መለስ ዜናዊ የወለደው ርሃብ!!!
ከዝግጅት ክፍላችን፤
በቅርቡ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ርሃብ አለ እንዴ ተብሎ ተጠይቆ ሳያንገራግር የሚከተለውን መልስ ሰጠ፤
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ርሃብ ሳይሆን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው”። አለ ሌባ ጣቱን ወደላይ ቀስሮ።
መለስ ዜናዊ ይህን መልስ በሰጠበት ወቅት ኦጋዴን ውስጥ ህጻናት፤ ጎልማሶችና አዛውንቶች እንደቅጠል ይረግፉ ነበር። እንዲህ ህዝቡ በርሃብ ሲያልቅ የረድኤት ድርጅቶች ወደ ኦጋዴን ገብተው በርሃብ የሚረግፈውን ህዝብ እንዳይታደጉ በመደረጉ ኦጋዴን ሰው አልባ ሆነች።የኦጋዴን ህዝብ ዘር ሆን ተብሎ እንዲጠፋ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ተፈጸመበት። ይህ ሁሉ ጭካኔ በመለስ ዜናዊ አመራርና በዙሪያው በተሰበሰቡ ሆድ አደሮች አማካኝነት መፈጸሙን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልብ ሊለው ይገባል።
የርሃቡ ነገር በኦጋዴን ብቻ ሳይወሰን በኦሮሚያ፤ በደቡብ፤በአማራ፤ በጋምቤላ ዘልቆ አገሪቷን ሁሉ አዳረሰ። መለስ የርሃብተኞችን ቁጥር እየደበቀ ቢሰነብትም በያዝነው ዓመት 4 ነጥብ አምስት ሚሊዮን አስቸኳይ ነፍስ አድን የምግብ እርዳታ የሚጠባበቁ ርሃብተኞች እንዳሉ ተገልጿል። እነዚህ በአደባባይ የወጡና ዓለም ያወቀቻው ሲሆኑ በየጎጆው በጠኔ የሚሞቱትን ህጻናትና አዛውንቶች ቤቱ ይቁጠራቸው።
አገሪቷ መለስ ሰራሽ ችጋር ውስጥ ከመግባቷ በፊት መፍትሄ እንፈልግለት ያሉ ዜጎችን መለስ ዜናዊ በአሸባሪነት እየከሰሰ የቻለውን እየገደለ ያልቻለውን ደግሞ የሞት ፍርድ እየፈረደ በክፍ አቋሙ ጸንቷል። ዜጎቻችን የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በየሜዳው ሲወድቁ እያየ ”ርሃብ የለብንም ችግሩ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው መጠነኛ ገንዘብ ካገኘን ችግሩ ይቃለላል” ብሎ ተሳለቀ። መለስ ዜናዊ እንዲህ ያለውን ነገር አስቦና አውቆ ሲናገረው በዙሪያው የተሰበሰቡ ሆድ አደሮች ደግሞ ሳያስቡ ያጨበጭቡለታል። መለስም ክፍ ሃሳቡ ዋጋ ያገኘ እየመሰለው በኢትዮጵያዊያን ስቃይ ሃሴት አድርጎ እስከ ዛሬ ዘለቀ።
መለስ ዜናዊ “ገንዘብ ካገኘን ችግሩ ይቃለላል” ሲል በረሃብተኛው ሥም በየአመቱ ከምዕራባዊያን ለጋሽ አገሮች የሚጎርፍለትን ያልደከመበት ገንዘብ መዝረፍ ልማዱ በመሆኑና አንዱም የዝርፊያ መንገድ በእርዳታ የሚገኝ ገንዘብ መሆኑን ስለሚያውቅ በርሃብ የሚያልቀውን ህዝቡ ሊታደግ የሚችል ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ ከመጠየቅ ፈንታ ጥሬ ገንዘብ ቢሰጠኝ ሲል ተመኘ። ለርሃብተኛ የሚላከውን እርዳታ መዝረፍ አሁን የጀመረው አዲስ ነገር ሳይሆን ያደገበት የኖረበትና የለመደው ዓመሉ ነው።መለስ ገንዘብ እስካስገኘና ስልጣን ላይ እስካቆየው ድረስ በዝህች ምድር ላይ የማይፈጽመው የወንጀል ዓይነት እንደሌለ የኋላ ታሪኩ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። የትግራይ ህዝብ እንደቅጠል በሚረግፍበት በዚያ ክፍ ወቅት የተገኘውን የምግብ እርዳታ ሽጦ የቻለውን በግል ባንኩ ቀሪውን ደግሞ ዘረኛና ዘራፊ ቡድኑን ይበልጥ ለማደረጃት መጠቀሙን ታሪክ መዝግቦ ይዞታል።
መለስ ዜናዊና አስተዳደሩ ርቀው ማየትና የነገውን ማሰብ የሚችል የአእምሮ ልቀት የሌላቸው በመሆኑ አገሪቷን እንዲህ ያለ ችጋር ውስጥ ዘፍቀዋታል። የመለስ ዜናዊ እኩይ አስተሳሰቡ ካልተተገበረ ቁጥሩ 12 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አይደለም ኢትዮጵያ ራሷ ከገጸ ምድር ብትጠፋ ግድ የሚለው ግለሰብ እንዳልሆነ ሥራዎቹ ያስረዳሉ። ለዚህም አባባል ምስክር የሚሆነው የተሳሳተ ፖሊሲውን እንዲቀይር ብዙ ግዜ ሲጠየቅ “በእኛ ሬሳ ላይ ታደርጉታላችሁ” እያለ ሲፎክር መኖሩ ነው”። የፍከራው ውጤት የሰው ልጆች እንደቅጠል እንዲረግፉ አደረገ።ኢትዮጵያም እንደገና ስሟ በርሃብ ተነሳ ኢትዮጵያዊያንም በያሉበት አንገታቸውን እንዲደፍ ሆነ።
አገሪቷ በእንዲህ ዓይነት ችጋርና ውረደት ውስጥ እያለች ሥልጣኑን እስከወዲያኛው ማደላደል ተቀዳሚ ተግባሩ የሆነው ይህ ግለሰብ፤ ይባስ ብሎ ለአገር ውስጥ ደህንነትና ለመከላከያ ሃይሉ ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት መድቧል። ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጎም ሁለት መቶ ዘመናዊ የጦር ታንኮችን ገዝቷል።ይህም ግዥ ዩክሬን ከ15 ዓመታት ወዲህ የሸጠችው ከፍተኛው ሽያጭ ሁኖ ተመዝግቦላታል።በዚህም ብር ዩክሬን ህዝቧን ትመግብበታለች። ኢትዮጵያዊያንም በርሃብ ያልቃሉ። ቢያንስ ላለፉት 10 አመታት ያህል በያመቱ ከ12 ሚሊዮን ያላነሰ ርሃብተኞች ያላት አገር ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥታ የጦር ታንኮች ስትገዛ ማየት የችግሩ ሰለባ ለሆነው ለኛ ለኢትዮጵያዊያኑ ብቻ ሳይሆን ስንዴና ጥሬ ገንዘብ የሚለግሱንን ባዕዳን ሳይቀር አስገርሞአል። አገሪቷ የሚያሰጋት የውጪ ጠላት ሳይኖራት ከረሃብተኛው ጉሮሮ ነጥቆ 200 ታንኮችን መሸመት፤ ከጥጋባቸው ብዛት ማመዛዘን ተስኖአቸው ጦር አውርድልን እያሉ ነጋሪት በመጎሰም ላይ ያሉትን መለስና ዘራፊ ቡድኑን የደረሱበትን እብሪት ደረጃ አመልካች ነው። ሁላችንም እንደምንረዳው እነዚህ ቡድኖች ለዚያች አገር ዳር ድንበር መከበርና ክብሯን ለማስጠበቅ ብለው ታንኮችን እንዳልገዙ የተሰወረ አይደለም። ይህ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጥቶባቸው የተሸመቱ ታንኮች ወያኔ ራሱ በፈጠረው የኑሮ ውድነት የተዳከመው ህዝባችን ብሶት መሮት በአገዛዙ ላይ እንዳያምጽ በፍርሃት ለማርበድበድና ለማሸበር ታሳቦ እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን። መለስ የአገር ሉአላዊነትእና ዘላቅ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችለው የአገር ፍቅር ስሜት እንደሌለው፤ ሂሊናውም በጥላቻ የታወረ መሆኑ ግልጽ ነው። ፋይዳ ለሌለው ጦርነት በባድሜ የከፈልነውን መስዋዕትነት ምን ጊዜም አንረሳውም። ወገኖቻችን ተፈናቅለው ለሱዳን ተቆርሶ ከተሰጠው ሰፊ መሬታችን በተጨማሪ ለህንድና ለአረብ ከበርቴዎች እየታደለ ያለው ለም የአገራችን ክፍል ጉዳይ እጅግ ያንገበግበናል። መለስ የጦር ታንኮችን ከመግዛት ይልቅ የእርሻ ታንኮች ቢገዙ አይሻልም ነበር ወይም ደግሞ የጦር ታንኮችን ከመግዛት ይልቅ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን አስቆፍሮ ህዝቡን ከችጋር ለማላቀቅ ጥረት ማድረግ አይሻልም ነበረ ወይ ተብሎ ቢጠየቅ የጠላት ወሬ ነው ይለናል እንጂ እንደ አንድ አገር መሪ ትኩረታችንን አይጋራንም ወይንም ተገቢውን መልስ አይሰጠንም።መልስ የመስጠት ግዴታም አለብኝ ብሎ አያምንም።
እንደ ፈርኦን ልቡ የደነደነው መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያችን ምንም ዓይነት በጎ ምኞት ለህዝቡም ፍቅር የሌለውና አርቆ ማሰብ የሚችል አእምሮ የጎደለው ግለሰብ በመሆኑ ህዝባችን ተራበ የሚሉትን ዜጎች አሸባሪዎች ይላል እንጂ በበጎ አይመለከትም። እግዜር የፈጠረው ሰው እንዲህ በየሜዳው እንደምናምንቴ ነገር ወድቆ ሲቀር መለስ ቅንጣት ታክል ልቡ በሃዘን የሚነካ አልሆነም። በትንሹ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ በርሃብ አለጋ እየተገረፈ ባለበት በዚህ ወቅት መለስና ቡድኑ 8.4 ቢሊዮን ዶላር ከአገሪቷ አውጥተው በውጭ ባንኮች መደበቃቸው እነ መለስ ዜናዊ ማን እንደሆኑ ያሳያል። በአገራችን ታሪክ እንዲህ ዓይነት ዝርፊያ ሲፈጸም የመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት በብቸኝነት ሲጠቀስ ይኖራል። ከመለስ ዜናዊ በፊት የነበሩ እንዲህ ዓይነት ዝርፊያ መፈጸማቸውን አልሰማንም ከመለስ በኃላ የሚመጣውም መንግስት እንዲህ ዓይነቱን ዝርፊያ ለመፈጸም እድሉ አይኖረውም። መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ እስከ ቆየ ድረስ ግን እንዲህ ያሉ አስገራሚ ዝርፊያዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ችጋሩም እየተባባሰ ይሄዳል እንጂ አይሻሻልም።
አገራችን እንደገና ስሟ በርሃብ ተነስቶ በሚወራበት ዘመን አዜብ መስፍን ወይም አዜብ ጎላ በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያዎች ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ አድርጋ ሸመታ ማካሄዷን የስፔኑ ጋዜጣ አጋልጧል። በዚህም በዓለም አሉ ከሚባሉ አባካኝ ሴቶች ተርታ ተሰልፋለች። ህዝቧ በርሃብ እያለቀ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥታ ጫማና ልብስ ስትገዛ ሰው ምን ይለኛልን የማታውቅ ጉድ በኢትዮጵያችን ላይ መንግሷ በአገራችን ውስጥ አሳፋሪ የታሪክ ክስተት በመሆን ተመዝግቧል።
እነዚህ ሰዎች በአገራችንና በህዝብ ላይ እየፈጸሙ ያሉት ነገር የወዳጅ ሳይሆን የጠላትነት ነው። ዜጎች የእርሻ መሬት አጥተው በየከተማው ሲንከራተቱ መለስና ቡድኑ ለም መሬቶችን ብቸኛ ዓላማቸው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ለአረብና ለህንድ ነጋዴዎች ይሸጣሉ። በዚህም ተጨማሪ ተንከራታች አርሶ አደሮችን ይፈጥራሉ። ያስርቡታል፤ እንዲታረዝ ያደርጉታል፤ ቤትና መኖሪያ አልባ አድርገው በገዛ አገሩ ስደተኛ እንዲሆን ሜዳ ላይ ይጥሉታል። ይሄ ነው የነመለስ ዜናዊ ልማትና ብልጽግና።ይሄን መሰል ተግባራቸው ነው እንደጠላት የሚያስቆጥራቸው።
መለስ ለዝሪፊያው እንዲመቸው ሳያስቡ የሚያጨበጭቡለትን ሰዎች በዙሪያው አሰልፏል። ሳይስቡ የሚደግፉት ቡድኖች እያሰበ ወንጀል ከሚሰራው መለስ ዜናዊ ጋር በታሪክ ፊት እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። እነዚህ ተባብረው አትዝረፍ የሚላቸውን አንደበት ለመዝጋት ህግ አውጥተዋል ብዙ ገንዘብም አፍስሰው ነጻ ሚዲያዎችን አፍነዋል። ከችጋር ለመላቀቅ ነጻ አስተሰሰብ ያስፈልገናል ያሉትን አሸባሪ ብለዋል። ለርሃቡ መብትሄ አለን የሚሉትን ሁሉ ጠላቶቼች ሲሉ ጠርተዋቸዋል። እነዚህ ቡድኖችና መለስ ዜናዊ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው።የሞራል ዝቅተትና ዝርፊያ በዚያች አገር ውስጥ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዲያበቃ መለስ ዜናዊ ከስልጣኑ መባረር አለበት።
እንዲህ ጥቂቶች ተደራጅተው አገሪቷን ሲያዋርዱና የብዙሃኑን ስቃይ ሲያበዙ እያየ ዝም የሚል እንደምን ሁኖ ሰው ሊባል ይችላል? ሰው ማለት በወገን ላይ የሚደርስን ግፍንና በደልን ራስ ላይ እንደደረሰ አድርጎ መቆርቆር ማለት ነው። የመጽሃፍ ቅዱሱ ሙሴ የወንድሞቹን በደል አይቶ ዝም ባለማለቱ እግዚአብሄር እራሱን እስከሚገልጽለት ድረስ ለክብር አብቅቶታል። ኢትዮጵያዊም እግዚአብሄር እንዲያከብረው በወገኖቹ ላይ የሚፈጸመውን በደል እያየ ዝም ማለት የለበትም።
ነገ ልትፈጠር የምትችለውን መልካም አገር እያሰብን በጋራ ጠላታችን ላይ በአንድነት መነሳት ለነገ የምንለው ተግባር አይደለም።ከትላንትናዋ ኢትዮጵያ የተሻለችና ለሁላችንም የምትሆን አገር መፍጠር የእኛ ሥራ ነው። በልዩነቶቻችን መካከል ያሉ አንድነቶቻችንን ተንከባክበን ማሳደግ ይገባናል። መለስ ዜናዊ እንደሚያድረገው ልዩነቶቻችን የመለያያችን ምክንያቶች ሳይሆኑ የውበታችንና የአንድነታችን ጥንካሬ መገለጫዎች እዲሆኑን ኑ! አብረን ለኢትዮጵያ ትንሳኤ እንስራ ። ርሃብንና ችጋርንም እናጥፋ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!