በኢትዮጵያ ሚሊየኖች ይራባሉ፣ ነገር ግን የውጪ ሃገራት ኢንቨስተሮች በሺሆች የሚቆጠር ቶን እህል ኤክስፖርት ያደርጋሉ ተባለ

በርካታ ሚሊየኖች በርሃብ አለንጋ እየተገረፉባት በምትገኘው ኢትዮጵያ የውጪ ሃገራት ኢንቨስተሮች በርካታ ሺህ ቶን የጥራጥሬ ምግብ እህልን እያመረቱ ለትርፍ ወደ ውጪ ሃገራት ኤክስፖርት እያደረጉ መሆኑ የሚያሳዝን እውነታ ነው በማለት ስዊስ ኢንፎ በመባል የሚታወቅ የዜና አውታር ገለጸ። እንደ ስዊስ ኢንፎ ዘገባ በሃገሪቱ ምእራባዊ ክፍል የህንድ ኢንቨስተሮች ገና እድሚያቸው ለስራ ያልደረሱ ህጻናትን ሳይቀር በጉልበት እያሰሩና እየረገጡ ትርፍ ያግበሰብሳሉ ብሉአል።

በህንድ ኢንቨስተሮች በተያዘው የሸንኮራ አገዳ ተክል ማሳ በመገኘት የታዘበውን የዘገበው የስዊስ ኢንፎ ጋዜጠኛ እንደገለጸው የአየሩ ሙቀት 40 ዲጊ ሴንቲግሬድ በደረሰበት በዚሁ የእርሻ ማሳ የስምንት አመቱ ለጋ ህጻን በጉልበቱ ተንበርክኮ አረም ያርማል፣ ከሁአላው ደግሞ የህንዱ ባለሃብት ቆሞ ህጻኑ እያንዳንዱአን አረም ሳያስቀር እያረመ መሆኑን በመጎማለል ይቆጣጠራል ካለ ቦኋላ፣ የሚገርመው ነገር ለዚህ ህጻን የጉልበት ስራ በቀን የሚከፈለው ባለሃብቱ ለአረም መድሃኒት ከሚያወጣው ውጪ በጣም ያነሰና ዜሮ ነጥብ ስምንት ሶስት ዩሮ የሆነ ዝቅተኛ ገንዘብ ነው በማለት በሃዘን ገላጹአል።

በኢትዮጵዩአ ከ12 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በርሃብ አለንጋ እየተገረፉ እንደሆነ ራሱ ዘረኛው አገዛዝ በይፋ የገለጸ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከነኝህ ረሃብተኞች ውስጥ ወደ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊየን የሚሆኑት በአስሽቸኳይ ጊዜ ርዳታ የሚገኙ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢው የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት እየታየ ስላለው ረሃብ ለበርካታ ወራት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፡ በቂ ምርት አለመኖርና በአካባቢው ያለው የእርስ በርስ ግጭት የምግብ እጥረትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ፣ አገሮቹም ሆኑ ወዳጆቻቸው እንዲያስቡበት ጥሪ እንዳደረገና በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ለተከሰተው ከፍተኛ የሆነ ረሃብና ለሚጠፋው የሰው ልጅ ሕይወት ተጠያቂዎቹ የየሃገራቱ መንግስታት ናቸው የሚል አይነት መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ነው፡፡

የወያኔ መሪዎች በ1977 በአገራችን ሰሜን ክፍል ተከስቶ የነበረውና በአገሪቱ ላይ አሉታዊ ገጽታውን ጥሎ ያለፈው አስከፊ ድርቅና ረሃብ ዳግም ላይከሰት ተቆጣጥረነዋል በማለት በባዶ ፕሮፖጋንዳ ሲያደነቁሩን ከኖሩ ቦኋላ በታሪካችን ረሃብ ታይቶበት ወደማይታወቅበት ደቡብ የአገራችን ክፍል ተዛምቶ ቢያንስ ላለፉት 10 አመታት በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ዜጎች ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅትን ጠቅሶ ዘ ጋዜት እንደዘገበው ደግሞ፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የሟቾች ቁጥር በአሥር ሺዎች መቆጠር ጀምሯል፡፡

ይህ በንዲህ እያለ ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ያሉ የርሃብተኞችን ቁጥር እየደበቀ መሆኑ እየተዘገበ ሲሆን፣ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም የዓለም አቀፍ ሚዲያም ሆነ የርዳታ ሰጪ ድርጂቶች እንዳይገቡ መከልከሉ ታውቆአል። በወያኔ የልማት ፖሊሲ አርሶ አደሩ ትርፍ ምርት እያመረተ ሚሊየነር ሆኖአል በማለት የሚደሰኩረው የአረመኔው መለስ ዜናዊና ግብረአብሮቹ ቡድን እራሱ በፈጠረው የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተከሰተውን ረሃብ በተፈጥሮ ድርቅ በማሳበብ ላይ እንደሚገኝ፤ ገመናውንም ለመደበቅ ሲል ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች መንግሥት አልባ በሆነቺው ሶማሊያ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ለማድረግ ሌት ከቀን እየሰራ እንደሆነ ታውቆአል።

ዘረኛው አገዛዝ ህዝብ እንዲህ በረሃብ እንደቅጠል እየረገፈ በሚገኝበት ወቅት በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር በማውጣት የጦር ታንኮችን መግዛቱን መዘገባችን ይታወሳል።