በዘረኛው አገዛዝ በጥናት ላይ ያልተመረኮዘ የዘመቻ ስራ፣ የትግራይ አርሶ አደሮች እጅግ መማረራቸው ታወቀ

በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ የውሃ ማቆር በሚል ከበርካታ አመታት ጀምሮ መተግበር አለባችሁ ብሎ በግዳጅ የጀመረው ዘመቻ ውጤታማ አለመሆኑና አርሶ አደሮችም በዚህ የግዳጅ ዘመቻ ክፉኛ መማረራቸውን የጀርመን ራዲዮ ጣቢያ ዶቺቨለ ዘገበ።

እንደ ዶቺቨለ ዘገባ ገበሬዎቹ በሰጡት አስተያየት ከላይ የወረደ መመሪያ ነው ተብሎ የተጫነባቸው የውሐ ማቆር ሥራ ጉልበት ከማባከን በስተቀር አንድም ጥቅም እንዳላስገኘላቸው መናገራቸውና፣ ይልቁንም ለዚሁ ሥራ ተብሎ የታደለውን ላስቲክ ለታሰበለት የውሐ ማቆሪያ ሳይሆን ለቤት ክዳንና ሌሎች ግልጋሎቶች ማዋላቸውን አስታውቀዋል ብሉአል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሥራው ውጤታማ ያልሆነበት ምክንያት በቂ ጥናት ተደርጎ ባለመጀመሩ መሆኑን በወቅቱ በዚህ ስራ ላይ የተካፈለ አንድ የእርሻ ልማት ሰራተኛ መናገሩ ታውቁአል።

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ፣ ከምእራባዊያን ሃገራት የሚያገኘውን ድጋፍ ላለማጣት “አድርግ” የተባለውን ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ጥናት እንደወረደ በኢትዮጵያዊያን ላይ ሲጭን እንደቆየ በስፋት የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህ የውሃ ማቆር ስራ ዘመቻ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች በግዳጅ እንዲሰራበት ተወስኖ ምንም ውጤት ሳያመጣ የቀረና በርካታ ሚሊየን ዶላር በአየር ላይ እንዲበተን ያደረገም እንደነበር ፣በዚህ የውሃ ማቆር ስራ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያ ከሰጡን አስተያየት ለመረዳት ተችሉአል።