ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ በኢትዮጵያው አገዛዝ ላይ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሆነ የቀድሞ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ አቶ አሰግድ ተፈራ ተናገረ

የቀድሞ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረውና በአሁኑ ሰዓት በውጭ አገር በስደት ላይ የሚገኘው አቶ አሰግድ ተፈራ ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ በወያኔ አገዛዝ ላይ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሆነ ከግንቦት 7 ድምጽ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ገልጿል።

ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ በ1997ቱ ምርጫ የወያኔን አገዛዝ በግልጽ የደገፈ ከመሆኑም ባሻገር፤ ዘረኛው አገዛዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን ካስጨፈጨፈ በኋላም ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ይታወቃል። ወያኔ በየካቲት 1998 31ኛ አመት የልደት በአሉን ሲያከብር፣ ግለሰቡ 5.5 ሚሊዮን ብር ለዘረኛው ቡድን በስጦታ ማበርከቱ ይታወሳል። ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከወርቅ ማእድን አንስቶ የበርካታ መሬት ይዞታዎች ባለቤት እንደሆነ ይታወቃል።

አቶ አሰግድ ተፈራ ግለሰቡ ከወያኔ ጋር ያለው ግንኙነት ከጥቅም ትስስር ያለፈ እንደሆነ በመጠቆም፤ “ኢትዮጵያን የሚመራት ሼክ መሃመድ ነው” ብሏል። ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚገልጡት፥ አዜብ መስፍን እና ስብሃት ነጋ በህወሃት ውስጥ በሚያደርጉት ሽኩቻ፤ ሼክ አላሙዲ ጉልበት ካለው የአዜብ መስፍን ጎራ በመሰለፉ ለጊዜውም ቢሆን ከፍተኛ ሃይል ለማግኘት ችሏል።