መለስ ዜናዊና የቀደሙት ነገስታት

በ1808 ዓ.ም እንግሊዞች በአጼ ዮሃንስ እየተመሩ መቅደላ ድረስ ገስግሰው ደርሰው ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ጦርነት ገጥመው ረቷቸው።አጼ ቴዎድሮስም ለባእድ እጄን አልሰጥም ብለው በገዛ ሽጉጣቸው ራሳቸውን ገደሉ። ይህም ጀግነንት ሆኖ ተቆጥሮላቸው እስከ ዛሬ ባለው ትውልድ ዘንድ ሲዘከር ይኖራል።

አጼ ቴዎድሮስ በገዛ ሽጉጣቸው ራሳቸውን የገደሉ ግዜ በወቅቱ ከነበሩ ባለ ቅኔዎች አንዱ የሚከተለውን ቅኔ ተቀኘላቸው፤

በመቅደላ አፋፍ ላይ ጩኸት በረከተ፤

የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ።

አያችሁት ወይ ያንበሳውን ሞት፤

በሰው እጅ መሞትን ነውር አድርጎት።

በወቅቱ የንጉሱ ጀግንነት ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ታውቆ ስለነበረ የተደረሰላቸው ግሩም ቅኔ ነው።

የጦርነቱ ምክንያት ንጉሱ እጃቸውን ይዘው ያሰሯቸው የእንግሊዝ ዜጎች ነበሩ። እንግሊዞች ዙሪያቸውን ከበው ባስጨነቋቸው ግዜ ካጠገባቸው ከቆሙት አንዱ “ጃንሆይ እንግዲህ መሞታችን ካልቀረ የዚህ ጦርነት ምክንያት የሆኑትን እነዚህን የታሰሩትን እንግሊዞች መዥመሪያ ገድለን እኛም ሄደን እንሙት” ሲል አማከራቸው።

አጼ ቴዎድሮስ ግን “ያገሬን ሕዝብ አንድ ለማድረግ እኔ ያጉላላሁት አንሶ እነዚህን ገድየ ሕዝቤን በባእድ እጅ እንዲጠቃ አላደርግም” ብለው መለሱለት። ይሄም ሃሳባቸው እስከ ዛሬ ሲያስመሰግናቸው ይኖራል። ጀግና እንዲህ ነው። በጥላቻ መካከል ፍቅርን፤ በጭካኔ ውስጥ ርህራሄን ማሳየት የጀግና ሰው ተግባሩ ነው።

ከጀግኖች መካከል የማይመደበው መለስ ዜናዊ ቢሆን ኑሮ ሊያደርግ የሚችለውን ሁላችንም እናውቃለን። ድህረ ምርጫ 97 ድምጻችን ይከበር ብለው አደባባይ የወጡትን ንጹሃን ለሥልጣኔ ስጋቶች ናቸው በሚል ከደቂቅ እስከ ሊቅ ማስፈጀቱን አናስታውሳለን። እንባቸውን እየዘሩ ባለቤቴን አትውሰዱብኝ እያሉ ሲለምኑ የነበሩትን ወ|ሮ እቴነሽን ልጆቻቸው ፊት በጥይት ግንባራቸውን ተደብድበው እንዲሞቱ ቀጭን ትእዛዝ ሰጥቶ የንጹሃን ደም ማፈሰሱን አንዘነጋውም። የአቤል ደም ከምድር ወደ ሰማይ እንደሚጮህ ሁሉ የ10 አመቱ ህጻን ያሲን ደም እስከ ዛሬ ካዲስ አበባ ምድር ወደ ላይ ወደ ሰማይ እየጮኽ መሆኑንም እያዳመጥን ነው። እንደመለስ አይነቱ ወይ ከጀግንነት አለያም ከፈረሃ እግዜአብሔር አንዱንም ያልተቸረ ው ስልጣን ላይ እስካቆየው ድረስ በወገንና በአገር ላይ ምንም የከፋ መከራ ቢመጣ የማይፈጽመው ዓይነት ወንጀል እንደሌለ በስልጣን ዘመኑ ያየነው ነው።

የዛሬው ሃተታችን የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ መዘከር ወይም መለስ ዜናዊን ከእነርሱ ጋር ማወዳደር አይደለም። ይልቁንም መለስ ዜናዊ በቅርቡ በዚያ ልቅ አንደበቱ በራሳቸው ዘመን ስለአገራቸው ወቅቱ የፈቀደላቸውን መልካም ነገር ሠርተው ስለአለፉት የተናገረውን ነውር ህዝቡ ልብ እንዲለው ለማሳሰብ እንጂ።

በመጀምሪያ ደረጃ መለስ ዜናዊ ቀጥሮ ሰው የሚያደርግ ስብእናቸውን ገፍፎ ለሚያዋርዳቸው ጋዜጠኞች እናዝናለን። በመለስ ዜናዊ ዘመን በመንግስት በጀት ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኞች እንደ ህጻን ልጅ ጥያቄ ተዘጋጅቶ እየተሰጣቸው እንዲጠይቁ ይደረጋል እንጂ ህዝቡ ማወቅ ያለበትን ወይም ደግሞ ጋዜጠኛው ራሱ ሂሊናው የሚያዘውን ለመጠየቅ እድሉ የለውም።እንዲህ አይነት ውረደትን ለብዙ ግዜ መሸከም አንችልም ብለው አገር ጥለው የወጡ የራሱ ጋዜጠኞች የነገሩን እኛም የምናውቀው እውነት ነው።

እናም መለስ ዜናዊ ጥያቄ አዘጋጅቶ እንዲህ ብላችሁ ጠይቁኝ አለ “የቀድሞ ትውልድ መጥፎ አሻራዎች ምንድ ናቸው?” ። ይህ ሰው የዚያችን አገር ታሪክ ማዋረድና ምንም በጎ ነገር እንዳልተሰራ አድርጎ ለማቅረብ ካለው ምኞት የተነሳ ከጥሩ አሻራዎች ይልቅ መጥፎ አሻራዎችን ፈለጋ ላይ ግዜውን በከንቱ ያጠፋል። መለስ ዜናዊ ራሱ ላዘጋጀው ጥያቄ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ ለምሳሌ አለ “ለምሳሌ አጼ ቴዎድሮስ መድፍ መስራታቸው “tragedy” ወይም ደግሞ አሰቃቂ ስህተት ነበር” አለ። በዚህም ሳያበቃ “አገሪቷን አንድ ለማድረግ ይከተሉት የነበረው አቅጣጫ የጦርነት ነበር”። ስለሆነም እንደ መጥፎ አሻራ ሲጠቀስ ይኖራል አለ። ይታያችሁ አገራችን ኢትዮጵያን በሃይል ለመቀራመት በወቅቱ ያሰፈሰፉትን የውጪ ቅኝ ገዢዎችን ለመመከት የሚያስችል ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን መነሳትን ነው እንደወንጀል ቆጥሮ “tragedy” ነው የሚለን። እንግሊዞችን መርቶ ቴዎድሮስን በማስገደል በርሳቸው እግር የተተኩትንና ስለአገር አንድነት ቴዎድሮስ የሄዱበትን ሁሉ መንገድ ስለመጓዛቸው ታሪክ የሚያስታውሳቸው አጼ ዮሐንስን በተመለከተ መለስ እስከዛሬ ምንም ሲያወራ አለመሰማቱ እንቆቅልሽ ነው።

ወደ ዋናው ነጥባችን ስንመለስ መለስ ዜናዊ በዚህ ዙሪያ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተከታተለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሰውየውን ጤነኛ መሆን መጠራጠሩ አይቀርም። በዚህ ረገድ መለስ ዜናዊ ፍጹም ጤነኛ ነው። የሚናገረውም አስቦበትና አውቆት ነው።ዓላማውም አንድና አንድ ነው። ብዙዎች የሚኮሩበትንና ጀግንነታቸው በብዙዎች ዘንድ የታመነለትን አጼ ቴዎድሮስን ማንቋሸሽና ማዋረድ። ለነገሩ በዚያ ዘመን መለስ ዜናዊ በአጼ ቴዎድሮስ እግር ቢሆን ኑሮ ምን ታደርግ ነበር ተብሎ ቢጠየቅ ምን ብሎ እንደሚመልስ አድማጭ ልብ ይበል።መቸስ ጋዜጠኛዋ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ለመጠየቅ የሂሊና ነጻነት የላትምና ጥያቄው አለመነሳቱ ደግ ሆነ። ለማንኛውም መለስ ዜናዊና ድርጅቱ አጼ ቴዎድሮስን የማንቋሸሽ ምንጩ ለአማራ ህዝብ ካለው ሥር የሰደደ ጥላቻ የተነሳ እንጂ ሌላ አይደለም። ነፍጠኛ ወይም ደግሞ ትምክህተኛ እየተባሉ በመለስ ልቅ አንደበት ከሚሰደቡ ሰዎች መካከል አንዱ አጼ ቴዎድሮስ ናቸው። ይህን ጥላቻውን የሚገልጥበት መንገድ ፈልጎ ያገኘው የንጉሱን በጎ ሥራ”tragedy” ወይም አስቃቂ ስህተት ብሎ በማንቋሸሽ ነው።

በዚያ በጨለማ ዘመን ጉልበት ያለው ሁሉ እየተነሳ ለእኔ ካልገበራችሁ በክልሌ እንዳትደርሱ እያለ በየቀየው ነግሶ በሚያስቸግርበት ወቅት አገሪቷን አንድ ለማድረግ አጼ ቴዎድሮስ ሃይል ተጠቀሙ ብሎ መውቀስ የመለስን ወደር ያጣ ጥላቻ ከማሳያት ውጪ ሌላ የሚፈይደው ቁም ነገር የለም። አጼ ቴዎድሮስ በጎ ራእይ ይዘው ያለ ግዜያቸው የተፈጠሩ ከደመናው ባሻገር የጸሃይ ብርሃንን ማየት የሚችሉ ሩቅ አሳቢ መሪ ነበሩ። ኢትዮጵያችንን ትልቅ ለማድረግና በወቅቱ ከሚደረገው አፊሪቃን የመቀራመት አደጋም አገሪቷን ለመታደግ መድፍ ለመሥራት መጣራቸው በግዜው ማድረግ የሚገባቸው ወሳኝ ነገር እንጂ “ትራጄዲ” ወይም ደግሞ “አስቃቂ” ስህተት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ክስተት አይደለም። ይልቁንስ ትራጄዲ ተብሎ ሊጠቀስ የሚገባው ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ በሚፈልግበት ረሃብ ላይ ባለበት በዚህ በያዝነው አመት ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥቶ ሁለት መቶ የጦር ታንኮችን መግዛት ነው። ትራጄዲ የሚባለው ህዝቡ በርሃብ እያለቀ ባለበት በዚህ ክፍ ወቅት ከ8.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካገር አሽሽቶ በውጭ ባንኮች መደበቅ ነው። ትራጄዲ የሚባለው አጼ ቴዎድሮስ በባዶ እግራቸው ከጫፍ ጫፍ ደክመው ሊገነቡ የሞከሩትን ትልቅ ኢትዮጵያ ለማፍረስ መጣር ነው። ትራጄዲ ማለት እንደ መለስ ዜናዊ ዓይነት ጥቁር ሞሶሎኒ በምንሊክ ቤተመንግስት መቆናጠጡ እንጂ የአጼ ቴዎድሮስ መድፍ ለመስራት መሞከር አይደለም።

መለስ ዜናዊ የጣቱን ቅሰራ በአጼ ቴዎድሮስ ላይ ብቻ አያበቃም።አጼ ዮሃንስን ዘሎ አጼ ምንሊክንም ሊያጣጥል ሞክሯል። አጼ ዮሃንስን ያላነሳው አለምክንያት አይደለም ለንጉሱ ልዩ ፍቅር ያለው መስሎ በመታየት የትግራይን ሰዎች ደስ ያሰኘ መስሎት ነው።እውነቱ ግን መለስ ዜናዊ አጼ ዮሃንስ የሞቱለትን የደም መሬት ለደርቡሾች ወይም ለሱዳኖች አሳልፎ በመስጠት ለኢትዮጵያው ንጉስ አጼ ዮሃንስ ያለውን ብርቱ ጥላቻ በተግባር አሳይቷልና በመለስ ቶንኮል የተሞላበት ስልት የሚታለል ካለ ራሱ የፈጠራቸው ሆድ አደሮች ናቸው እንጂ ለእውነትና ለእኩልነት የቆሙ የትግራይ ተወላጆች በዚህ ርካሽ ምኞት የሚታለሉ አይሆንም።

አጼ ምንሊክን እንዲህ ሲል ያንቋሽሻቸዋል”አጼ ሚንሊክ ያደረጉት የልማት ጉዞ የተቀባባ ነበር።የውጭ ቴክኖሎጂን የራሳቸው ከማድረግ ይልቅ የውጭ ሙያተኞችን መጠቀምን እንደ አማራጭ ወሰዱ”የዚህ አባባል ጭብጥ ምን እንደሆነ ለአድማጭ ይቅርና ለራሱ ለመለስ ዜናዊም የሚገባው አይመስለንም። አጼ ምንሊክ እንደማንኛውም ሰው የራሳቸው ደካማ ጎኖች ቢኖሯቸውም በዘመናቸው ለዚያች አገር እድገት ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግናቸው እንጂ የሚያስወቅሳቸው አይደለም። ዛሬ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያዊያንን እያባረረ ከጉልበት ሠራተኛ አንስቶ እስከ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ድረስ ያሉትን ከውጭ አገር አምጥቶ እያሰራ ባለበት በዚህ ዘመን አጼ ምንሊክን በውጭ ሙያተኞች ተጠቀሙ ብሎ ሲወቅስ ትኝሽም አለማፈሩ የመለስን የጥላቻ ጥልቀት ያመለክታል። ዛሬ አጼ ምንሊክ ቢኖሩ ከመለስ ዜናዊ እጅግ በተሻለ ሁኔታ አገሪቷን መምራት የሚችሉ ሰው መሆናቸውን ታሪካቸው በቂ ምስክር ነው።

መለስ ዜናዊ የአጼ ምንሊክ ልማት የተቀባባ ነው ሲል የአንተስ ልማት ምን አተረፈልን ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ በየአመቱ ከ 14 |አሥራ አራት| ሚሊዮን በላይ ርሃብተኛን ይዛ ለልመና የተሰለፈችን አገር እንጂ ሌላ አይደለም። የአጼ ምንሊክ ልማት የተቀባባ አይደለም። በግዜያቸው ሊሰሩ የሚችሉትን ሰርተዋል። መኪና የሰይጣን ፈርስ ነው ብሎ በሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ መኪና በመሳፈር የሰው ልጅ የሰራው መጓጓዥያ መሆኑን ለህብረተሰቡ ለማስተማር ጥረዋል። ከዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ልቀው ወጥተው ባሰሩት የባቡር ሃዲድ ላይ ዛሬ አዜብ መስፍን ጫት እያመላለስች እየነገደችበት ነው። ያን ግዜ አጼ ምንልክ የጀመሩትን ስልክ ዛሬ “የምትታለብ ላም ነቸ” ብለው እነመለስ እየፈነጩበት ይገኛሉ። አጼ ምንሊክ ከሃይማኖት ትምህርት ውጭ ሌላ ትምህርትና እውቀት መኖሩን በማያወቅ ህብረተሰብ ውስጥ ሁነው ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር ችለዋል። ከጠበልና ከቅጠላ ቅጥል ውጪ ሌላ የህክምና ዘዴ መኖሩን ሰምቶ በማያውቅ ማህበረሰብ ውስጥ ሆስፒታል ለመክፈት አቅሙ የነበራቸው ብርቱ ሰው ናቸው። ልማታቸው የተቀባባ አልነበረም። በወቅቱ አስፈላጊ የሆነና በአስፈላጊው ቦታ ዘርን ማእከል ሳያደርጉ የተጀመሩ ከልብ የሆኑ ልማቶች ነበሩ። መለስ ዜናዊ ለእነዚህ ልማቶች እውቅና አልመስጠቱ የአጼ ምንሊክን ክብር ቅንጣም ታክል አይቀንሰውም።በዚህ ሃያ ዓመት ውስጥ መለስ ዜናዊ ከውጭ አገራት ያገኘው እርዳታና ብድር ኢትዮጵያ በታሪኳ መቸም አግኝታ የማታውቀው ቢሆንም አጼ ምንሊክ ካሰሩት የባቡር ሃዲድ ላይ አንድ ተጨማሪ የባቡር መንገድ እንኳን ሊሰራ አልቻለም። በልመናና በብድር የተገኘውን ገንዘብ በውጭ አገራት ባንኮች ደብቆ አስቀምጦ አጼ ምንሊክን ለመወቀስ መለስ የሞራል ብቃቱ የለውም። ሞሶሎኒ ምንሊክን እንደማያመሰግን ሁሉ ጥቁሩ ሞሶሎኒ መለስ ዜናዊ ምንሊክን ለማመስገን የሚያስችል የሞራል ብቃቱ አይኖረውም። ይሄን ደህና አድርገን እንገነዘባለን።

እንደገናም የጃፓንን እድገት ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር እየነጻጸረ የጃፓን እድገት ተሳክቷል የአጼ ቴዎድሮስ ግን አልተሳካም ብሏል።አሁን በመለስ ዜናዊ የምትገዛው ኢትዮጵያ ግን ከጃፓን ጋር አይደለም መንግስት አልባ ከሆነችው ሶማሊያ ጋር ስትነጻጸር የማትሻልበት ብዙ ነገሮች ያሏት መሆኑን መለስ ዜናዊ መናገር አይፈልግም። ዛሬ ሶማሊያውያን ሳታላይት ቴሌቭዝንን ለማየት የሚያግዳቸው የለም። በሶማሊያ ምድር ሬዲዮኖች ያለምንም አፈና ይሰራሉ። ኢንቴርኔትን ከኢትዮጵዊያን በተሻለ ደረጃ ሶማሌዎች ይጠቀማሉ። በሶማሌ ምድር የሚታፈን ወይም ብሎክ የሚደረግ ድህረ-ገጽ የለም።ዛሬ መለስ ዜናዊ እየገዛ የሚያሰቃያት ኢትዮጵያ ግን ህዝቦች ርስ በራሳቸው የማይተማመኑ፤ ጥላቻና ክፍፍል የነገሰባት፤ አንድነትና አገራዊ ስሜት የጠፋበት፤ በድህነቷና በኋላ ቀርነቷ የምትጠቀስ፤ በሙስና ምሳሌ ሆና የምትታወቅና አጠቃላይ የአገሪቷ የሞራል እሴቶች ተገለው የተቀበሩባት አገር ሆና ሳለች አጼ ቴዎድሮስን ከጃፓን ጋር እያነጻጸረ ሲወቅስ ማን ይጠይቀኛል ከሚል ከንቱ ትእቢት መሆኑን እንረዳለታለን። ይህም የትንሽነቱና ውረድት የሚሰማው ግለሰብ መሆኑን የሚያመላክት መሆኑንም እንገነዘባለን። ይህ ትእቢትና ማን አለብኝነት ግን ለከፋ ውረደት ይዳርገዋል እንጂ የሚያስከብረው ተግባር እንዳልሆነ አሳስበን እናበቃለን።

በመጨረሻም በህዝባቸው መካከል እጅ እየተነሳላቸው ከሚመላለሱና በወቅቱ ከነበረው ማህበረሰብ ጋር በቅርብ የሚተዋወቁ ነገስታትን አንድም ቀን ከቤተ መንግስት ወጥቶ ምን እንደሚመስል እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ይህ መንፈሰ ደካማውና ፍጹም ጨካኙ መለስ ዜናዊ በአገራችን አበው ላይ ትችት ሊሰነዝር ምንም ሞራል ብቃት የለውም።እንዲህ ዓይነት ግለሰብም ከስልጣኑ ወርዶ ለፍርድ እስከሚቀርብ ድረስ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን እንጂ በምንም አንፈታም።

መለስ ዜናዊ ሊያጣጥላቸው የከጀላቸውን ነገስታት በዘመኑ የነበረው ህዝብ እንዴት ያያቸው እንደነበርና ምን ዓይነት ቅኔ ይቀኝላቸው እንደነበረ በጥቂቱ አሳይተን ነገራችንን እንቋጫለን።

ለአጼ ቴዎድሮስ እንዲህ የሚል ቅኔ ተደርሶላቸው ነበር፤

ገደልን እንዳይሉ ሙተው አገኟቸው፤

ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው፤

ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው።

ይሄ እንግዲህ አጼ ቴዎድሮስ ለጠላት እጄን ከምሰጥ ብለው በገዛ ሽጉጣቸው ራሳቸውን የገደሉ ግዜ የተደረሰላቸው ቅኔ ነው።

ለአጼ ምንሊክ፤

ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ግዜ አበሻ።

በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ፤

ተፈጠመ ጣሊያን አበሻ እንዳይደርስ።

አጼ ምንሊክ አድዋ ላይ ድል ቀንቷቸው ወደ ሸዋ ሲመለሱ የተቀኙላቸው ነው።

አጼ ዮሃንስ በመተማ በተደረገው ጦርነት ድል ተመትተው የሞቱ ግዜ አንዱ እንዲህ ሲል ተቀኘላቸው።

በደንቢያ መታረድ አዝኖ ዮሃንስ፤

ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ።

እንዳያምረው ብሎ ድኻ ወዳጁን፤

መተማ አፈሰሰው ዮሃንስ ጠጁን።

ዜጎች ይሄን መሰሉን ቅኔ እየተቀኙ በወቅቱ ለነበሩት ነገስታት ፍቅራቸውንና ክብራቸውን ይገልጡ ነበር። አሁን መለስ ዜናዊ እንዲህ ያለ የህዝብ ፍቅርና ክብር አለው ወይ ብለን መጠየቅ ፈልገን ነበር። ሆኖም ግን መለስን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ማወዳደር እንደ አንድ አገር ወዳድ ነኝ እንደሚል የዋህ አምባገነን ስለሚያስቆጥረው ጥያቄውን ትተነዋል። የህዝብ ጠላት የሆነን ይህን ጨካኝ ግለሰብ ከነገስታቱ ጋር ማወዳደር የማይገባውን ክብር መስጠት ነው። መለስ ዜናዊ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ለማነጻጸር የሚያበቃ ስብእና የለውም። ነገራችንን በዚህ አበቃን። ቸር እንሰንብት።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!