በኢትዮጵያ በስፋት እየታየ ያለው የትምህርት ጥራት ደረጃ ዝቅተኝነት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጎላ መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ

ዩ ኤስ አይ ዲ በመባል የሚታወቀው የ አሜሪካ የልማት ተራድኦ ባወጣው ጥናታዊ ጽሁፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ማንበብ በሚገባቸው ሰአት በብቃትና በጥራት እንደማያነቡ አጋለጠ።

ዩኤስ አይ ዲ ባወጣው በዚሁ ጥናቱ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙት 8 ክልሎች በሚገኙት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 80 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት ማንበብ በሚገባቸው እድሜ ማንበብ እንደማይችሉ ታውቋል። እንደ ጥናታዊ ጽሁፉ ሪፖርት ይህ አሀዝ ወደ ሲዳማ ክልል በሚመጣበት ጊዜ 100 በመቶ እንደሚደርስ ጥናቱ አሳይቷል።

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ለብሄር ብሄረሰቦች መብቶች ጠበቃ ነኝ በማለት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ አድርጊያለሁ ቢልም፣ በሲዳማ ከ70 በመቶ፣ በትግራይ ከ57 በመቶና በቤንሻንጉል ጉሙዝ 54 በመቶ የሚሆኑ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች የሃገራቸውን ታሪኮች አንብበው መረዳት ፈጽሞ እንደማይቺሉ አጋልጧል።

ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ ሰፊ ጥናት ያካሄደው ዩ ኤስ ኤድ በክልሎች ያለው የመጽሀፍ አቅርቦት በሚመለከት ያካሄደው ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው አቅርቦቱ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው በእጅጉ እንደሚለያይ ያመለክታል። በዚህም መሰረት የመጻህፍት አቅርቦት በክልል ደረጃ ሲታይ በሶማሊያ 42 በመቶ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ 59 በመቶ የሚሆኑት የሚያነቡት መጽሀፍት ያላቸው ሲሆን፣ በትግራይ ግን 95 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች የሚይነቡት መጽሀፍት አላቸው። ይሄው ጥናት አያይዞ በአማራ 70 በመቶ በሲዳማ ደግሞ 61 በመቶ ተማሪዎች የራሳቸው መጽሀፍት አላቸው ብሏል።

ዩ ኤስ ኤይድ ያካሄደውን ጥናት ሲያጠቃልል፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ተማሪዎች ለሁለትና ሶስት አመታት ትምህርት ቢከታተሉም አብዛኞቹ መሀይም እንደሆኑ ናቸው ካለ በኋላ የተማሪዎችን የማንበብ ብቃት ለማሳደግ ተጨማሪ መጽሀፍት እንዲሰራጩ፣ ውስብስብ የሆነው የቋንቋ ችግር እንዲፈታ፣ የመምህራን ብቃት እንዲያድግ ጥረት እንዲደረግና ትምህርት ንባብ ከአንደኛና ከሁለተኛ ክፍል እንዲጀመር ሀሳብ አቅርቧል።

በኢትዮጵያ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመምህራን ብቃት ማነስ ችግርና ለትምህርት አስፈላጊ በሆኑ ቁሳቁሶች እጥረት ምክንያት ተመራቂዎች በየተማሩባቸው የትምህርት መስኮች ምንም አይነት በቂ እውቀትን እንደማይጨብጡና ለስራም ብቃት እንደማይኖራቸው ራሳቸው ተመራቂዎች መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ለምእራባዊያን የተጋነነ አሃዝን ሪፖርት በማድረግ በጤናና በትምህርት መስክ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች አሳክቻለሁ በማለት ለማደናገር ቢሞክርም ፣ በሁሉም ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አገሪቷ በጥራትም ሆነ በአቅርቦት ገና ብዙ ያልተሠሩ ነገሮች እንዳሉ ይታወቃል።