ኢህአዴግ የሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን አዳፍኖ ለማለፍ ያቀደው ሴራ በሕዝባችን ሠላማዊ ትግል ይከሽፋል!
ከኢትዮጵያ ፌዴራል ዴምክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)
የኢህአዴግን ስርአት ባለፉት 20 ዓመታት እንዳየነው አቋሞቹ ላይ ከፍተኛ መዋዠቆች የሚታዩበት ዛሬ ያዝኩ ያለውን አቋም አምኖና በርሱም ተማምኖ ምንም ነገር በግልም በቡድን ማቀድ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም ሆኖ “በእቅድ የምመራ ነኝ በዚሁም ፈጣን እድገት እያመጣሁላችሁ ነው” እያለ መመፃደቁን ቀጥሎበታል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት አሳካዋለሁ ብሎ ቃል የገባውን ምን ላይ እንደደረሰ በቅጡ ሳይነግረን አሁን ደግሞ “በአምስት ዓመት ውስጥ በምግብ ራሳችንን እንድንችል አደረጋለሁ” “በአምስት ዓመት ውስጥ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እውን እንዲሆን በማድረግ ኢኮኖሚው ግብርና መር ከመሆን ኢንዲስትሪ መር ወደ መሆን እንዲሸጋገር አደርጋለሁ” የሚል ይዘት ያለው ዲስኩር ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡ ይህ ባዶ ተስፋ የመደርደር እውነታ በተለይ በፖለቲካው መድረኩም ላይ የጎላ መሆኑ ሁኔታዎቸን በንቃት ከሚከታተል ማንኛውም ዜጋ የተሰወረ አይደለም፡፡
ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን እገነባለሁ›› ማለቱና ይህንን አቋሜ ያለውን ቁም ነገር በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ጭምር መደንገጉም የሚታወቅ ነው፡፡ መላው ሕዝባችን ከዘመናት የጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ በነበረው ጉጉት ኢህአዴግ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ የገባውን ቃል ተረጋግቶ እንዲፈጽም ዕድልና ፋታ ሰጥቶታል፡፡ የተደራጁ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ሃይሎችም አንግበው ለተነሷቸው ጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚገኘው በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንደሆነ በማመን ኢሕአዴግ ባዋቀረው የሽግግር መንግሥት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለሂደቱ እገዛ በማድረግ ተባብረዋል፡፡ አለም አቀፉ ለጋሽ ሀገራትና የገንዘብ ተቋማትም ከቀውስ ነፅቶ በማያውቀው አፍሪቃ ቀንድ ላይ የሰላምና የዴሞክራሲ ተስፋ ቀንዲል ኢትዮጵያ ላይ የበራ መስሏቸው በከፍተኛ ተስፋ ያልተቆጠበ ድጋፍ መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡
በዚህ ድጋፍ የተኩራራው የኢሕአዴግ አመራር በሰነዶቹ ያስፈራራቸውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እሴቶች መሸርሸር፤ ለዴሞክራሲ መብት የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች ሁሉ መወንጀል /criminalize ማድረግ/፤በራሱ አመራር ውስጥ የዴሞክራሲና የሀገር ሉዓላዊነት ጥያቄዎችን ባነሱት ላይም አልባሌ ምክንያቶችን በመፍጠር ማሰርና ማሳደድን፤ በሕዝቦች መሃከል አታካራዎችና ግጭቶች እንዲፈጠሩ ማድረግን ሥራዬ ብሎ አቅዶ ትንቀሳቅሷል፡፡ ይህንን ሁኔታ በማክረርም ከሽግግሩ ፓርላማ ጀምሮ በአገራችን የፖለቲካ መድረክ ተዋናይ የነበሩትንና ሕዝባዊ ይሁንታን በማግኘት በፌዴራልና በየክልል ምክር ቤቶቹ አማራጭ አቋማቸውን ሲያራምዱ የቆዩትን የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ስም በተቀነባበረ ሴራ በምክር ቤቶቹ እንዳይገኙ እስከ ማድረግ ዘልቋል፡፡
ይህ በኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ሀይሎችና በአጠቃላዩም በሕዝብ ላይ ሲፈፀም የነበረው የአፈና ተግባሩ እንዳለ ሆኖ የአለም አቀፉን ለጋሽ ማህበረሰቡንም በአንፃሩ ሲያምታታ እንዱን ከሌላው ነጥሎ ሲያስፈራራና ‹‹ዕርዳታችሁን ጠቅልላችሁ ሀገራችሁ ግቡ…. ወዘተ›› በማለት ጉራ ሲነዛ ቆይቷል፡፡ይህ የምእራባውያንን ለጋሽ ሀገሮች መንፈስ ያናወጠ ዘዴው በእጅጉ ተሳክለቶለት የጠየቀውን ድጋፍ ሁሉ እያገኘ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥረቶች ላይ ከፍተኛ ደባ በማንአለብኝነት እየፈፀመ እነሆ አሁን ለደረሰበት የዴሞክራሲ ግብዓት-መሬት እወጃ እርምጃው ደርሷል፡፡
የኢሕአዴግ አፈና ገና ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ የታየ ቢሆንም የለበሰው የዴሞክራሲ ለምድ ተገፎ ማንነቱ ያለምንም ድብብቆሽ ገሃድ የወጣው በምርጫ 1997 መባቻ ነው፡፡ ከ1998 ጀምሮ የተሰየመውና ኢሕዲግ በጉልበትና በማጭበርበር ፍፁማዊ የበላይነት የያዘበት ፓርላማ፤ የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን የሚያፋኑ፣ ከኀብረተሰቡም ድጋፍ እንዳያገኙ በሕግ ተጠያቂነት ማዕቀብ አጥሮ ዐቅም የሚያሳጡ ሕጎችን ሲያወጣ ከርሞል፡፡ ለፓርቲዎች ድጋፍ ‹‹መንግሥት በጀት ይመድባል›› የሚል የይስሙላ ምክንያት በመደርደር ለጋሽ ሀገራት ይስጡ የነበረውን ድጋፍ ምንጩን በማድረቅ፣የፓርቲዎችን በምርጫዎች የመወዳድር አቅም ጨርሶ የማሳጣት ተንኮል ሠርቷል፡፡ አዲስ ባወጣው የሲቪክ ማሕበራት ሕግ በኩል ሊያሳካ ያሰበው የማይቆጣጠራቸውን ነፃ ማሕበራት ሁሉ የማክሰም ሴራውም እንዲሁ ተሳክቶለታል፡፡
የምዕራብ ዓለም በመላና የአሜሪካን መንግሥት በተለይ፣ ‹‹የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ›› በማለት ለተያያዘው እንቅስቃሴ በጉዳይ ፈጻሚነት ራሱን ከማቅረብ አልፎ በመሄድ፣ ኢሕአዴግና መንግሥቱ አዋጅ አውጭ እና ፈፃሚ በመሆን፣ በሀገሪቱ ውስጥ የሚደረገውን የፓርቲዎች እንቅስቀሴዎች ከሽብረተኝነት ጋር ለመፈረጅና በዚሁ ለመወንጀል ተንቀሳቅሰዋል፡፡ይህ መሰሪ የኢህአዴግ እርምጃ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የእንቅስቃሴ ነፃነት ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወጡት የምርጫ ሕጐችን የማሻሻያ አዋጆች ቀደም ባሉ አመታት የነበሩትና ለተቀዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቀሴዎች በአንፃራዊነት ዕድል የሚሰጡ በሮችን ሁሉ ጠርቅመው ዘግተዋል፡፡ በዚህ ላይ የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን አውታሮችን በብቸኛነት ከመቆጣጠር አልፎ የግል ፕሬስን በሕግ ጥሰት በመወንጀል ፍራቻ የሚሸብብ አዲስ ሕግ በማውጣት፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎች አዘጋገባቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራስያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ይህንን በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለውን ኢ-ሕገመንግሥታዊ ዙሪያ-ገብ ከበባ ለመስበር ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ የመጣውን ፖለቲካዊ ምኅዳር ለማስፋት እንዲቻል ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ያደረገው ጥረት ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ጥረቱ የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰቡ ድጋፍ ይታከልበት ዘንድ ከፍተኛ ዲፕሎማስያዊ እንቅስቃሴዎች ማድረጉም ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ ኢሕአዴግ ዋነኛውን የፖለቲካ ምህዳር የማስፋቱን ጥያቄ ዋጋ ለማሳጣት አቅዶ ባደረገው እንቅስቃሴው “የምነጋገረውና የምደራደረው በምርጫ ስነ-ምግባር ሕጉ ላይ ብቻ ነው” የማለት አቋም ወስዷል፡፡ ለዚህ የተንኮል አቋሙም በቂ ፓርቲዎች ከተቃዋሚ ጎራ ጭምር ማሰለፍ ከመቻሉ ባሸገር የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡንም በእጅጉ አሳስቷል፡፡ ኢህአዴግ ‹‹ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የሥነ-ምግባር ኮድ ላይ ከተስማማን ሁሉም የምርጫ እንቅስቃሴ ችግሮች ይፈታሉ›› በሚለው የብልጣብልጥነት ስልቱ ሌሎችን ሊያሳስት ቢችልም መድረክ ግን የዚህ ተንኮል ሰለባ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በአንፀሩ መድረክ ይህንን ኢሕአዴግን የተንኮል ዕቅድ በተገቢው ተረድቶት ስለነበር በዚያ ድርድር ተብዬው ሂደት ውስጥ ሳይገባ በመሰረታዊ የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበት ጉዳዮች ላይ ውይይቱና ድርድሩ እንዲደረግ በሚያደርጋቸው ጥረቶቹ ለመቀጠል ተገዷል፡፡
ኢሕአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን በአፋኝ አዋጆች ተብትቦ ባጠበበበትና ለምርጫ ውድድር የማይመች ሁኔታን በፈጠረበት አኳኋን መድረክ ወደ ግንቦት 2002 ምርጫ ሲገባ እውነታውን ካለመገንዘብ ሳይሆን አባል ድርጅቶቹ ባለፉት ምርጫዎች ላይ ከነበራቸው ልምድ በመነሳት፤ የምርጫውን ሜዳ ለኢህአዴግና ለግብረአበሮቹ ከመልቀቅ ይልቅ በሂደቱ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡን በማታገል ኢህአዴግ ላይ ጫና እያሳረፉ አንዳንድ ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ በማድረግ፤ለድል መብቃት ይቻላል ከሚል እሳቤ ነበር፡፡ መድረክ በኃላፊነት መንፈስ ይህን ያድርግ እንጂ በሂደቱ እንደታየው ኢሕአዴግ መድረክ በምንም መንገድ የፓርላማ ወንበር እንዳያገኝ በሚል ምርጫውን ሙሉ ለሙሉ ለመንጠቅ ኢ-ሕገመንግሥታዊና ሕገ-ወጥ ዝግጅቶችን አጠናቆ መንቀሳቀሱ በሂደት ጉልህ ሆኖ ወጥቶአል፡፡ ከነዚህ ዝግጅቶች መሃከል መድረክን ‹‹ፀረ-ሰላምና ሽብርተኛ ድርጅት ወዘተ›› በማለት በድርጅታዊ ሰነዶች ሁሉ መወንጀሉና ለጥቃት ዒላማው ማዘጋጀቱ ነበር፡፡ መራጩን ሕዝብ በካድሬዎቹ በማስፈራራት ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚል የጥርነፋ ስልቱ ውስጥ በማስገባት በቡድን ለኢሕአዴግ ድምፅ እንዲሰጥ በሕገ ወጥነት ማስገደዱ ከዚህ በፊት ያልታየ ሌላው የኢህአዴግ አዲስ ስልት ነበር፡፡ ለዚህ ሕገ ወጥ አስፈራርቶና አስገድዶ ድምፅ የማሰጠት ዕቅዱ ስኬት፤ የምርጫ ቦርድም በቡድን ድምፅ ለመስጠት የሚያመች ሁኔታዎችን በየድምፅ መስጫ ጣቢያዎቹ በማዘጋጀት የበኩሉን ዝግጅት አድርጓል፡፡
በ2002 ምርጫ ላይ ኢሕአዴግ ከሠራቸው ወንጀሎች ሁሉ በላይ የሚያስገርመው በመጨረሻውና ባለቀ ሰዓት ላይ ‹‹መድረክ ከምርጫው ወጥቻለሁ አለ›› የሚል የተጭበረበረ ሀሰተኛ ሰነድ በመድረኩ ስም በካድሬዎች ማስበተኑ ነበር፡፡ መድረክን ከምርጫው ሂደት ውስጥ ለማስወጣት ያከናወናቸው ነውረኛ ተግባራት ሳይሳኩለት ሲቀሩ ኢህአዴግ እንደዚህ ወደ መሳሰሉ ያዘቀጡ ተግባራት ነው የገባው፡፡ ይህም ሁኖ ፍትሕና ዳኝነት ባያገኝም መድረክ እነዚህን ክስተቶች በማስረጃ በማስደገፍ ለብሄራዊ የምርጫ ቦርድና ከዚያም በኃላ ጉዳዩን በይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመውሰድና እስከ ሰበር ችሎት ድረስ በመዝለቅ በምርጫ ስም የተፈፀመውን ውንብድና ለማጋለጥ ጥረት አድርጓል፡፡
ኢህአዴግ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ሃይል ማሰማራትን ጨምሮ ያከናወነው ሕገ ወጥ የምርጫ ዝርፊያ የሕዝብ ቁጣና እምቢታ ያስከትላል የሚል ስጋት እንዳሳደረበት መገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህም በማሳበብ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በሃሰት ለመወንጀል ውጥን እንደነበረው በገሃድ የገለጸበት ሁኔታ ቢኖርም መድረክ የሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ፓርቲ በመሆኑ ውጤቱን በመቃወም ምርጫው ይደገም ብሎ ለሕዝብ ይፋ ከማድረግና ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ አልፎ ሰበብ ሊሆን የሚችል ሁኔታ ባለመፍጠሩ ኢህአዴግ ይህንኑ የቋመተለትን ሴራ እውን ማድረግ አልተቻለውም፡፡ መራጩ ሕዝባችንም በምርጫው የተፈፀመውን ደባ አሳምሮ ቢገነዘብም መድረክ ያሳየውን ትዕግስት የተሞላበት አካሄድ በመገንዘብ ቁጣውንና ቁጭቱን ተቋቁሞ ምርጫው በሰላም እንዲያልፍ በማድረግ የተለመደውን ታጋሽነቱንና ትልቅነቱን አሳይቶአል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ‹‹ደምፄን አላስርቅም›› በሚል ፍጥጫ መራጩ ሕዝባችን በስፋት ገብቶ ቢሆን በሰው ሕይወት ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን የጉዳት መጠን በውስን ደረጃም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ከደረሰው ስንመለከተ እጅግ የከፋ ሊሆን ይችል ነበር፡፡
ኢህአዴግ አገኘሁት የሚለው የምርጫ ውጤት በሕግና በስርዓት የተገኘ ሳይሆን በጉልበትና በአፈና የተገኘ ምርኮ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎች “ምርጫው ዓለማቀፋዊ መመዘኛዎችን ያላሟላና ለሁሉም እኩል ባልሆነ የጨዋታ ሜዳ የተካሄደ ነው” ማለታቸው፤ የአሜሪካን መንግስታ ጨምሮ በርካታ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ይህንኑ ማስተጋባታቸውን ስንመለከት የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግንዛቤም ከሕዝባችን ግንዛቤ ብዙም ያልተራራቀ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ እውነታ እየታወቀም ነው ኢህአዴግ “ሕዝቡ 99.6% ድምፁን ሰጥቶ መረጠኝ፣ በዚህም አውራ ፓርቲ እንድሆን አብቅቶኛል” ወደ ማለቱ ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ አይነቱ ድራማ የገባው፡፡ ይህንን በምርኮ የተገኘን ውጤት መነሻ በማድረግ “የአውራ ፓርቲና የተተካኪ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርአት” በሚለው ፌዝ ውስጥ ገብቶ ህዝባችንንና የአለምአቀፉን ማሕበረሰብ ግራ ለማጋባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ “ሕዝቡ እኔን ብቻ በአውራ ፓርቲነት መርጦ መሪነቱን ሰጥቶኛል” በሚል ማጭበርበራያ ስልት በሕገ-መንግስቱ በተደነገገው የመድበለ ፓርቲ ግንባታ መርህ ላይ ከሰራው ወንጀል ራሱን ነጻ ለማውጣትና ተዓማኒነትን ለማግኘት እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡ የዚህ ሴራ ዋና አለማ እያሰፈነ ያለውን የአንድ ፓርቲ ፍፁማዊ አምባገንነት ለተጨማሪ 20 አመታትና ከዚያም በላይ ለማዝለቅ እንደሆነ ደግሞ ከሚሰጣቸው እወጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡
ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች በተለይ ደግሞ መድረክ ምርጫው አንዳች ወንበር እንዳያገኙ ያላሴረ ይመስል የምርጫ ድራማውን ከውኖ በጨረሰ ማግስት “በፓርላማ ወንበር ባታገኙም አብሬአችሁ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” በማለት ሲመጻደቅ ተስተውሎአል፡፡ ይህም ቢሆን ሃላፊነት የተላበሰ (magnanimous) መስሎ በመቅረብ የሕዝባችንንና የአለምአቀፉን ማሕበረሰብ ቀልብ ለመሳብ የመጣ ማስመሰያ ተውኔት እንጂ ኢህአዴግ ሰጥቶ ለመቀበል ያልተዘጋጀ ፓርቲ ለመሆኑ የእስካሁኑ የድርድር ልምዶች ያመለክታሉ፡፡ ኢህአዴግ በአንድ በኩል “አብሬአችሁ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” እያለ በሌላ ወገን ደግሞ ፓርቲዎቻችንን ለማፍረስ በደህንነት ተቋሞቹ ዘመቻ ከፍቶብናል፡፡ በርካታ አባሎቻችን ከነበሩበት የመንግስት ስራ እንዲባረሩ እየተደረገና ስራም የመቀጠር እድል እየተነፈገ በገዛ ሃገራቸው ሰርተው ለመኖር የማይችሉበትን ሁኔታ እየፈጠረባቸው ይገኛል፡፡
የታሪክን ሂደት ወደ ኃላ ለመመለስ ኢህአዴግ የሚያደርገውን ሕገ መንግስታዊው መድበለ ፓርቲያዊ ስርዓትን የማጥፋት ሴራ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገለውና የሚያከሽፈው እንደሆነ መድረክ ፅኑ እምነት አለው፡፡ የሕዝቡን ትግል በቆራጥነትና በብቃት ለመምራት መድረክ ድርጅታዊ ብቃቱን በማጠንከር በሁለንታዊ መልኩ መዘጋጀት እንደሚኖርበትም ይገነዘባል፡፡ ለዚህም የመድረክን ድርጅታዊ ብቃት ለማሳደግና አሁን ካለበት የቅንጅት ደረጃ አደረጃጀት ከፍ ወዳለው የግንባር ደረጃ ለማሸጋገር የተደረሰውን ውሳኔ እውን ለማድረግ የሚከናወነው ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢህአዴግ ዝግጁነቱና ፈቃደኝነቱ ካለው መድረክ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ ወደፊትም በመሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመደራደርና የመነጋገር ፍላጎትና እቅድ እንዳለው ለማሳወቅ ይፈልጋል፡፡ የድርድሩና የንግግሩ ማጠንጠኛው ‹‹የሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች መሰረት የሆነው መድበለ ፓርቲያዊ ስርዓት ሕጋዊና ተቋማዊ ጥበቃ እንዲያገኝ›› መጠየቅ ይሆናል፡፡ በዚህ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳይ ስር የሚከተሉት አምስት አበይት ጉዳዮች ይካተታሉ፡፡
1. በአገራችም መድብለ ፓርቲያዊ ስርዓት ይረጋገጥ ዘንድ ሕጋዊና ተቋማዊ ሁኔታ ስለ መፍጠር:-
1.1. በሕግ መሰረት ለፖለቲካዊ ስልጣን የሚፎካከሩ ፓርቲዎችን ከሻዕብያ፤አልሸባብና መሳርያ አንግበው ከሚቃወሙ ድርጅቶች በ “ጥፋት ግምባርነት” ፈርጆ እንደጠላት የድህንነት ተቋማት የጥቃትና የስለላ ዒላማ ማድረግ እንዲቆም፡፡
1.2. መድረክ ሪፈረንደምን ጨምሮ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ የሚፈቅደውን ስርዓት በመከተል ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል እንዲሻሻል የሚል አቋም ማራመዱ ሕገ መንግስታዊ መሆኑ፤ኢህአዴግ “ሕገ መንግስቱ የተዋጣለት ነው” ማለት መብቱ እንደሆነ ሁሉ መድረክ “ሕገ መንግስት ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል” ማለቱ ሕገ መንግስታዊ መብቱ መሆኑን እንዲቀበል፡፡ የመሻሻል ወይም ያለመሻሻል ውሳኔውና ስልጣኑ የሕዝብ እንጂ የኢህአዴግ ወይም በኢህአዴግ ሰጦታ የተወሰኑ የመንግስት አካላት (መከላከያ፤ ድህንነት፤የፍትሕ ተቋማት ወዘተ) ስልጣን እንዳልሆነ እንዲቀበል፡፡
1.4. በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተከሰተው የገዢው ፓርቲ መዋቅርና የመንግስት መዋቅር ድንበር የጠፋበት ሁኔታ እንዲስተካከልና ገዢው ፓርቲ እንደ አንድ ፓርቲ ራሱን ችሎና ተለይቶ እንዲቆም እንዲደረግ፡፡
1.5. ገዢው ፓርቲ የመንግስትን ሃብት እንደ ራሱ ሃብት የሚጠቀምበት ሁኔታ እንዲቆም፡፡ መንግስት አቅም የፈቀደውን ድጎማ ለፓርቲዎች እንዲያደርግና ገዢው ፓርቲም እንደሌሎቹ የዚህ ጥቅም ተካፋይ የሚሆንበት ሁኔታ በመፍጠር አሁን የሚታየውን አድሎአዊ አሰራር ማስቀረት፡፡
2. በአገራችን ለነፃ ዴሞክራስያዊና ፍትሐዊ መርጫ መኖር እንቅፋት የሆኑ ሕጋዊና ተቋማዊ ሁኔታዎችን ማስወገድ:-
2.1. ለነፃ ዴሞክራስያዊና ፍትሐዊ ምርጫ እንቅፋት ሆነው የተገኙት ሕጎች እንዲከለሱ ማድረግ፡፡
2.2. ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎችን ሲያከራክር የቆየው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ያለመሆኑ ጉዳይ ሁለቱንም ወገኖች ሊያስማማ የሚችል አመራር እንዲኖረው ማድረግ፡፡እርሱን የሚመለከቱ አዋጆችና ደንቦችም እንደዚሁ እንዲከለሱ ማድረግ፡፡
2.3. ከምርጫ ቦርድ ቀጥሎ እስከ ዝቅተኛው ደረጃ ድረስ የሚቋቋመው የምርጫ አስፈፃሚ መዋቅር እንደዚሁ ገለልተኝነቱን ይረጋገጥ ዘንድ የሚደራጅበት ስርዓትና የስራ መመርያው በስምምነት እንዲቀረፅ ማድረግ፡፡
2.4. በአገራችን ገለልተኛ የሆኑ የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች በብዛት ይኖሩ ዘንድ በአገራችን ነፃና ገለልተኛ ሲቪክ አደረጃጀቶች እንዳያብቡ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችና ሕጎች እንዲስተካከሉ ማድረግ፡፡
2.5. በገለልተኝነታቸውና የሙያ ስነ ምግባራቸው አለማቀፋዊ ከበሬታ ያተረፉ አለምኣቀፍ ታዛቢዎች በብዛት የሚመጡበት፤በወቅቱ ስራቸውን የሚጀመሩበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግ፡፡ አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ሁሉንም የሚያስማማ የምርጫ ታዛቢዎች ስነ ምግባር ኮድ እንዲኖር ማድረግ፡፡
2.6. ሁኔታዎችን ለአንድ ፓርቲ አገዛዝ ለማመቻቸት ተብሎ ኢህአዴግ በብቸኝነት የቀረፀው የቀበሌ ምክር ቤት አወቃቀር ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንደሚመች ሆኖ መልሶ እንዲዋቀር ማድረግ፡፡
2.7. በቀበሌ ያለው የመንግስት መዋቅር፤የገዢው ፓርቲ መዋቅርና የእርዳታ እደላ መዋቅሮች አንድ እንዲሆኑ በማድረግ እርዳታን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ለመፍጠር የሚውልበትን ሁኔታ ማስወገድ፡፡ ዜጎች እርዳታ የማግኘት መብታቸው እንዲከበርና ይህ መብታቸው ከፖለቲካ አቋማቸው የማይቆራኝበት ሁኔታ መፍጠር፡፡
3. የዜጎች ሃሳብን በነፃ የመግለፅ፤የመደራጀትና የመቃወም መብቶች ሕጋዊና ተቋማዊ ጥበቃ እንዲያገኙና ክልከላና ፍርሃት እንዲወገድ ማድረግ:-
3.1. በሕገ መንግስቱ ከሰፈሩት ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች ጋር የሚጣረሱ አሰራሮችና የስር ሕጎች እንዲከለሱ ማድረግ፡፡ እነዚህ መብቶች በሕገ መንግስቱ በሰፈሩበት መንፈስ ተግባራዊነታቸውን የሚያረጋግጡ ሕጎች እንዲወጡና አስፈፃሚ ተቋማትም በዚሁ መንፈስ እንዲደራጁና እንዲሰሩ የሚያስገድድ ሁኔታ መፍጠር፡፡
3.2. የመንግስት ሚድያ የገዢው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ አዝማቾችና በተቃዋሚዎች ላይ የስነ ልቦና ጦርነት ማካሄጃ ተቋሞች ከመሆን ተላቀው ገለልተኝነታቸው የሚረጋገጥበት ስርዓት እንዲበጅ፡፡ ተቃዋሚዎችም የመደመጥ መብታቸው ተረጋግጦ ጉዳያቸው ተገቢውን ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ፡፡
3.3. አሌክትሮኒክ ሚድያ መንግስታዊ ላልሆኑና ለግሉ ሴክተር ክፍት የሚሆንበት፤ በእነዚህ በኩል አማራጭ የተሌቪዥንና የአጭር ሞገድ ሬድዮ ስርጭት የሚኖርበት ሁኔታ መፍጠር፡፡መረጃን ለመከልከል የሚደረጉ ተግባራት ቆመው በምትኩ የአገራችን ዜጎች ለመረጃና ለእውቀት ቅርበት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ፡፡
3.4. መረጃን በማሰባሰብና በማሰራጨት መብቶች ዙርያ በተለይ በሕትመት የሚካሄዱትን ክልከላዎች እንቅፋቶችና እጅ አዙር ሳንሱሮች እንዲቀሩ ማድረግ፡፡ ፍርሃት የሚፈጥሩ አሰራሮችንና ሕጎችን መከለስ፡፡
3.5. በዜጎች የመደራጀት መብት ላይ፤በመሰብሰብ መብት ላይ፤በመቃወምና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች ላይ የተደቀኑት አስቸጋሪ አሰራሮች በማያዳግም መልኩ ይስተካከሉ ዘንድ ወጥና ግልፅ የሆኑ ሕጎችን በማውጣትና የታወቀ አስፈፃሚ ተቋም በማደራጀት እንዲስተካከል ማድረግ፡፡
4. በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እየተደረገ ያለውን የአፈና እና የማቀጨጭ እርምጃ እንዲቆም ማድረግ:-
4.1. ስብሰባ ለመጥራት፤ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራትና ማንኛውም ሕጋዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማከናወን ረገድ የሚፈጸሙባቸውን ዕንቅፋት ማስወገድ
4.2. በእንቅስቃሴ ላይ ላሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጽ/ቤት የሚሆኑ ቤቶችን ለሁሉም በመስጠት ይህ ለሁሉም በፍትሐዊነት የሚፈቀድ መብት መሆኑን ማረጋገጥ፡፡ ፓርቲዎች ጽ/ቤቶችን ከፍተው እንዳይንቀሳቀሱ በግልፅም ሆነ በስውር በድህንነትና በፖሊስ የሚደረግባቸውን ወከባና ስለላ እንዲቆም ማድረግ፡፡
4.3. ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳና መሰል የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ማድረግና በሰበብ አስባብ አባላትን እያሰሩ ሰዉ ተቃዋሚዎችን እንዳይጠጋ የሚደረገው ሴራ እንዲቆም ማድረግ፡፡
5. በሃገራችን የሕግ የበላይነትና የዳኝነት ነፃነት እውን ይሆን ዘንድ አስፈላጊውን ማሻሻያን ለውጥ ማድረግ፡፡
በግንቦት 2002ቱ ምርጫና ከዚያም በፊት ኢህአዴግ በፈፀማቸው ጥፋቶችና በደረሰብንም ጥቃቶች በመመረርና በመቆጨት የሀገራችንን መፃኢ እድል በሚወስነው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ጉዳይ ላይ አኩርፈን ዳር መቆም አንችልም፡፡ በመሆኑም ከፍ ብለው በተዘረዘሩት በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ላይ ኢህአዴግ ለፈጠራቸው እጅግ አደገኛ ክስተቶች መፍትሔ እንደሚሆኑ መድረክ ባመነባቸው አምስት አበይት ጉዳዮች ላይ ድርድርና ውይይት ወሳኝ ነው በሎ መድረክ በጽኑ ያምናል፡፡
ስለሆነም፡-
1. ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ይህንን መድረኩ የነደፈውን የድርድርና የውይይት አጀንዳ በመደገፍ ውጤት ለማስመዝገብ የእንቅስቃሴው አካል እንዲሆኑ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
2. መላው ሕዝባችን በግንቦት 2002ቱ ምርጫ ድምፁን የመነጠቁና የመዘረፉ ቁጭትና ንዴት፣ እንዱሁም በተሰነዘረበት ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የሚታወቅ ቢሆንም የዚህ አይነቱ ኢ-ሕገመንግስታዊና ሕገ ወጥ ክስተት እንዳይደገም ኢህአዴግን መድረክ ወዳስቀመጠው ድርድርና ውይይት እንዲገባ በሁለንተናዊ መልኩ በሚያደርገው ተሳትፎ ጫና ሊፈጥርበት ይገባል እንላለን፡፡ ለዚህም በመድረኩ ፖለቲካዊ አመራር ዙሪያ በመሰባሰብ ወሳኝ ሚና የመጫወቱን አስፈለጊነት እናስገነዝባለን፣ በቸልታ ማየት ሀገራችንን ወደ አንድ ፓርቲ ፍፁማዊ አምባገንነት ይዟዋት እየገባ እንደሆነም ማሳሰብ እንወዳልን፡፡
የመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ወገኖቻችንን እንኳን ለ143ዐኛ ኢድ አልፈጥር በዓል በሠላም አደረሳችሁ እንላለን፡፡
በመጨረሻም፣ አዲሱ አመት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የሚደረገው ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ወደላቀ ደረጃ የሚያድግበት ወቅት እንዲሆን እየተመኘን፣ መላውን ህዝባችንን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ በማለት ልባዊ መልካም ምኞታችንን እንገልፃለን፡፡
እንኳን አደረሳችሁ! እንኳንም አደረሰን!
የኢትዮጵያ ፌዴራል ዴምክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)
ጳጉሜ 4 ቀን 2002 ዓ.ም
አዲስ አበባ