በአፍሪካ እየተካሄደ ያለው የመሬት ቅርምት የአገሩን ህዝብ ከመሬቱ በማፈናቀል በክፍለ-አህጉሩ የተከሰተውን ረሀብ ማባባሱ ተገለፀ

ተቀማጭነቱ ዋሽንግተን የሆነው ወርልድዎች ኢንስቲትዩት፤ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት በመካከለኛውና ከሳህራ በታች ባሉ በ25 የአፍሪካ አገራት የሚገኙ ገበሬዎችና የገጠር ነዋሪዎች፤ያለጥናት በተደረገ የመሬት መቀራመት ይዞታቸውን አጥተው ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል አለ።

ወርልድ ዎች ኢንስቲትዩት እንደገለጸው በዚህ መልኩ እየተከሰተ ላለው ችግር በዋነኝነት ሳዑዲ አረቢያንና ቻይናን ጨምሮ የመካከለኛውና የሩቅ ምስራቅ አገራትን ኮንኗል።

በሌላም በኩል ጉዳዩን አስመልክቶ ሬውተርስ እንደዘገበው፤ መሬት መቀራመቱን በዘመቻ መልክ የተያያዙት እነዚህ አገሮች፤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2006 እስከ 2009 ባለው የሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ፤ ከ 15 እስከ 20 ሚሊየን ሄክታር የሚሆን መሬት መከራየታቸውን ጥናቱ ጠቁሟል።

“ወደ አፍሪካ በማቅናት ነዋሪዎችን እያፈናቀሉ- በወደቀ ዋጋ መሬት እየተከራዩ ናቸው” ያላቸውን አገሮች ”ራስ ወዳዶች” በማለት የወቀሰው ወርልድ ዎች፤ መሬትን ለውጭ አገር ባለሀብቶች በርካሽ ዋጋ ለማከራየት- ተወላጅ ገበሬዎቻቸውን ከይዞታቸው የሚያፈናቅሉ መንግስታትም፤ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሣስቧል።

መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣በመንግስታት ወኪሎችና በተመራማሪዎች በተከናወነውና 17 ወራት በፈጀው በዚህ ጥናት፤ በ25 አገሮች የሚኖሩ የ 350 ገበሬ ማህበራት አስተያዬት መካተቱ ተገልጿል።

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በሚሊየኖች የሚቆጠር ለምና ሰፋፊ እርሻ ለሃብታም ሃገራት ባለሃብቶች በርካሽ ዋጋ ሲቸበችብ መቆየቱ፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ፣ ለርሃብና ለችግርም እንደተዳረጉ መዘገባችን ይታወሳል::