ከስራ የተባረሩ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሰራተኖች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸው ታወቀ
ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ከተቀየረ በኋላ በርካታ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ከስራቸው እንዲሰናበቱ የተደረጉ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን እነኝህ ከስራ የተባረሩ ሰራተኖች ከነቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የጥቃቱ ሰለባ ሰራተኞች ገልጸዋል።
አንዲት ለገሃር በሚገኘው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ጽ ቤት በጸሃፊነት ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ የስራ ተፈናቃይ እንደገለጹት ቴሌ ከጸሐፊ እስከ ከፍተኛ ክፍል ኃላፊነት የሥራ ደረጃ የደረሱ የበርካታ ዓመታት የስራ ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች ማባረሩንና ሁሉም ለማለት በሚቻል ደረጃ ቤተሰብና በርካታ ልጆችም ያሏቸው በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ላይ እንደወደቁ በምሬት ገልጸዋል:: ወይዘሮዋ እንደገለጹት፣ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ ቴለኮም ይቀየራል የሚል ወሬ ሲናፈስ ጀምሮ አሁን የደረሰባቸው እጣ ፈንታ ሊደርስባቸው እንደሚችል ስጋት እንደነበረባቸው፣ ከገለጹ በኋላ፣ የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ተብየው በተለያየ አጋጣሚና በተወካዮች ምክር ቤት ‹‹አንድም ሠራተኛ ሥራውን አያጣም፤›› በሚል ተናግሮ እንደነበር እንደማይዘነጉት ገልጸዋል::
በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን እውቀት በመጠቀም ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ እንደነበር የተናገሩት ወይዘሮ፣ ሚኒስትር ተብየው በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት የገባው ቃል ታጥፎና፣ የሥራ ዋስትና መብታቸውን በሚጥስና ፍፁም ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከሥራ መባረራቸው ፣ ሐዘናቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል::
በመጨረሻም ኢትዮ ቴሌኮም የወሰደው ዕርምጃ በመላው አገሪቱ የሚገኙትንና በሺዎች የሚቆጠሩ የድርጅቱን ሠራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ የሚባል ችግር ውስጥ የጣለ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ፣ ከሥራ ገበታቸው ሊያፈናቅላቸው የቻለው ምክንያት ምን እንደሆነ ሳይነገራቸው በደፈናው ‹‹ተሰናብታችኋል›› መባላቸው ዘረኛውና ግፈኛው የወያኔ አገዛዝ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ገደብ ያጣ በደል ያመለክታል በማለት ተናግረዋል::
በተመሳሳይ መልኩ አንድ የአስተዳደር ክፍል ሰራተኛ ቴሌ የሚከስር መሥርያ ቤት ሳይሆን በየዓመቱ ትርፉ እየጨመረ የሚሄድ መስሪያ ቤት በመሆኑ ያለውን ሠራተኛ ማባረር ሳይሆን ተጨማሪ መቅጠር እንደሚችል በግልጽ እየታወቀ ሕገወጥ በሆነና የግል ፍላጐትና ጥቅም ላይ ተመስርቶና ፣ አሠራሩም በጎሳ፣ በድርጅት አባልነት፣ በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ መፍትሄው ከዚህ የወያኔ ኢህአዴግ አገዛዝ ልንላቀቅ በምንችልበት መንገድ ላይ መሳተፍና የበኩላችንንም አስተዋጽኦ ማድረግ ብቻ ነው ማለታቸው ታውቁአል::
ቴሌ ውስጥ በነባርም ሆነ በአዲስ ተቀጣሪነት የተመደቡት ሠራተኞች ከተባረሩት ሠራተኞች በምን መመዘኛ ተሽሎ አንደተገኘ ግልጽ ካለመሆኑም በላይ፣ በትምህርት ዝግጁነት፣ በሥራ ልምድ፣ በሥነ ምግባርና በሥራ አፈጻጸም ብቃት ብልጫ ያላቸው ሠራተኞች ሳይመደቡ በሁሉም ነገር ዝቅተኛ ነጥብ ያላቸውና በዕድሜ የገፉ ሠራተኞች ሳይቀር መመደባቸው ታሪክ ወደፊት የሚያወጣው ነገር ይሆናል በማለት የአስተዳደር ክፍል ሰራተኛው ተናግረዋል::
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በቅርቡ ከወታደራዊ ሃይል አሰናበትኋቸው ያላቸውን ጄነራሎች ሳይቀር በኢትዮ ቴሌ ኮም መስሪያ ቤት ውስጥ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች መመደቡና እነኝህም ጄነራሎች የትግራይ ብሄር ተወላጆች እንደሆኑ ቀደም ብለን መዘገባችን ይታወሳል::