ፊታቸውን ሲያዞሩብህ አንተ እንደማትኖር፤ ለአንተ የኔቶን ጦር ማዝመት እንደማያስፈልግ አስተውል!!!

ውድ ሊቢያውያን ትግላችሁ ሙሉ በሙሉ ዳር እንዳልደረሰ እናውቃለን። ሆኖም እስካሁን ባየነው ኮርተንባችኋል። ሊቢያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራችሁ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈበት ሥርዓት ትገነባላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

እኛ ኢትዮጵያዊን ከናንተ ብዙ እንማራለን።

መለስ ዜናዊም ከሊቢያ ህዝባዊ አብዮት ትምህርት ወስዶ ሥልጣኑን ለህዝብ እንዲያስረክብ እንመክራለን። አለበዚያ ግን አወዳደቁ ከሙባረክም ሆነ ከጋዳፊ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለማስጠንቀቅ እንወዳለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!