አረመኔው የወያኔ አገዛዝ ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ የቴሌ ሠራተኞችን መድሃኒት እንዳያገኙ ከለከለ

ከኢትዮ ቴሌኮም መሥርያ ቤት ሕግና ሥርዓት ሳይጠበቅ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከሥራ ገበታቸው ላይ ከተባረሩት መካከል፣ ከኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሠራተኞች መድኃኒት እንዳይወስዱ መከልከላቸውን በማስረዳት ቦርዱ እንዲታደጋቸው መጠየቃቸውን ለአረመኔው አገዛዝ ቅርበት እንዳለው የሚነገርለት ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገበ፡፡

ከኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖሩት ሠራተኞች ለኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ “ፋታ የማይሰጥ ማመልከቻ አለን” ይታይልን በማለት ሊያስረዱ ሲሞክሩ፣ ቦርዱ “በቃለ መሀላ ያስገባችሁት ማመልከቻ ስላለ ከዚህ የተለየ ምን ትናገራላችሁ?” የሚል ዘለፋ የተሞላበት ምላሽ የተሰጣቸው መሆኑንም ይሀው ዘገባ አመልክቱአል። እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር ከሚኖሩት ሠራተኞች አንዷ ለቦርዱ እንደገለጹት፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን መድሎዎና መገለል በመቋቋም “ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ” ብለው ራሳቸውን አጋልጠው ሕዝብን ሲያስተምሩ ቆይተዋል ካለ በሁአላ ሐምሌ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ክሊኒክ መድኃኒት ለመውሰድ ሲሄዱ አይገቡም ተብለው መከልከላቸውን መናገራቸውን ገልጹአል፡፡

መድኃኒቱን አንድ ቀን ሳይወስዱ ካደሩ ሲዲፎራቸው እንደሚጨምር የገለጹት ሠራተኛዋ፣ ነፍሰጡሮች መኖራቸውንና ወደ ሌላ ክሊኒክ ወይም ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ከመሥርያ ቤቱ ክሊኒክ ሪፈር ማጻፍ እንዳለባቸው እየታወቀ፣ ከመሥርያ ቤቱ ጋር ያላቸው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ “አትገቡም” መባላቸው ለበቀል የሚያነሳሳ መሆኑን በመግለጽ ቦርዱ በአስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውም በዚሁ ዘገባ ላይ ተመልክቱአል፡፡

ከኤችአይቪ(ኤድስ ጋር የሚኖሩት ሠራተኞች ችግራቸው ታይቶ ደመወዛቸው እየተከፈላቸው በሒደት ሥራውን እንዲያቆሙ አለመደረጉ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ፣ ሕይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ለበርካታ ዓመታት ከሠሩበት መሥርያ ቤት ወጥተው መጣላቸው ሳያንስ፣ ዓለም ሳይቀር የሚረባረብበትንና ስርጭቱን ለመግታት ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበትን ኤችአይቪ/ኤድስን ትኩረት መንፈግ አግባብ ባለመሆኑ፣ ቦርዱ በአስቸኳይ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው መለመናቸው ታውቁአል፡፡ “እንኳን ደመወዝ ታግዶብን ተከፍሎንም መኖር አቅቶናል፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ያለምግብ መውሰድ አይቻልም፡፡ ከባድ መድኃኒት ነው፡፡ ልጆች አሉን፣ የቤት ኪራይ እንከፍላለን፤” ያሉት ሠራተኛዋ፣ ከብሔራዊ ኤችአይቪ/ኤድስ ሴክሬታሪያትና ከሌሎችም ቦታዎች የተሰጡዋቸው ንብረቶች መኖራቸው በክሊኒኩ እንዲጠቀሙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል::

በዘረኛውና አምባገነኑ አገዛዝ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን አማካኝነት በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየተዘረፈበት ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ችግር በኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በርካታ ታማሚዎች ተገቢ የሆነ ርዳታ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ህይወታቸው በየ እለቱ እየተቀተፈ እንደሚገኝ በስፋት ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።