በግንቦት7፣ በኦነግና በኦብነግ መካከል ተቀራርቦ የመስራት ጅመር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ሲሉ ዶ/ር ብርሁኑ ነጋ ገለጹ
የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ድርጅት ኢሳት ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን በኒዘርላንድስ ዋና ከተማ አምስተርዳም ላይ አዘጋጅቶት በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ ስብሰባ ላይ በተጋባዥ እንግዳነት ንግግር ያደረጉት የግንቦት 7 ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶር ብርሃኑ ነጋ፤ ድርጅታችን ግንቦት 7 ከኦሮሞ ነጻነት ግንባርና ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ጋር ተቀራርቦ በጋራ ለመሥራት የጀመረው ጥረት የኢትዮጵያን አንድነት አስተማማኝ መሠረት ላይ ለማቆም የሚረዳ እንደሆነ ስለሚያምን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አስታወቁ።
ዶ/ር ብርሀኑ በዚህ ንግግራቸው ከእነዚህ ሁለቱ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ መስራትን የሚቃወሙ የአንድነት ሀይሎች ያዋጣል የሚሉትን መንገድ መከተል እንዳለባቸው ገልጸው፣ በድርጅቶች መካከል እርስ በርስ ሽኩቻ ሊኖር እንደማይገባውና ድርጅቶች ጉልበታቸውን፣ ሀይላቸውንና ጊዜያቸውን አገራቸውን በማዳን፣ አንባገነኑን ስርአት በማስወገድ ላይ ብቻ እንዲያውሉ መክረዋል።
ግንቦት7 የኢትዮጵያን አንድነት በይፋ እንደማይቀበሉ ከገለጡ ሐይሎች ጋር ከመስራቱ በፊት የኢትዮጵያን አንድነት ከሚቀበሉ ሀይሎች ጋር በቅድሚያ መስራት ነበረበት በማለት አስተያየታቸውን ለሰጡ አንድ ተሳታፊ የኦሮሞ ተወላጅና የኦነግ አባል መሆናቸውን በመግለጽ ምላሽ የሰጡ ሌላው ተሳታፊ “ኦሮሞ በዲሞክራሲና በህግ የምትመራ አገር ከተመሰረተች የሚገነጠልበት ምንም ምክንያት የለም፣ ኦሮሞ ግንድ ነው፣ ኢትዮጵያን ያለ ኦሮሞ ኦሮሞን ያለ ኢትዮጵያ ማሰብ አይቻለም በማለት” ከማንም በላይ ለአንድነት ተቆርቋሪ ነን ለሚሉ ወገኖቻችን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢሳት ባዘጋጀው በዚህ የገቢ ማሰባሰብ ስብሰባ ላይ ከተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን፤ ግንቦት7 ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ በጋራ ለመታገል የሚያደርገውን ጥረት በማድነቅ፤ ከኦነግና ኦብነግ ጋር ለመቀራረብ የሚደረገው ጥረት ዛሬ እንዳልተጀመረና የአንድነት ሀይሎች ነን የሚሉ የተለያዩ ድርጅቶች ለረጂም ጊዜ ሲደክሙበት የቆዩ መሆኑን፤ አሁን ግንቦት7 ከእንዚህ ሁለቱ ደርጅቶች ጋር ለመስራት በመወሰኑ ቀደም ሲል ተመሳሳይ ሙከራ ያካሂዱ የነበሩ ለምን የተቃውሞ አቧራ ለማስነሳት እንደፈለጉ እንደማይገባቸው የተናገሩ ይገኙበታል።
በመጨረሻም ኢሳት በጠራው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የኢሳት የሆላንድ የድጋፍ አስተባበሪ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ወንዶሰን ገብረህይወት ኢትዮጵያውያን ኢሳትን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበው ይህን የተሳካ ዝግጅት ለማዘጋጀት እገዛ ላደረጉት ሁሉ በኢሳት ስም ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ የገቢ ማሰባሰቢያው ዝግጅት አንደተካሄደ ከኢሳት ያገኘነው ዘገባ ገልጾአል።