ቅ/ሲኖዶስ እና ፓትርያሪኩ የአቡነ ያዕቆብ የመላው አፍሪካ አህጉረ ስብከት አስተዳደር እያስከተለ ለሚገኘው ጉዳት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡ ተጠየቀ

  • ለወራት በአ/አ የተቀመጡት ሊቀ ጳጳሱ ትላንት ምሽት ወደ ደ/አፍሪካ ተጉዘዋል
  • በሊቀ ጳጳሱ አስተዳደር የተማረሩና አስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ አቤቱታዎች ለውጭ ግንኙነት መምሪያውና ለፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት እየጎረፉ ነው

ከዚህ በታች የምናቀርበውና ‹‹የአቡነ ያዕቆብ ሲሞናዊነት[ስምዖናዊነት] ሲገለጥ›› በሚል ርእስ የተጠናቀረው መልእክት የደረሰን በኬንያ – ናይሮቢ ከሚገኙ ምእመናን ነው፡፡ መልእክቱ÷ የመላው አፍሪቃ አህጉረ ስብከትን የተመለከተ ዘገባ በጡመራ መድረኩ ለንባብ ከበቃበት ጊዜ ጀምሮ ከሚደርሱን በርካታ አስተያየቶች መካከል ለማለዘብ የተገደድናቸውንና በተለይ ሊቀ ጳጳሱን የሚመለከቱ ግልጽ የወጡ መረጃዎችንና ትችቶችን መልሰን እንድናጤናቸው፣ ደጋግመን እንድናጣራቸው አግዞናል፡፡

መልእክቱን መሠረት ያደረጉ ዋና ዋና ነጥቦችን በቅድሚያ ያስቀመጥን ሲኾን ምእመናኑ ከናይሮቢ ያደረሱን መልእክትም መጠነኛ ማለዘቢያ ተደርጎበት ተያይዞ ቀርቧል፡፡ ቁም ነገሩ÷ በቀደሙት ዘገባዎቻችን እንዳመለከትነው፣ ቤተ ክርስቲያናችን በብዙ በምትጠበቅበት የአፍሪቃ አህጉር ሐዋርያዊ ተልእኮዋ በምን ደረጃ እየተፈጸመ እንዳለ ለማሳየትና ከዚያም በመነሣት ለችግሮቹ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ ለተግዳሮቱም የሚመጥን የአገልግሎት ዝግጁነት እንዲኖር ለማትጋት ነው፡

 

ዐበይት የትኩረት ነጥቦች

  • የማጥመቅ ሥርዐታቸውና የሚታሙበት ጥንቆላ ለምእመናን እምነት፣ ጤንነትና ማኅበራዊ ኑሮ ፈተና ኾኗል፤ ይህን የሚቃወሙ ካህናትም በደል ይፈጸምባቸዋል፡፡
  • በአብያተ ክርስቲያን ቅጽር ማረፊያ ቤት እያለ በቀን 150 የአሜሪካን ዶላር የሚከፈልበትን ‹ገስት ሃውስ› እና የግለሰብ ቤት ለማረፊያነት መምረጣቸው ከአዋኪው የማጥመቅ ሥርዐታቸውና ከሚታሙበት የጥንቆላ ተግባር ጋራ ተያይዞ ለከፋ ሐሜትና ትችት ዳርጓቸዋል
  • አዲስ አገልጋዮችን በመቅጠር አመካኝተው ገንዘብ ለመቀበል ሲሉ በአገልግሎት ላይ ያሉ ካህናት አገልግሎታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ይገፋፋሉ፤ የሚቃወሟቸውን ካህናት ከምእመናን ያጋጫሉ፤ ምእመናንን በካህናት ላይ ያነሣሣሉ፡፡
  • የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ሳያውቀው በጎጠኝነትና ጥቅመኝነት ላይ ተመሥርተው ለሚፈጽሙት ቅጥር በአዲስ አበባ በደላላነት የሚያገለግሏቸው ቀሲስ ግሩም ታዬ ናቸው፡፡

*            *            *

  • በዑጋንዳ፣ ታንዛንያና ሌሎችም የአህጉሪቱ ክፍሎች አብያተ ክርስቲያን እንዲስፋፉ ለሚማፀኑ በጎ አድራጊ ምእመናን ቀናና አፋጣኝ ምላሽ አይሰጡም፤ ይልቁንም የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳደርን በመጋፋት ያለገደብ በሚጠይቁት የገንዘብ ወጪ አድባራቱን ለብኩንነት እየዳረጉ ማደኽየታቸ በፈጠረው ምሬት ከአንድነት መዋቅር የመለየት ስጋት የተጋረጠባቸው ነባር አድባራት አሉ፡፡
  • ይህ ምሬትና ስጋት ከተጋረጠባቸው አድባራት አንዱ የናይሮቢ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የደብሩን ይዞታ ንብረቷ ያደረገችው በሦስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አስተዳደር ወቅት ነው፡፡ የባዕለጸጎች መኖርያ ነው በሚባለው የከተማዪቱ ዕንብርት የሚገኘው ደብሩ ሁለት ዐበይት ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡
  • አንደኛው÷ የልማት ዕቅዶች ጅምር ቢኖሩትም ሊቀ ጳጳሱ በመስተንግዶና መጓጓዣ ስም የሚጠይቁት ያልተገባ ወጪ ፋይናንሳዊ አቅሙን እየተፈታተነው መኾኑ ነው፡፡ የኮፕት ቤተ ክርስቲያንና ካቶሊኮች ታላላቅ ገዳማትን በመመሥረት፣ ሆስፒታሎችንና ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማትን በማስፋፋት የሚያካሂዱት ልማት መንፈሳዊ ቅንዐት የማይፈጥርባቸው ሊቀ ጳጳሱ የቀደሙት ሊቃነ ጳጳሳት (ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ) የፈጸሟቸውን ሐዋርያዊ ክንውኖች እንኳ ለማስጠበቅ ተነሣሽነቱም ብቃቱም የላቸውም፡፡
  • ሁለተኛው÷ ሊቀ ጳጳሱ በርቱዐ ሃይማኖት እና በሞያ ብቃት ሳይኾን በጎጥና ጥቅመኝነት ላይ ተመሥርተው በሚያካሂዱት ቅጥር አንድ ቀሳጢ ‹መነኩሴ› በቀዳሽነት ለማስቀጠር ከደብሩ አስተዳደር ጋራ ውዝግብ መፍጠራቸው ነው፡፡ በውጭ ግንኙነት ጽ/ቤትና በፓትርያሪኩ ዕውቅና የተላኩት ካህን በግፍ ቦታውን ጥለው እንዲሰደዱ ካደረጉ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ በግል ውሳኔያቸው ሊያስቀጥሩት የነበረው ይህ የሃይማኖት ቀሳጢ ማንነቱ በማስረጃ ተጋልጦ ቅጥሩ ቢከሽፍም ሊቀ ጳጳሱን ተስፋ አድርጎ በዚያው የሚገኝ በመኾኑ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ስጋት ፈጥሯል፡፡ ውዝግቡ፣ በለቀቁት ባለሞያ ካህን ቦታ ተተኪ እንዳይቀጠርና ባሉት ጥቂት አገልጋዮች ላይ ጫና እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

*            *            *

  • መላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ያላቸውን የምክትል ፕሬዝዳንትነት ሓላፊነት በአግባቡ እየተወጡ አይደለም፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶሱን የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባዎች መንፈሴ አላዘዘኝም እያሉ በተለያዩ ሰበቦች እንደሚቀሩት ሁሉ፣ መሳተፍ የሚገባቸውን የምክር ቤቱን ስብሰባዎችም ኾነ ብለው በማስተጓጎላቸው በአህጉር ደረጃ የተወከሉበትን የቤተ ክርስቲያናችንን ሚና ከሌሎች አብያተ እምነት መሪዎች ሚና አሳንሰዋል፡፡
  • ‹‹ለመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ርዳታ መስጠት››፣ ‹‹በደቡብ አፍሪካና በኢትዮጵያ የማሳድጋቸው ሕፃናት አሉ›› በሚሉ ሰበቦች መጠኑ ያልታወቀ የበጎ አድራጊ ምእመናንን ገንዘብ ለግላቸው አካብተዋል፡፡ ለዚህ ዓላማ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ስታፎችንና ባዕለጸጋ ነጋድያንን በጥቅመኝነት በቀጠሯቸው አገልጋዮች ደላላነት ዒላማ አድርገዋቸዋል፡፡
  • ‹‹ኤርትራዊ ነኝ›› በሚል ከኤርትራውያን ምእመናን ገንዘብ ለግላቸው ይሰበስባሉ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ÷ ኤርትራዊ ተወላጅ ሲያገኙ ኤርትራዊ ነኝ፤ የኢሕአዴግ ደጋፊ ሲያገኙ ኢሕአዴግ ነኝ በሚል ጥቅም የሚያጋብሱበትን ኹኔታ በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በትኩረት እየተከታተለው መኾኑ ተጠቁሟል፡፡

*            *            *