ወያኔ በሥራ ዋስትና አስገድዶ የኢህ አደግ አባል ያደረጋቸው የመንግሥት ሠራተኞች ድርጅቱ የሚጠብቅባቸውን የአባልነት ግዴታ ላለመወጣት እያንገራገሩ ነው ተባለ

ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በምርጫ 97 በህዝብ መተፋቱን ከተገነዘበ ወዲህ በመላው አገሪቱ የሚገኙትን አብዛኛውን የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ዋስትና እና የደረጃ ዕድገት ሥም እያስፈራራ አባል ያደረገ ቢሆንም አባልነታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ከመጣው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የሚታደጋቸው ሆኖ ባለመገኘቱ በርካቶች የአባልነት ግዴታቸውን እንወጣም ማለት ከመጀመራቸውም በላይ ወርሃዊ የአባልነት ክፍያቸውንም መክፈል እንዳቆሙ የግንቦት7 ዘጋቢ የወያኔን የውስጥ ምንጮች ጠቅሶ ከአዲስ አበባ ከላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎአል።

እንደ ውስጥ ምንጮቻችን መረጃ በአገሪቱ ውስጥ ሥር እየሰደደ በመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ምክንያት ከመንግሥት የሚከፈላቸው የወር ደመወዝ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መሠረታዊ ፍጆታ ከወር ወር የማያደርስ ሆኖ እያለ ፤ ቀደም ሲል ይፋ በሆነው የወያኔ 5 አመት መርህ ዕቅድ ውስጥ እንኳ ላልተካተተ የአባይ ግድብ ግንባታ የወር ደመወዛችሁን አዋጡ መባሉና በጉልበት ተግባራዊ መደረጉ የብዙዎቹን የኢህአደግ ተራ አባላት እጅግ አስቆጥቶአል።

የሥራ ዋስትና ለማስጠበቅና በየመሥሪያቤቶቹ የሚሠጡትን ደረጃ እደገትና የትምህርት ዕድል የመሳሰሉትን ጥቅማጥቅሞች ለማግኘት ሲሉ ድህረ ምርጫ 97 ወያኔ በከፈተው ጅምላ የአባላት ምልመላ ኢሃደግን ተቀላቅለው የነበሩት እነኚህ ዘጎች በሥር ዓቱ ላይ ያላቸው ቅረታና ጥላቻ ሥር እየሰደደ ከመምጣት አልፎ ወያኔ ኢህ አደግ በሚጠራው የአባላት ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንብታቸውን እየገለጹ ነው።

በአባላቱ እምቢታ የተደናገጠው የወያኔ ኢህ አደግ አመራር የአባልነት ድርሻቸውን አንወጣም በማለት በሚያንገራግሩት ላይ ከደመወዝ ቅጣት እስከ ከሥራ ማባረር ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ እየሰጠ መሆኑን ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ ተጠርቶ በነበረው የኢህአደግ ስብሰባ ላይ አንገኝም ባሉት መምህራን ላይ የተወሰደው የደመወዝ ቅጣት የኢህ አደግ አመራር የደረሰበትን ኪሳራ ያመለክታል ያለው ዘጋቢያችን፤ መምህራኑ እያንዳንዳቸው የ8 ቀን ደመወዛቸውን መቀጣታቸውን የሚገልጽ የቅጣት ደብዳቤ እንደደረሳቸውና በአባልነታቸው የማይቀጥሉ ከሆነ ከሥራ እንደሚባረሩ እንደተገለጸላቸው ማረጋገጡን አክሎ ገልጾአል።

የመንግሥት ሠራተኞች የሆኑ የኢህአደግ አባላት እያሳዩ ባለው የባህሪ ለውጥ የተደናገጠው ፋሽስቱ መለስ ዜናዊ በሁሉም ክልሎችና ሥራ ዘርፎች ላይ ያሉት አባልት እንዲገመገሙ ትዕዛዝ በመስጠቱ ሌላ ዙር ግምገማ እንደተጀመረ ለማወቅ ተችሎአል።

በደርግ የመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዘመናት ለመኖር ብለው የኢሠፓኮ አባል ሆነው የነበሩ ሁሉ ስብሰባ ባለመሄድና ወርሃዊ ክፍያቸውን በአገባቡ ባለመክፈል የደርግን ውድቀት እንዳፋጠኑት የሚያስታውስ ዘጋቢያችን፤ በምርጫ 97 የታየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ያበረደ መስሎት የአባላቱን ቁጥር በአንዴ ከሰባት መቶ ሺ ወደ አምስት ሚሊዮን ያስመነደገው ወያኔ የእራሱን መቃብር እራሱ እየማሰ እንደሆነ ምልክቶች እየታዩ ነው ብሎአል።