ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ፖሊሲዎቹን ዕርስ በርሳቸው ማጣረሱን ቀጥሏል፣ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የግል የጤና ኮሌጆች አዳዲስ ተማሪዎች እንዳይመዘግቡ ትእዛዝ ማስተላለፉ ተሰማ
የግል ትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ሌት ከቀን እየሰራሁ ነው በማለት ሲመጻደቅ የነበረው የወያኔ አገዛዝ ፣ ከሚቀለው ዓመት ጀምሮ የግል የጤና ኮሌጆች አዳዲስ ተማሪዎች እንዳይመዘግቡ ትእዛዝ ማስተላለፉን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ የውስጥ ምንጮቹን በመጥቀስ ገለጸ። የግል ትምህርት ተቋማት ባለቤቶችም ይህን የዘረኛውን ወያኔ አዲስ ትእዛዝ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ፖሊሲዎቹን ዕርስ በርሳቸው እያጣረሳቸው ለመሆኑ መረጃ ነው በማለት ተናገሩ።
የዘረኛው አገዛዝ የውስጥ ምንጮች ለዘጋቢያችን እንደገለጹት ይህ በቅርቡ በይፋ ለህዝብ ይገለጻል የተባለው አዋጅ ከዚህ በኋላ የግል ተቋማት በጤና ትምህርት መሰማራት እንደማይችሉ የሚገልጽ ሲሆን፣ ከሚቀጥለው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል። ይህ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ከተደረገ በጤናው ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያሰለጥኑ የግል ኮሌጆች በሙሉ እንዲዘጉ እንደሚያደርጋቸው ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአንድ የግል ጤና ተቋም መምህር ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት አገዛዙ ኮሌጆቹ የመዘገቧቸውንና በስልጠና ላይ የሚገኙትን ብቻ እንዲያስመርቁና ፡ አዲስ ምዝገባ ግን እንዳያካሂዱ ማስጠንቀቁ ታውቋል።
ቀደም ብሎ ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በተመሳሳይ መልኩ፡ የህግ ትምህርት የሚሰጡ የግል ኮሎጆች ስልጠናውን መስጠት እንዲያቆሙ አግዶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በሁዋላ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በደረሰብት ጫና ውሳኔውን መልሶ ለማንሳት መገደዱ ይታወሳል። በአሁኑ ጊዜ በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ከተመረቁ በሁዋላ በፍትሀዊ መንገድ ተወዳድረው ስራ ለማግኘት ባለመቻላቸው የድርጅት አባላት እንዲሆኑ እንደሚገደዱ ሂውማን ራይተስ ወችን የመሳሰሉት ድርጅቶች በተደጋጋሚ የዘገቡት ጉዳይ ነው።
የዘረኛውን የወያኔ አገዛዝ አዲስ ርምጃ አስመልክቶ ለዘጋቢያችን አስተያየት የሰጡት መምህር እንደገለጹት ወያኔ የተለያዩ ውጥረቶችና ፈተናዎች ሲገጥሙት ሁሌም እንደሚያደርገው ምንም ያልታሰበበትና እቅድም የሌለበት ርምጃ ይወስዳል፣ ርምጃውን ከወሰደ በኋላ፣ ያስባል፣ የወሰደው ርምጃ ስህተት ሆኖ ሲያገኘው እንኳን ይቅርታ ጠይቆ ከማስተካከል ይልቅ ርምጃዬ ትክክል ነበር ብሎ ይከራከራል፣ እናም በጤናው ዘርፍ አሁን የወሰደው ርምጃም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደሚገጥመው ምንም ጥርጥር የለኝም በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።