የፕሬዝዳንት ኦባማ የዉጭ ርዳታ የማሻሻያ ፕሮግራም አካል የሆነ አለም አቀፍ የጋራ ትብብር ድርጅት ተቋቋመ

የአሜሪካንን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ በየትኛውም አለም ክፍል ካሉት አፋኝና ጨቋኝ የአምባገነን መንግሥታት ጋር ተባብሮ መሥራት የውጪ ፖሊሲው አካል የነበረው የአሜሪካ መንግሥት፤ ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ወዲህ በአለማችን ላይ እያየለ የመጣውን የነጻነት ትግል ለመደገፍ በሚያስችል ሁኔታ እንዲሻሻል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ፍንጮች ያመለክታሉ።

ሰሞኑን የኦባማ አስተዳደር ይፋ ባደረገው መግለጫ፤ የመልካም አስተዳደር አለመኖር በተለያዩ አገሮች እያስከተለ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭቶች ለማስወገድ እንዲረዳ Open Government Parnership የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት የተቋቋመ ሲሆን አላማውም ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደርን ከአሜሪካ ጋር የጋራ ትብብር በሚያደርጉ አገሮች ውስጥ ለማስፈን እንደሆነ ታዉቋል። ይህ አዲስ የተቋቋመው አለም አቀፍ የጋራ ትብብር ድርጅት የፕሬዝዳንት ኦባማ የዉጭ ርዳታ የማሻሻያ ፕሮግራም አካል እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን መንግስታት ሁሉ የዚህ የጋራ ትብብር ድርጅት አባል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

ድርጅቱ በድረ ገፁ እንዳሰፈረዉ ግልፅነትን ለማስፈን፡ የዜጎችን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ፤ ሙስናን ለመዋጋት፤ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር ድርጅቱ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እና አገር እንመራለን የሚሉ መንግሥታት እነዚህን እሴቶች በየአገራቸው መተግበራቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸውና ከአሁን ቦኋላ መንግስታት በዚህ መመዘኛ እንደሚመዘኑ አስታውቆአል።

አድስ የተቋቋመውን ይህንን ድርጅት ዩናይትድ ስቴትስና ብራዚል በጋራ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ሲሆን 8 መንግስታትና ዘጠኝ የሲቪል ማህበራት በበላይ አስተባባሪነት የሚያስተዳድሩት እንደሆነም ተገልጾአል። ድርጅቱን በበላይ አስተዳዳሪነት የሚመሩት አገሮች በመጪዉ መስከረም ተገናኝተዉ የድርጅቱን ድንጋጌዎች ተቀብለዉ ሃላፊነታቸዉን እንዴት እንደሚወጡና የስራ መርሃ ግብራቸዉን ከነደፉ በሁዋላ ስራ ላይ ማዋል እንደሚጀምሩ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የድርጅቱን ድንጋጌ በመቀበል፤ እቅዳቸዉን ተግባራዊ ማድረጋቸዉ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ማረጋገጫ የሚሰጡ መንግስታት፤ በህዝብ ምክክር የዳበረ የስራ እቅዳቸዉን በመጋቢት 2012 ብራዚል በሚካሄደዉ ስብስባ ላይ በማቅረብ በአባልነት ሊመዘገቡ እንደሚችሉም ተጠቅሷል።

የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የውጪ ፖሊሲ አካል ይሆናል የተባለው አለም አቀፍ የጋራ ትብብር ድርጅት ከአገራት ጋር የሚኖረው ግንኙነት ግልፅነት፤ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በተግባር ከሚፈፅሟቸዉና በገለልተኛ ወገን ፊት ሊያረጋግጡ ከሚችሏቸዉ ስራዎቻቸዉ ጋር የተቆርኘ እንደሚሆንና የሚሰጡ እርዳታዎች አገሮችን ለዲሞክራሲ ለዉጥ ቁርጠኛ እንዲሆኑ የሚያስገድድ መሆኑ ታምኖበታል።