የኦብኮ ሊቀመንበር እጄን ለፖሊስ አልሰጥም አሉ

በታምሩ ጽጌ | Reporter

የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ቶለሳ ተስፋዬ፣ ትናንትና ጧት የፍርድ ቤት ማዘዢያ ይዘው በቤታቸው የተገኙ ሁለት ፖሊሶችን አምልጠው መሰወራቸውን ምንጮች ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡ ‹‹ሁኔታው እስከሚጣራ ድረስ እጄን ለፖሊስ አልሰጥም፤›› ሲሉ አቶ ቶለሳ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኦብኮ ፓርቲ ሊቀመንበር በሆኑት በአቶ ቶለሳና በፖሊሶች መካከል በትናንትናው ዕለት ተፈጥሮ የነበረውን ሁኔታ በአካባቢው ሆነው የተከታተሉ ምንጮች እንደገለጹት፣ ሁለት ፖሊሶች ወደ አቶ ቶለሳ ቤት ደርሰው በበራቸው አካባቢ ቆመዋል፡፡ አቶ ቶሎሳ ሊወጡ ሲሉ ፖሊሶች መሆናቸውን ነግረዋቸው እጃቸውን እንዲሰጧቸው ሲጠይቁ፣ አቶ ቶሎሳ የተናገሩት ሳይሰማ ወደኋላ ይመለሳሉ፡፡

የውጭ በራቸውን ዘግተው ወደ ውስጥ የገቡትን አቶ ቶለሳን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሲቪል ልብስ የለበሱት ፖሊሶች ጥግ ጥግ ይዘው ቢጠባበቁም፣ አቶ ቶለሳ የውኃ ሽታ ሆነው በመቅረታቸው ፖሊሶቹ ግራ እንደተጋቡና የአቶ ቶለሳ ባለቤት በር ከፍተው መውጣታቸውን የተናገሩት ምንጮቹ፣ ፖሊሶቹ የያዙትን የፍርድ ቤት ሕጋዊ መጥሪያ ይዘው ወደ ውስጥ መዝለቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ፖሊሶቹ ወደ ውስጥ ገብተው ያደረጉትን ሁሉ ማወቅና መናገር እንደማይችሉ የገለጹት ምንጮቹ አቶ ቶለሳን እንዳላገኟቸው ግን እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል፡፡

የኦብኮ ሊቀመንበር አቶ ቶለሳ ተስፋዬን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አግኝተን ስለጉዳዩ አነጋግረናቸው፣ ‹‹ሁለት ፖሊሶች ከንጋቱ 12፡30 አካባቢ ቤቴ መጥተው እጅ ወደ ላይ አሉኝ፡፡ ምን አጠፋሁ አልኳቸው፣ ፖሊሶች ነን እጅ ወደ ላይ ሲሉኝ በማላውቀው ነገር ሊገድለኝም የመጣ ሊሆን ይችላል ብዬ በሌላ መውጫ ወጥቼ ሄጃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

እሳቸው በማያውቁት ነገር ቀደም ባሉት ጊዜያት ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተጋጯቸው ሰዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ቶለሳ፣ መንግሥት በግለሰቦች ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባና በዚያ ምክንያት እንደማይፈለጉ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

ሊይዟቸው የመጡት ፖሊሶች የአራዳ ክፍለ ከተማ አባላት ሲሆኑ፣ እሳቸው የሚኖሩት ግን በጉለሌ ክፍለ ከተማ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቶለሳ፣ ‹‹ይኼ ዝም ተብሎ ቤተሰቦቼንና እኔን ለማሸማቀቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለመንግሥት፣ ለኤምባሲዎች፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለፓርቲው አመራሮች ሪፖርት ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ቶለሳ፣ በትናንትናው ዕለት ከሰዓት በፊት ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት ወደ አምቦ እየሄዱ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

‹‹ፖሊስ ጣቢያ ቃሌን ባልሰጠሁበት ጉዳይ ይህ ለእኔ አፈና ነው፡፡ እኔ ተከስሼ አላውቅም፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ከግለሰቦች ጋር በነበረኝ ግጭት ተከስሼ ኅዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ዘግቶታል፤›› በማለት ፖሊስ ነን ላሉት ሁለት ግለሰቦች ምላሽ መስጠታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እሳቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እንጂ የመንግሥት ሹመኛ እንዳልሆኑ ማንም እንደሚያውቃቸው የገለጹት አቶ ቶለሳ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በሕዝብ ተመርጠው የፓርላማ አባል ሆነው ማገልገላቸውንና አሁን ደግሞ የፓርቲ አመራር መሆናቸውን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡

ከመሬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከግለሰቦች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል ስለሚባለው ተጠይቀው፣ ‹‹እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ሆነ ብለው እኔን ለመወንጀል ወይም ለወንጀል መነሻ ለማድረግ ሊሆን ይችላል፤›› ያሉት አቶ ቶለሳ፣ ‹‹እኔ መሬት ሰጭም ከልካይም አይደለሁም፤›› ብለዋል፡፡

ሕዝብና መንግሥት የሚያውቀው የፓርቲ አመራር መሆናቸውንና ነገሩ እስከሚጣራ እጃቸውን ለፖሊስ እንደማይሰጡ ያስታወቁት አቶ ቶለሳ፣ ሁለት ሆነው ከሚያሳድዷቸው ግለሰቦች አምልጠው መሄዳቸውን አልደበቁም፡፡

አቶ ቶለሳ ጧት ወደ ሥራ ሊሄዱ ሲነሱ ‹‹ፖሊስ ነን›› በማለት ራሳቸውን በመሸፋፈን ‹‹እጅ ወደ ላይ›› ሲሏቸው ወደኋላ ተመልሰው ለባለቤታቸው በመንገር በሌላ መንገድ ወጥተው ለጊዜው ዘወር ማለታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የሠሩት ጥፋት ካለ መንግሥት አጣርቶ ጥፋተኛ ሆነው ካገኛቸው፣ ማንም ከሕግ በላይ ስላልሆነ በአግባቡ ተጠርተው ሕግ ፊት መቅረብ እንደሚችሉ አቶ ቶለሳ ተናግረው፣ ከዚህ ውጭ ከሆነ አፈና በመሆኑ እንደማይስማሙና የመንግሥትም አቋም እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡

አቶ ቶለሳ ‹‹ደረሰብኝ›› የሚሉትን ሕገወጥ ድርጊት በሚመለከት በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የአራዳ ክፍለ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ አበበን አነጋግረናቸው፣ ወደ አቶ ቶለሳ የሄዱት ፖሊሶች ሕጋዊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዘው መሆኑን አስታውቀው፣ ‹‹እርሳቸው ሕጋዊ ከሆኑ ወደ ሕጋዊ አካል መሄድ ነበረባቸው፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊስ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ የማስፈጸም ግዴታ እንዳለበት ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረው፣ አቶ ቶለሳ ግን ፍርድ ቤት የላከውን መጥሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ፖሊስ በዩኒፎርምም ሆነ በሲቪል ልብስ ሆኖ ሕጋዊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመያዝ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ቶለሳ ማድረግ የነበረባቸው ‹‹እናንተ እነማን ናችሁ?›› ብለው ጠይቀው መታወቂያቸውን ካዩ በኋላ ወደ ተፈለጉበት ቦታ መሄድ ሲገባቸው፣ ይኼንን አለማድረጋቸውን በመግለጽ ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

አቶ ቶለሳ በትናንትናው ዕለት ከሰዓት በኋላ 11፡30 ሰዓት አካባቢ ወደ ሪፖርተር ቢሮ ደውለው እንደገለጹት፣ አምቦ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ደርሰው ከወንድሞቻቸውና ከፓርቲው አባላት ጋር ከተመካከሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡

‹‹አንተ ንፁህ ከሆንክ ማንም በመሰከረው ወንጀለኛ አትሆንም፡፡ ወደፊት ወንጀለኛው በገሀድ ይታወቃል፡፡ አሁን ተረጋግቻለሁ፤ ለሚፈልገኝም አካል ለማስረዳት ፈቃደኛ ነኝ፤›› ያሉት አቶ ቶለሳ፣ እሳቸውም ሆኑ የሚመሩት ፓርቲ ሰላምን የሚያራምድ መሆኑን ተናግረው፣ እሳቸውን በሐሰት እየወነጀሉ ያሉትን ግለሰቦች እንደደረሱባቸውና ማስረጃ እያሰባሰቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቀድሞውንም ‹‹ፖሊስ ነን ሲሉዎት እጅዎን ለምን በሰላም አልሰጡም?›› ተብለው ሲጠየቁ፣ ‹‹ወደ ቤቴ ተመልሼ ራሴን ማረጋጋት አለብኝ፡፡ ማንንም የፈለጋችሁበት ውሰዱኝ የምል ሰው አይደለሁም፡፡ ፖሊስ ነኝ ብሎ ምንም ምልክት የሌለው ግለሰብ ገድሎኝ ቢሄድስ?›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገሩ የፖለቲካ እንጂ የወንጀል ጉዳይ አለመሆኑንና ለሚመለከተው አካልም እንደሚያስረዱ የገለጹት አቶ ቶለሳ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ‹‹ትፈለጋህ›› ብሎ ማንም ሰው አንድ ቀንም ቢሆን መጥሪያ አምጥቶላቸው እንደማያውቅ አስረድተዋል፡፡

አሁን ሕዝቡም ሆነ መንግሥት እንዲያውቀው ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በየደረጃው ደብዳቤ መጻፋቸውንም አቶ ቶለሳ ተናግረዋል፡፡