ሙሰኛው የቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ አባ ገ/ኢየሱስ መኰንን ሢመተ ጵጵስናን በገንዘብ ለመግዛት መንቀሳቀሳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል
admin
Tagged with addis ababa, Amharic, business, economy, election, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship

- ‹‹የሰባት ወይራ ሆቴልን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዳይወስድብን ለመለመን›› በሚል በደብሩ አስተዳደር ያስወሰኑትን ግማሽ ሚልዮን ብር፣ ሢመተ ጵጵስናውን ይቃወማሉ የሚባሉ አባቶችን የማግባባት አቅማቸውን እንደሚያጠናክሩበት ጠቁመዋል፡፡
- ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በተፃራሪ በሥልጣን ላይ የቆዩትና በአስተዳዳሪው ውሳኔ እስከ 7000 ብር በወር የሚከፈላቸው አብዛኞቹ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት እና የጽ/ቤቱ ሠራተኞች፣ በአስተዳዳሪው የግማሽ ሚልዮን ብር ጥያቄ እንዲስማሙ በ‹ጥቅማቸው› መገደዳቸው ታውቋል፡፡ ከአስተዳደሩ ሠራተኞች የሚበዙት ከገቢያቸው በላይ ከደብሩ በሚያካብቱት ሕገ ወጥ ጥቅም በከተማው ሦስትና አራት ፎቅ ያላቸው ሕንጻዎችንና መኖርያ ቤቶች ግንባታ በማካሄድ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
- አስተዳዳሪው አባ ገ/ኢየሱስ÷ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘውንና ደብሩ የይዞታ መብቱን በሕግ ለማረጋገጥ የተቃረበብትን የሰባት ወይራ ሆቴል ባለቤትነት፣ ባለፈው ዓመት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በድብቅ በጻፉት ደብዳቤ የተረከቡኝ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡ ድርጊቱ፣ የደብሩ አለቃ ሢመተ ጵጵስናን በስምዖናዊ መንገድ ለማግኘት የሚያግባቡበት ገጸ በረከት አካል እንደኾነ ታምኖበታል፡፡
- በ1965 ዓ.ም ከልዕልት ኂሩት ደስታ (የደጃዝማች ደስታ ዳምጠው ልጅ) ለቅ/ላሊበላ ደብር በስጦታ የተበረከተው የሰባት ወይራ ሆቴል በሙሰኛውና ዐምባገነኑ አስተዳዳሪ ፍቅረ ሢመት የተነሣ ሕጋዊ ባለቤትነቱ በድብቅ ተላልፎ መሰጠቱ ሳይበቃ፣ ‹‹ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዳይወስድብን መለመኛ/መያዣ›› በሚል የደብሩ አስተዳደር ብር 500,000 እንዲያጸድቅ በአለቃው መገደዱ በከተማው ምእመናን ዘንድ ከፍተኛ ቊጣ ቀስቅሷል፤ ሥር የሰደደውና ሃይ ባይ ያጣው የአለቃው ዘራፊነትና ዐምባገነንት በቁጣ ለተሞሉትና ለተመረሩት ምእመናን ጥቃት እንዳይዳርጋቸውም ተሰግቷል፡፡
- ምእመናኑ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ወደ ወልድያ ተጉዘው ለሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቤቱታቸውን ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል፡፡
- ላለፉት ስምንት ዓመታት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የውቅር አብያተ መቅደሱን ሀብት ያለቦታው በማፍለስ፣ ክብካቤ እንዳይደረግላቸው በመከላከል፣ በአብያተ መቅደሱ ዙሪያ የሚገኙና በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች ኾነ ብለው በቃጠሎ አደጋ እንዲጠፉ በማድረግ፣ የደብሩን ድጎማ እንዲያገኙ በሀ/ስብከቱ ለታዘዛላቸው ቤተ ጉባኤያት ደቀ መዛሙርት ድጋፍ በመንፈግና በማዳከም፣ የአብያተ መቅደሱን አገልጋዮች ሐሰተኛ ሰነድ እየፈጠሩ ከሥራ በማፈናቀልና በማንገላታት ከባድ ክሥ የቀረበባቸውን አስተዳዳሪ ከቦታቸው ለማስወገድ ወቅቱ አኹን እንደኾነ ታምኖበታል፡፡
