የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት ሃገርን እየጣሉ መኮብለላቸውን ቀጠሉ

በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለገሰ ዓለሙ ከሁለት ሣምንታት በፊት ለስብሰባ ከፍትሕ ሚኒስትሩ ብርሃን ኃይሉ ጋር ለስራ በሚል አሜሪካ ሄዶ የነበረ ሲሆን ወደ ሃገር ሳይመለስ በዚያው መቅረቱን ለአገዛዙ ቅርበት እንዳለው የሚታወቀው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገበ።

እንደ ሪፖርተር ዘገባ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ የፍትህ ሚኒስትር ብርሃንና ለገሰ ብቻ ለስብሰባው ሄደው እንደነበር፣ ባለስልጣናቱም የሄዱበትን የስብሰባ አጀንዳ ሳያውቁ ከአሜሪካ ከፍተኛ የሕግ ኤክስፐርቶች ጋር እየተገናኙ ለተወሰኑ ቀናት ሲወያዩ የቆዩ ሲሆን ዳይሬክተሩ ዘመዶቸን ጠይቄ እመጣለሁ በማለት ለሚንስትሩ ከነገረ በኋላ በዚያው መቅረቱ ታውቋል::

ለገሰ ዓለሙ ቀደም ብሎ የኦሮሚያ ክልል ዳኛ ሆኖ በማገልገል ላይ እያለ በ2000 ዓ.ም. ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ተዛውሮ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የለውጥ አመራር ማስተባበሪያ ኃላፊና አሁን ደግሞ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኖ እየሠራ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።

በዘረኛው የወያኔ አምባገነናዊና ግፈኛ አገዛዝ እየተማረሩ ሃገራቸውን ጥለው የሚኮበልሉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እጂግ በርካታ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አገዛዙን በሃላፊነት ቦታዎችና የተለያዩ የስልጣን ርከኖች ያገለገሉ ባለስልጣናት ይህን የስደተኝነት ጎራ እየተቀላቀሉ መምጣታቸው በስፋት ይታወቃል። ሆኖም ስደቱን ከተቀላቀሉ ቦኋላ ከፊሉ ከወያኔ ጋር በነበረበት ሰዓት ተባባሪ በመሆን በሰራው ወንጀል አፍሮ አንገቱን ደፍቶ ለመኖር የሚመርጥ ሲሆን አንዳንዱ ትቶት በመጣው ቤተሰቦቹ ላይ ወያኔ እርምጃ ይወስዳል በሚል ስጋት አደባባይ ወጥቶ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል ለማጋለጥ ድፍረት ሲያጡና ሲያወላውሉ ይስተዋላሉ።