ትኩረታችን በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ስርዓት ላይ ነው
ከዝግጂት ክፍላችን
ከጥቂት አመታት ወዲህ፣ ከዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ጋር በከፍተኛ ደረጃ በጥቅም እና በሙስና የተሳሰረ መደብ በኢትዮጵያችን መነሳቱ ሲወራ ቆይቷል። በተለይ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ በሙስና ሳይዘፈቁ እና ከወያኔ ጋር የጥቅም ትስስር ወይም የንግድ ሽርክና ሳይፈጥሩ ሃብት የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር እየተመናመነ እንደሆነ ይነገራል።
የአገዛዙን የድጋፍ ወይም የሽርክና ጥያቄ ያልተቀበሉ ነጋዴዎች በተፈበረከ ክስ ወደ እስር እንዲወርዱ፣ ከንግድ ሜዳ ተገፍተው እንዲወጡ ወይም ከአገር እንዲሰደዱ ሲደረግ ቆይቷል። የተቀሩት ግን በወያኔ የተጠየቁትን በማድረግ ንግዶቻቸውን እንደያዙ ለመቀጠል ወስነዋል፤ አገዛዙን ለማጠናከርም ተግተው ሲሰሩ ተስተውለዋል።
የወያኔን አገዛዝ በግልጽ ከሚደግፉት ነጋዴዎች ውስጥ አንዱ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የሳኡዲ ዜግነት ያለው ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ ነው። ለዚህ ጽሁፋችን መነሻ የሆነንም፥ የቀድሞ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረውና አሁን በስደት የሚገኘው አሰግድ ተፈራ ስለዚሁ ግለሰብ የተናገረው ነው። ጋዜጠኛ አሰግድ፥ “ኢትዮጵያን የሚመራት ሼክ መሃመድ ነው” ብሎናል። እኛም ይህንን ለመመርመር መረጃ ቃርሚያ ወጣን።
ሼክ መሃመድ አላሙዲ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ለወያኔ መቀስቀሱና፤ ዘረኛው ቡድን ዜጎችን ባስጨፈጨፈበትና የቅንጅት መሪዎችን በግፍ ወደ እስር በወረወረበት አመትም 5.5 ሚሊዮን ብር ለገዢው ቡድን በስጦታ መልክ ማበርከቱ ይታወቃል። ግለሰቡ በተለያዩ መንገዶች ለወያኔ ለሚፈጽመው ውለታም፤ በአገሪቱ ውስጥ ቁጥጥር በማይደረግበት ሁኔታ እንዳሻው እንዲነግድ ተፈቅዶለታል ይባላል።
አዲስ ነገር ኦንላይን የተባለው የመረጃ ድረ-ገጽ ከሶስት ወራት በፊት ባወጣው ዘገባ፤ አዜብ መስፍን እና ስብሃት ነጋ በህወሃት ውስጥ በሚያካሄዱት ሽኩቻ አላሙዲ ከአዜብ ጎራ መሰለፉን፤ እንዲሁም የአዜብ ጎራ የወያኔ የደህንነት ሃላፊ የሆነውን ጌታቸው አሰፋን እንደሚያካትት ውስጥ አዋቂ ምንጮቹን ጠቅሶ ገልጿል። በአዜብ እና በስብሃት ሽኩቻ ላይ ከዚህ ቀደም ባቀረብናቸው ዘገባዎች፤ አዜብ በተለያዩ ጊዜያት አሸናፊ ሆና መውጣቷን ጠቅሰናል።
ከበርካታ ወራት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ ከሼክ አላሙዲን የንግድ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ሙስናዎችን በሚመለከት ተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሲያወጣ፤ የጋዜጣው ባለቤት አማረ አረጋዊ ክፉኛ ተደብድቦ እንደነበር ይታወሳል። በርካቶች ሼኩ ወይም ለሱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ለዚህ ስራ ተጠያቂዎች እንደሆኑና፤ ይህም ግለሰቡ ያለውን ከፍተኛ ጉልበት ያሳያል ይላሉ።
ነገር ግን በህወሃት ውስጥ በሚደረገው ሽኩቻ የግለሰቡን አሰላለፍ አተኩሮ ለተመለከተ ሰው ስእሉ ግልጽ ነው። ከአዜብ ጋር የተሰለፈ በቀላሉ ጠላቶቹን ሊያንበረክክ የሚችልበትን ጉልበት ይኖረዋል። ይህንን በተመለከተ ያናገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝም፥ ግለሰቡ ለጊዜው ከዚህ አሰላለፍ የተወሰነ ጉልበት አግኝቶ እንደሆን እንጂ፣ ከወያኔ ቁጥጥር ውጪ ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም ብለውናል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ጦሩን ጨምሮ የመንግስት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ያለው ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ ቡድን እንደሆነ ጠንቅቀን ለምናውቀው ሁሉ ግልጽ ነው።
አዲስ ነገር ኦንላይን የሁለቱን ቡድኖች ሽኩቻ አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ላይ፤ ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ከሽኩቻው እንዴት እየተጠቀመ እንደሆነ አስረድቶናል። መለስ ሽኩቻው ህወሃትን እንደማይጎዳ እስከተረጋገጠ ድረስ አይኖችን ከሱ ላይ የሚያነሳ በመሆኑ ደስተኛ ነው። ሁለቱንም የደገፈ መስሎ በመቅረብም እነሱ ከስር ሲጫረሱ እሱ ከላይ ቁጭ ብሏል።
እኛ በዚህ መሰረታዊ ትርጉም በሌለው የወንበዴዎች ሽኩቻ መካከል ገብተን፤ ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች መሆናቸውን እያወቅን አንዱን የወንበዴ ጎራ ከሌላው ለይተን የማሳየት ፍላጎቱ የለንም። የአዜብ ቡድንም ሆነ የስብሃት፥ የአገራችንን ደም መጥጦ ልጆቻችንን ተስፋና እድል ፈንታ ሊያሳጣ የቆመው ዘረኛ አገዛዝ ስራ አስኪያጆች እና ዋና አጋፋሪዎች ናቸው።
ሼክ አላሙዲ እንደሆነ፥ ከወያኔ ፈቃድ እና ባርኮት ውጪ ምንም ሊያደርገው የሚችለው ነገር የለም። ወንጀል ሲፈጽም እና በሙስና ሲዘፈቅ ታይቶ እንደሆነ፤ አገዛዙ ስለፈቀደለት ነው። ይህ ሰው በወያኔ ምህረት ላይ ብቻ ተመክቶ የሚንቀሳቀስ ነው። አገዛዙ ቢፈልግ፥ በሙስና፣ ግብር ባለመክፈል፣ ወይም በሆነ ወንጀል አስሮ ሊከሰው ይችላል። ያ ባይሆን እንኳ በውጭ አገር ዜግነቱ ብቻ አንስቶ ቢያሽቀነጥረው ከልካይ አይኖረውም። በዘር ላይ በተመሰረተ አመራር የሚነዳና በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ያሰለፈ ጦር ያለው ወያኔ እንጂ ሼክ አላሙዲ አይደለም።
እንግዲህ ግለሰቦች ሁሉ ወንጀል መፈጸማቸው በማስረጃ ከተረጋገጠ፣ አንድ ቀን ነፃና ፍትሃዊ በሆነ ፍርድ ቤት ፊት መቆማቸው አይቀርም። ወቀሳና ሂስም ሊቀርባቸው አይገባም። ይሁን እንጂ፥ በአሁኑ ሰዓት ዋናው ችግራችን ስልጣንን በጉልበት ተቆጣጥሮ ያለው እና ሙስና እንዲስፋፋ ሆን ብሎ የሚሰራው ዘረኛና አምባገነናዊ ስርአት ነው። የኛም ትኩረት ከዚህ ስርአት ላይ እንዳይነሳ የዘወትር ጥሪያችንን እናቀርባለን።