ለወራት ያለአስተዳዳሪ የቆየው የካርቱም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በችግር ላይ ነው
- አስተዳደሩና ማኅበረሰቡ የመረጣቸው አስተዳዳሪ ምደባ እንዲወሰንለት ጠይቋል
- ሊቀ ጳጳሱ ለምደባ ያቀረቧቸው ስድስት ሠራተኞች ማንነት እያጠያየቀ ነው
- ቋሚ ሲኖዶስ በአህጉረ ስብከቱ አስተዳደር ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን እየመረመረ ነው
- ለደቡብ አፍሪካ የቅዱስ ያሬድ ገዳም ከአ/አ አድባራት የተሰበሰበውና በሊቀ ጳጳሱ የግል አካውንት ተልኮ የነበረው አራት ሚልዮን ብር ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተጠቁሟል
ላለፉት ሦስት ወራት ያለአስተዳዳሪ የቆየው በምድረ ሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጵጵስና የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ እየተበደለ መኾኑን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፈው ደብዳቤ አስታወቀ፤ በደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና በኦርቶዶክሳዊው ማኅበረሰብ ሙሉ ስምምነት በቀድሞው አስተዳዳሪ ቦታ እንዲተኩ የተመረጡት አባት ምደባ እንዲጸድቅለትም ጠየቀ፡፡
የደብሩ አስተዳደር በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በግልባጭ ለመላው አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የላከው ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ ከሐምሌ ፳/፳፻፩ ዓ.ም ጀምሮ ደብሩን ለአራት ዓመታት በእልቅና ያገለገሉት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ይርሳው ከሐምሌ ወር ፳፻፭ ዓ.ም ከቦታው ተቀይረው ወደ ኢትዮጵያ በመመለሳቸው ደብሩን ከውጭ አካላት ጋራ የሚያገናኙት አገልግሎቶቹ እየተበደሉ ይገኛሉ፡፡
በምድረ ሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን በተለይ ከሱዳን የሃይማኖት ሚኒስቴር፣ ፍርድ ቤት፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲና መሰል አካላት ጋራ የሚከናወኑ የማኅበረሰቡን ጉዳዮች ምትክ አስተዳዳሪ ባለመመደቡ ለማስፈጸም መቸገሩን የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት አስታውቆ፣ በቀድሞው አለቃ ፈንታ ‹‹ማኅበረሰቡ የተቀበላቸውና ለአገልግሎቱ ብቁ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸው›› አባት ምደባ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ እልባት እንዲሰጠው የፓትርያርኩን መልካም ፈቃድ ጠይቋል፡፡
ምደባቸው በፓትርያርኩ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲያገኝ የደብሩ አስተዳደር የጠየቀላቸው አባ ገብረ ኢየሱስ አየለ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት የካርቱም ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን በግብዝና በማገልገል ላይ ያሉ መኾናቸው ተገልጧል፡፡
በምድረ ሱዳን የተበተነውን ስደተኛ ኢትዮጵያዊ በማሰባሰብና ለንስሐ የሚያበቃ ትምህርተ ወንጌል በማስተማር፣ ከዐጸደ ሕፃናት ጀምሮ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ (እስከ ስምንተኛ ክፍል) ዘመናዊ ትምህርት የሚሰጥበትን ት/ቤት ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ በማሳደግ፣ በገዳሪፍ የጻድቁ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርኩ ታውቆ በማእከላዊነት እንዲተዳደር ምእመኑን በማስተማርና በማሳመን በሰበካ ጉባኤውና በቀድሞው አስተዳዳሪ ትብብር የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት አስጠብቆና አጠናክሮ ለማስቀጥል ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ከደብሩ ጋራ ያላቸው የሥራ ግንኙነት የታወከው የመላው አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ በካርቱም ደ/ሰ/መድኃኔዓለም የጸሐፊነት መደብ ጨምሮ በኬንያና በጅቡቲ አብያተ ክርስቲያን የስድስት አገልጋዮች ቅጥር እንዲጸድቅላቸው ለመንበረ ፓትርያርኩ ጥያቄ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ ምደባቸው እንዲጸድቅ ከተጠየቀላቸው ስድስት አገልጋዮች መካከል፣ ሊቀ ጳጳሱ ቀድሞ በግል መፍቀዳቸው በሚፈጽሙት የአዲስ አገልጋዮች ቅጥር ሰበብ የግል ጥቅም ይሰበስቡበታል የሚባለውን የአዲስ አበባ ኔትወርክ ያንቀሳቅሳሉ የሚባሉት ቀሲስ ግሩም ታዬ እንደሚገኙበትና በካርቱም ደ/ሰ/መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በጸሐፊነት ሊያስመድቧቸው ማቀዳቸው ተነግሯል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ ቀሲስ ግሩምን በጸሐፊነት ለመመደብ ያላቸውን ፍላጎት ቀደም ብሎ በኢንፎርሜሽን ደረጃ ሲከታተለው ቆይቷል የተባለው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምደባቸውን በጽኑ እንደሚቃወም ባለፈው ዓመት ሐምሌ አጋማሽ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፈው ደብዳቤ ማሳሰቡ ተዘግቧል፡፡ ‹‹የካህኑን ሕይወትና ሥነ ምግባር ጠንቅቄ ዐውቃለኹ›› ያለው የደብሩ ጽ/ቤት፣ ሰበካ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ መክሮ ያስተላለፈውን ውሳኔ ባስታወቀበት በዚያ ደብዳቤው፣ ቀሲስ ግሩም ታዬ ‹‹ከቦታውና ከኅብረተሰቡ ጋራ ተመጣጥነው መሄድ የማይችሉ ናቸው›› ሲል ነው የሊቀ ጳጳሱን የምደባ ዕቅድ ውድቅ ያደረገው፡፡ ከዚህ በመነሣት በኬንያና በጅቡቲ አብያተ ክርስቲያን ምደባቸው እንዲጸድቅ ሊቀ ጳጳሱ ዝርዝራቸውን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ያቀረቧቸው የተቀሩት አገልጋዮች ማንነት በሚገባ ሊጤን እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡
በጥቅመኝነት፣ ወገንተኝነትና ብቃት ማነስ ክፉኛ ከሚተቸው የሊቀ ጳጳሱ አስተዳደርና ከማጥመቅና ሌሎች ኢክርስቲያናዊ ተግባራት ጋራ ተያይዘው ሲጎርፉ የቆዩ አቤቱታዎችንና መረጃዎችን ማጠናቀሩ የተገለጸው የፓትርያርኩ ጽ/ቤት፣ ጉዳዩን በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በኩል ለቋሚ ሲኖዶስ በአጀንዳነት ማቅረቡ ተገልጧል፡፡
በአጀንዳው÷ የሊቀ ጳጳሱ አስተዳደራዊ ድክመት በአህጉረ ስብከቱ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አንድነት ከማስጠበቅ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ከማስፋፋትና ከማጠናከር አንጻር የደቀነው ስጋት በቀዳሚነት እንደሚመረመር ይጠበቃል፡፡ መንበረ ጵጵስናው በሚገኘበት ደቡብ አፍሪካ ለተቋቋመው የቅዱስ ያሬድ ገዳም ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተሰብስቦ በሊቀ ጳጳሱ የግል አካውንት መላኩ የተገለጸው አራት ሚልዮን ብር አጠቃቀም ደግሞ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ተመልክቷል፡፡