ኢትዮጵያ በተማረ ሀይል ፍልሰት ከዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ላይ መቀመጧ ኦን ላይን ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ጥናት አስታወቀ

በጥናቱ ፤እጅግ የተባባሰ የምሁራን ፍልሰት ከሚታይባቸው 10 አገሮች በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አራት የተቀመጡት፤ ከአፍሪካ ሲሆን፤ እነሱም ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪቃ ናቸው። ከአምስተኛ እስከ አስረኛ ባለው ደረጃ እንደ ቅደም ተከተላቸው የተቀመጡት ደግሞ ኢራን፣ቻይና፣ሜክሲኮ፣ጃማይካ፣ ማሌዥያና እንግሊዝ ናቸው።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተማረ ሀይል አስደንጋጭ በሆነ ደረጃ የሚፈልስባት የመጀመሪያዋ አገር ኢትዮጵያ መሆኗን የጠቀሰው ይህ የኦንላይን ዩኒቨርሲቲ ጥናት፤ በተለይም በህክምናው መስክ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ምሁራን፣መሀንዲሶችና ሳይንቲስቶች ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች መፍለሳቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ምሁራን ስደትን ለመምረጥ ተገደዱት በዋነኝነት በተለያዩ ፖለቲካዊ ጫናዎች በመገፋታቸው ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል። በጥናቱ የተጠቀሰው ሌላው የፍልሰት ምክንያት ደግሞ፤ ምሁራኑ በሌሎች አገሮች በሚገኙ አማራጭ የስራ መስኮች መሳባቸው ነው ተብሎአል።

ጉዳዩን አስመልክቶ በቅርቡ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባዘጋጁት ብሄራዊ ሲምፖዚየም ላይ በቀረበ አንድ ጥናት ይፋ የሆነው ቁጥር እጅግ አስደንጋጭ መሆኑን ያወሳው ኦን ላይን ዩኒቨርሲቲ፤ ኢትዮጵያ፤ባለፉት አስር ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ከሰለጠኑት ምሁራኗ መካከል- 75 በመቶ የሚሆኑትን በፍልሰት እንዳጣች መረጋገጡን ገልጿል።

ይህም በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ከፍ ያለ እንቅፋት እንደሚፈጥር የጠቀሰው ይህ ጥናት፤ እጅግ የሰለጠኑትን ዜጎቹን በአግባቡ መያዝ ያልቻለው የወያኔው አገዛዝ በተማረ ሰው ሃይል ዕጥረት የተከፈተውን ክፍተት ለማሟላት ባልተለመደና ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁሟል።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአገባቡ ያልጨረሱ እንዲያውም ከ7ኛ ና 8ኛ* ክፍል ያልዘለሉ እንደ ባለቤቱ አዘብ መስፍን አይነቶቹን አባላቶችና ካድሬዎችን ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ብሎ በከፈተው የካድሬዎች ማሰልጠኛ እያስገባ በድግሪና በዲፕሎማ እያስመረቀ እንደሚያወጣ በትላልቅ የሙያና የኃላፊነት ቦታዎችም እየመደባቸው አገሪቱን ወደ ጨለማ እየወሰዳት መሆኑ ይታወቃል:: ከዚሁ ጎን ለጎን፤ በተለያዩ የውጪ አገሮች በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ስም በሚገኙት የትምህርት ዕድሎች እየተላኩ ከሚማሩት መካከል፤ 98 በመቶ የሚሆኑት የገዥው ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች እንደሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

ከሁለት ዓመት በፊት በኔዘርላንድስ -ዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ የመማር ዕድል አግኝተው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙት 69 ተማሪዎች መካከል፤ 67ቱ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ፤ በቤልጂዬም አገር ባሉ ሁለት ታላላቅ ዩኒቨርሲትዎች ማለትም በሉቨን ካቶሊክ ዩኑቨርሲት እና በጌንት ዩኒቨርስቲ የሚላኩ አብዛኛዎቹ ተማሪዎችም ይህንን እፍትሃዊ ያለሆነ የዘር መድልዎ የሚያመለክት እንደሆነ እንደሆኑ መዘገቡ አይዘነጋም።