ለዴሞክራሲና ለእኩልነት መረጋገጥ በጋራ የምናደረገውን ትግል የአንድነታችን መሠረት እናድርግ

የግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ራዕይ ሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጎች፤ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች እና ሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ታስቦ የተቀረፀ ነው።

የግንቦት 7 ተልዕኮ በሃገራችን ውስጥ አካባቢ ለይቶ፤ ዘውግንና ሃይማኖትን አማርጦ ተግባራዊ እንዲሆን የተቀረፀ አይደለም።

ግንቦት 7፣

  • “ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆን ይኖርበታል” የሚለው፣
  • ነፃ ተቋማት እንዲገነቡ የሚጥረው፣
  • ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲኖር የሚታገለው በመላው አገራችን – ኢትዮጵያ – ውስጥ ነው።

እነዚህ ታላላቅ ግቦች በአንድ ወይም በጥቂት የአገራችን ክፍሎች ተሳክተው በሌላ የአገራችን ክፍል ባይሳኩ የግንቦት 7 ተልዕኮ ተሳካ አይባልም።

ግንቦት 7 ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚያይ እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል እንዲታይ የሚታገል ንቅናቄ ሲሆን የህግ የበላይነት የሰፈነባት፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፤ የዜጎቿ ሁለንተናዊ መብቶች በእኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ብቻውን ወይም ከሚመስሉት ጥቂቶች ጋር ብቻ ተጋግዞ እውን ማድረግ ይቻላል ብሎ አያምንም። የምናልማት ውብ ኢትዮጵያን ለመገንባት መተባበራችን የግድ ነው ብሎ ያምናል።

እርግጥ ነው ግንቦት 7 በተቻለው ሁሉ ራሱን ጠንካራና በህዝብ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ድርጅት ለማድረግ ይሰራል። ይሁን እንጂ የሃገራችን የዴሞክራሲና የነፃነት ትግል ስፋት ያለውን የኅብረተሰቡን አባላት እና በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ አመለካከቶችንና ፍላጎቶችን አካቶ ካልተንቀሳቀሰ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላቂ ድል ሊቀዳጅ የሚችልበት እድል እጅግ ዝቅተኛ ነው ብሎ ያምናል። የተለያዩ አመለካከቶችንና ፍላጎቶችን የሚያንጸባርቁ የፖለቲካ ኃይሎችን በማስተባበር የሚደረግ ትግል መስዋዕትነቱን አነስተኛ፤ ትግሉን ደግሞ ቀልጣፋ ከማድረግ አልፎ በወያኔ ግፈኛ አገዛዝ መቃብር ላይ ለሚቆመው ዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት የሚሆነውን ሃገራዊ ሰላም ያስገኛል ብሎ ያምናል። በትግሉ ሂደት የሚፈጠረው መግባባት በድል ማግስት ለሚጀመረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና የሽግግር ሂደት አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብሎ ያምናል። ባለንበት ሁኔታ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸው ቡድኖች በከፍተኛ ትዕግስትና መግባባት አንዱ ሌላውን ሳያገል መሄድ ካልቻሉ ትግላቸው ከወያኔ ጋር መሆኑ ቀርቶ እርስ በርሳቸው ይሆናል የሚል ስጋት አለው። ከእንዲህ አይነቱ የተቃዋሚዎች ሽኩቻ በላይ ወያኔን የሚያስፈነድቀው ነገር የለም፤ እስካሁንም በኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ላይ እንዲቆይ ያደረገው ይኸው ነው።

ግንቦት 7፣ ዛሬ በሃገራችን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ፍላጎቶችና አመለካከቶች ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች፣ ማኅበረሰቦችና ዜጎች ሁሉ የወያኔ የመብት ረገጣ፣ የስደት፣ የግድያና የዝርፊያ ሰለባ ሆነዋል ብሎ ያምናል። ይህን ሃቅ ሆኖ እያለ ሁሉም በየግሉ የራሱን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርገው ጥረት የጋራ ባርነት፣ ውርደትና ስቃይ የሚያተርፍልን መሆኑ ብዙሃኑ የሃገሪቱ ህዝብ እየተረዳው መጥቷል የሚል እምነት አለን።

ግንቦት 7 ይህ የጋራ የመከራ እጣ ከታሪክ እስረኛነት፤ ከድርጅቶችና ከመሪዎች ግላዊ ፍላጎቶች፤ከምንከተለው የፖለቲካ ርዕዮተዓለምና ቀኖና በላይ ገዝፈን እንድንገኝ ያደርገናል የሚል እምነት አለው። ይህ እምነት ግንቦት 7 በአጠቃላይ በሃገር ጉዳይም ይሁን በአንድ ማኅበረሰብ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች፤ የሲቪክ ድርጅቶች፤ ከትልቁ ሆነ ከትንሹ፤ በርካታ ተከታይ አለኝ ከሚለው ሆነ ተከታይ የለውም ከሚባለው ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያደርገውን ጥረት አጥብቆ እንዲገፋበት የሚያበረታተው ሆኖ አግኝቶታል።

ግንቦት7 በአመለካከት በሚቀርቡትና በማይቀርቡት መሃል ጎራ ለይቶ ከሁሉም የኅብረተሰባችን አካላት ጋር የጀመረውን ግንኙነት የሚያጠብበት ምክንያት የለውም። በአስቸጋሪ ሁኔታ እየገነባው ያለውን የመገናኛ ድልድይ ሰብሮ ከዚህኛው ወይም ከእዛኛው የፖለቲካ ቡድን ውስጥ ተካቶ አንዱን አግልሎ ሌላውን አቅፎ የሚሄድበት በቂ ምክንያት የለም።

በወያኔ ላይ ተቃውሞ አለን የሚሉ ቡድኖች በሙሉ ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ እርስ በርሳቸው ተጨባጭነት ባላቸውም ሆነ በሌላቸው ጉዳዮች በመነታረክ የሚያጠፉት ጊዜ ለጋራ ውድመት እንጂ ለግል ድል የማያበቃቸው መሆኑን ነው። በተቃዋሚ ድርጅቶች መሃል ሰፊ ስምምነት መፍጠር እንኳን ባይቻል የሚስማሙ ኃይሎች ተባብረው በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ላይ ይዘምታሉ እንጂ ትግላቸውን ከሌሎች ታቃዋሚ ድርጅቶች ጋር አያደረጉም።

እንኳንስ ተቃዋሚዎች በተዳከሙበት በአሁኑ ጊዜ ቀርቶ ጠንካሮች ሁነው ቢሆንም ኖሮ ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ ለመፍታት መሞከር አዋቂነትንና አርቆ አሳቢነትን አያመለክትም።

ግንቦት7 ለድክመቱም ሆነ ለጥንካሬውም ተጠያቂ የሚያደረገው እራሱን ነው። የራሱን ድክመት ከራሱ ውጭ ባሉ አካላት ላይ አያላክክም።

ግንቦት 7 የሃገራችንን፣ የአካባቢያችንን የፓለቲካ ሁኔታ፤ ወያኔን እንቃወማለን የሚሉ ድርጅቶችን ጥንካሬና ድክመት በሚገባ መርምሮ በትብብር ጉዳይ ላይ የወሰደው አቋም አለው። ሌሎች ድርጅቶችም ይህንኑ አቋም፣ አመለካከትና እምነት እንዲጋሩ ጥረት ያደርጋል። ከዚህ ውጭ ግን የምለውን ካልሰማችሁ ብሎ የወያኔ ግፈኛ አገዛዝ ሰለባ ከሆኑ ወገኖቹ ጋር የሚያቃርነውና የሚያጣላው ምክንያት ከቶውኑ አይኖርም። ግንቦት 7 የሃገርና የዜጎች ጠላት ከሆነው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ላይ አይኑን አንስቶ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም።

የጋራ የሆነች አገራችንን በጋራ ለመገንባት የወንድሞቻችንና የእህቶቻችንን ቅሬታዎች የማድመጥ ትዕግሥትና ብልህነት ይኑረን። የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚያረጋግጠው እኩልነት የአንድነታችን መሠረት እናድርግ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!