ሱዳን ድንበሯን አቋርጠው ወደ ግዛቷ ከገቡት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ወደ 500 የሚጠጉትን በሃይል ወደ አገር ቤት መመለሷ ተገለጸ

የዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በአገራችን ውስጥ ባሰፈነው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተስፋ ቆረጠው የተሻለ ህይወት ፍለጋ አገራቸውን ጥለው በሱዳን በኩል ከተሰደዱ በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣት ስደተኞች መካከል ቁጥራቸው ወደ 500 የሚጠጉትን የሱዳን ፖሊስ አሳልፎ ለወያኔ አገዛዝ እንዳስረከበ አንድ የመተማ ነዋሪ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ አስታወቁ።

የወያኔው አገዛዝ ጠረፍ አቋርጠው ሱዳን የሚደርሱ ወጣቶች በብሶት ምክንያት አገራቸውን ትተው በመሄዳቸው የተነሳ ከውጪ ሆነው እየተደራጁ ነው በማለት የሚከሳቸውን አማጽያን እንዳይቀላቀሉ ከፍተኛ ስጋት አድሮበታል ያሉት እኒህ የመረጃ ምንጫችን፤ በመተማ ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ ዜጎች ከመሃል አገር በሁመራና መተማ በኩል ወደ ውጪ እየፈለሱ ያሉትን ወጣቶች ለማስቆም እንዲተባበር መወትወት ከጀመረ ቆይቶአል ብሎአል።

በአገራቸው ተስፋ ቆርጠውና ህይወት ጨልሞባቸው ወደውጪ እየጎረፉ ያሉ ያገሪቱ ዜጎች ከወጣትነት እስከ ጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ሲታወቅ፤ የሴት እህቶቻችን ቁጥር ከወንዶቹ እየበለጠ መምጣቱ፤ በተለይ ደግሞ በሱዳንና ሌሎች የአረብ አገሮች በቤት ሰራተኝነት ለመቀጠር ከወንዶቹ እኩል በረሃውን አቋርጠው ሱዳን የሚገቡ ሴቶች ልጆች በመንገድ ላይ አስገድዶ የመደፈር ችግር ሁሉ እንደሚገጥማቸው ለማወቅ ተችሎአል።

ከመሃል አገር፤ ከጎንደር፤ ከጎጃም እና ከትግራይ ወደ ሱዳን እየፈለሱ ያሉ እነኚህ በአገራቸው ተስፋ ያጡ ወገኖቻችን ድንበር ለማቋረጥ ከአራት አስከ ስምንት ሺህ የኢትዮጵያ ብር ለህገወጥ ደላሎች እንደሚከፍሉ ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የሱዳን ፖሊሲ አስገድዶ ወደ አገራቸው ከመለሳቸው ከነዚህ 500 ያህል ወጣት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃና የኮለጅ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ቦኋላ ሥራ የማግኘት ዕድል ሳያገኙ ቀርተው ለወላጅ ቤተሰብ ሸክም ከመሆን ብለው ስደት የመረጡ እንደሆነ ታውቆአል።

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ ፖሊሲ በቀፈቀፈው የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ምክንያት የወደፊት ተስፋቸው ጨልሞ አገራቸውን በየብስ፤ በምድርና በባህር አያቋረጡ የሚሰደዱ ስደተኞች ቁጥር ባለፈው 10 አመት እጅግ እንደጨመረ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ሪፖርት ያመለክታል።