የኢትዮጵያን ባንዲራ በማጥላላት ታሪኩ የሚታወቀው የወያኔ አገዛዝ “የባንዲራ ቀን” ለማክበር ደፋ ቀና ማለት ጀምሯል
በአንድ ወቅት ከዱቄት መቋጠሪያ ጨርቅ ያለፈ ጥቅም ወይም ክብር እንደሌለው በአደባባይ ይናገር የነበረው ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ከጥቂት አመታት ወዲህ የህዝቡን ልብ ለማማለል ይረዳኛል በሚል እምነት ለአገሪቱ ነጻነት ምልክት የሆነውን ባንዲራችንን አፍቃሪ መስሎ ለመታየት የባንዲራ ቀን ማክበር መጀመሩ ይታወቃል።
የወያኔ አገዛዝ በ1997ቱ ምርጫ የኢትዮጵያን አንድነት ባቀነቀኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከተሸነፈ በኋላ እራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ ቡድን ለመቅረጽ እያደረጋቸው ካሉት ሙከራዎች ውስጥ አንዱ የባንዲራ ቀን መሰየም ነበር። በዚህም አኳኋን አገዛዙ በመጪው መስከረም 10 ቀን “የባንዲራ ቀን” ለማክበር በተሾመ ቶጋ መሪነት ደፋ ቀና እያለ መሆኑ ታውቋል። በየአካባቢው በርእሱ ላይ እንዲሰብኩ የታዘዙት የአገዛዙ ካድሬዎች የባንዲራን ቀን ማክበር ወጣቶች አገራቸውን እና ባንዲራቸውን እንዲወዱ እንደሚያደርጋቸው ከቀበለ ቀበለ እየተዘዋወሩ መስበክ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የግንቦት 7 ድምጽ የአዲስ አበባ ዘጋቢ መጪውን በዓል በሚመለከት ተዘዋውሮ ካናገራቸው የመዲናይቱ ነዋሪዎች አንዱ፥ “እኛ አገራችንን የምንወደው እነሱ ስለነገሩን አይደለም። ባንዲራችንን ባጥላሉበት ዘመንም አገራችንን እንወድ ነበር፤ አሁንም እንወዳለን፤ ወደፊትም እንወዳለን። ይህ በደማችን ውስጥ ያለና መቼም ቢሆን ከልባችን ሊወገድ የማይችል ነገር ነው፤” ብለዋል።