በሊቀ ጳጳሱ ዳተኝነት፡ በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ከመንግሥት የተሰጣቸውን ዕውቅና የመነጠቅ ስጋት እንደተጋረጠባቸው ተጠቆመ
- ችግሩ የውጭ ግንኙነት መምሪያውን አፋጣኝ ትኩረት ይሻል
የመላው አፍሪቃ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኾኑት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ አስተዳደር ላይ በወጣው ዘገባ ዙርያ ከሚደርሱን አስተያየቶችና ትችቶች የሚበዙት ከደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ምእመናንና አገልጋዮች የሚላኩልን ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በኤጲስ ቆጶስነት ከተሾሙበት ፲፱፻፺፯ ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ለስምንት ዓመታት የቆዩበት ደቡብ አፍሪቃ መንበረ ሊቀ ጵጵስናው እና የአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት ከበርካታ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋራ የሚገኝበት ነው፡፡
‹‹ማንነቴን የተቸኋቸው ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ›› ያሉ አስተያየት ሰጭ፣ በደቡብ አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያን በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና እርሳቸው በግል ዕውቅና ብቻ በሚመድቧቸው አለቆችና ካህናት ይፈጸማል ያሏቸውን በደሎች በዝርዝር አስፍረዋል፡፡ ከያዙት ሓላፊነት አኳያ የተጣለባቸውን መንፈሳዊና አባታዊ አደራ ከመወጣት ይልቅ ‹‹እርሳቸው[ሊቀ ጳጳሱ] ናቸው እንጀራዬ›› የሚሉ የደብር አስተዳዳሪዎች ኹኔታ በምደባ ረገድ የተገለጸውን የጥቅመኝነት ግንኙነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
በዚህ መልኩ በተመደቡና በተቀጠሩ አለቆችና ካህናት ደግሞ ኑፋቄና ከፍተኛ የእምነት ማጉደል ወንጀልን የሚያቋቁሙ የምግባር ችግሮች ሲታዩ ደግሞ አስተያየት ሰጭው እንዳሉት ‹‹የዋህና አባቶቹን አክባሪ የኾነውን ክርስቲያን እምነትና አንድነት የሚፈታተን›› ነው፤ ከፋፋይና በታኝ ነው፡፡
የአስተያየት ሰጭው ትችት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ስለ ደቡብ አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያን የልማት እንቅስቃሴ ያቀረቧቸውንና በመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የተዘገበውን ሪፖርት የሚያስተባብል ነው፡፡ ከዚያ በላይ አስተያየት ሰጭው ስጋታቸውን እንደሚገልጹት፣ በአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዳተኝነት ምክንያት የአህጉረ ስብከቱ አሠራር የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ዕውቅና ከሰጠበት መንገድ አኳያ እንዲጣጣም ባለመደረጉ ‹‹የተሰጠን ዕውቅና እንደሚነጠቅና ሕዝበ ክርስቲያኑም እንደሚበተን አጠያያቂ አይደለም፡፡››
በአጠቃላይ በመላው አፍሪቃ አህጉረ ስብከት የብፁዕ አቡነ ያዕቆብ አስተዳደር ላይ በጥቅሉ የተጠቆሙት ችግሮች÷ ሐዋርያዊቷና ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት እጃቸውን ዘርግተው ለሚጠብቋት ጥቁር ሕዝቦችና ለመላው ዓለም ለመድረስ በዓለም አቀፋዊ ተልእኮዋ ረገድ ያሉባት በርካታ ውስንነቶች አነስተኛው መገለጫና ከዚህም አንጻር ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት የሚጠቁም ነው፡፡ ለማንኛውም ሐራዊው አስተያየት ሰጭ ‹‹ለሚመለከተው አካል በቀጥታ መድረስ ያለበትና አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ነው›› ያሉት መልእክታቸው ከሚያስፈልገው ልዩ ትኩረት አንጻር እንዳለ አቅርበነዋል፡፡
* * *
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ላይ በግለሰቦች እየተሠራ ያለው በደል በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ ከዚህ በታች የምተነትነው መልዕክት በቀጥታ ለቤተ ክርስቲያንዋ እውነተኛ ተቆርቋሪዎች ይደርስ እንደሆነ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ነው፡፡
የማይታየውንና ሰማያዊውን ነገር መንፈስ ቅዱስ ይመርምር!!! የሚታየውንና በግልጽ የማውቀውን ግን በድፍረት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ስል እመሰክራለሁ፡፡
በደሉም በሰፊው እየተፈጸመ ያለው በአቡነ ያዕቆብና በየአጥቢያው በየግል እውቅና ብቻ በመደቧቸው አስተዳዳሪዎች ነው፡፡ ይህን በደል እንዲያቆሙ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እውነተኛ ለቤተ ክርስቲያናችን የምንቀና ግለሰቦች ፊት ለፊት በግልጽ ልንመክራቸው ሞክረናል፡፡ እርሳቸው ግን በማን አለብኝነት የዋህና አባቶች አክባሪውን ሕዝበ ክርስቲያን በማታለልና በመከፋፈል የክርስትና አንድነታችንን በሚፈታተን መልኩ እየበተኑን ነው፡፡
ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመድበው ሲመጡ ለነበሩበት መንበር ሰበካ አባላት ዕንቆቅልሽ በሆነ መልኩ ስብከተ ወንጌል እንዳይስፋፋ የነበረውም አሠራር እንዲዳከም አደረጉ፡፡ በመቀጠልም የማይገባቸውን “የመላው አፍሪካ አህጉረ ስብከት” አስተዳዳሪነት ከፓትሪያርኩ ጽ/ቤት ተሰጥቶኛል የሚሉትን ደብዳቤ ይዘው መጥተው ለአገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በማሳወቅ የጥፋት ዘመቻቸውን ጀመሩ፡፡
በመጀመሪያ ለሌሎች አርኣያ የነበረውንና ለሌሎችም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መመሥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተውን የደርባንን ጉባኤ ከእናት ቤተ ክርስቲያን እንዲለይ አደረጉ ወይም እንደ አባት ያጠፋውን ክፍል ገሥጸው መመለስ ሲችሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እስከ አሁን መፍትሔ ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡
በመቀጠልም በጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለመግለጽ ለአእምሮ የሚከብድ ጥፋት ሲጠፋ እየሰሙ እንዳልሰሙና “በሐላፊነት ብዛት ልፈታው ጊዜ የለኝም በማለት” እያደባበሱ መንበረ ጵጵስናቸውንም ችላ በማለት በሌሎች “የአህጉረ ስብከቱ” አባል አገሮች በተለያየ ቦታዎች “ሥራ እየሠራኹ ነው” በማለት በጽ/ቤታቸው ላለመገኘት ምክንያት እየሰጡ ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተለያዩ ግንባታዎች እንዲካሄዱ አድርጌያለሁ ብለው የሰጡትን ሪፖርት በሚመለከት፡- አንድ እና አንድ ግልጽ ነው – የሚመለከተው የበላይ አካል መጥቶ ይመልከት!! የተደረጉትም ጥቂት ልማቶች በጠንካራ የቤተ ክርስቲያኑ ምእመን እንጂ በርሳቸው የአመራር ብቃት ወይም ፍላጎት አይደለም፡፡ እንዲያውም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለግንባታ መሰናክል ሲሆኑ ነው የሚታዩት፡፡
በመጨረሻም አሁን በፕሪቶርያ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት የተፈጠረው ችግር ያልተፈታው እርሳቸውን በመጠባበቅ ነው፡፡ ከላይ አንደተገለጸው በየአጥቢያው የሚመደቡትን አስተዳዳሪዎች የሚመድቡት እርሳቸው ናቸው፡፡ እኝህም የችግሩ መንሥኤ የኾኑት መነኩሴ የተመደቡት በርሳቸው ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ደብሩን ያስተዳደሩት መነኩሴ ሰበካው ያወጣውን የአስተዳደርና ሌሎችንም የቅጥር መስፈርቶች ያላሟሉና ተመድበው ከመጡበት ጌዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ የደብሩ ካህናትንና ዲያቆናትን ጨምሮ በተለያዩ ግለሰቦች በምንፍቅና፣ በገንዘብ ማታለልና እንዲሁም በወሲብ ክሶች ሲከሰሱ የቆዩ ነበሩ፡፡ ሰበካው በመደበው ንኡስ ኮሚቴ ጉዳዩ ለረጅም ጊዜ ተመርምሮ በምንፍቅና እና በገንዘብ ማታለል የተከሰሱበትን በግልጽ ተነግሯቸው እንዲታረሙ ተደርገው፣ በወሲብ ምክንያት የተከሰሱበትን ክስ ግን በቂ ማረጋገጫ ስላልተገኘ ውድቅ ኾኖ ነበር፡፡
መነኩሴው “እሳቸው ናቸው አንጀራዬ” ብለው በግልጽ እየተናገሩ ለአቡነ ያዕቆብ ወሬ አቀባይ ከመኾንና ሰበካውን ከምእመኑና ከካህናት ጋር ከማጋጨት በስተቀር ምንም ለቤተ ክርስቲያኑ ያበረከቱት ነገር የለም፡፡ በመጨረሻም ከደብሩ የተባረሩበት በግልጽ በተረጋገጠ የወሲብ ትንኮሳ ክስ ከሰበካው አባላት በተጨማሪ ዐሥር ያህል ገለልተኛ ምእመናን በተገኙበት በሙሉ ድምፅ የተወሰነ ውሳኔ እርሳቸውም በወቅቱ አምነው የፈረሙበት ነው፡፡
ይህ ከላይ የተገለጸው ታሪክ ምናልባት እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አሠራር ይቅር በመባባል እንዲሁም እንደተለመደው አንድ ደብር ያጠፋውን አስተዳዳሪ ወደ ሌላ ደብር መመደብ ቀላል ሊኾን ይችላል፡፡ ነገሩ ግን ከዚህም በጣም የከፋ ገጽታ አለው፡፡
ይኸውም አሁን ጠቅላላ መስተዳደሩ ላይ ያለው አካል ላለንበት አገር (ደቡብ አፍሪካ) መንግሥት ቤተ ክርስቲያንዋ የተሰጣትን ዕውቅና ላለማጣት ዓመታዊ የሒሳብና የተለያዩ ሪፖርቶችን ለሁለት የመንግሥት አካላት (Social Development እና South African Revenue Service) ማቅረብ ግዴታ አለባት፡፡ ይህም ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ጽ/ቤታችን “የመላው አፍሪካ አህጉረ ስብከት” ጽ/ቤት ተብሎ እስከተሰየመ ድረስ ጽ/ቤቱ ላለበት አገር ጠቅላላ የውስጡንም ኾነ የውጪውን በሥሩ ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ገንዘብ ነክ የሆኑና ያልሆኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች ሪፖርት ማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን እንኳን የውጪውን አገሮች የውስጡንና የመንበረ ጵጵስና ደብራቸውን የተሟላ ተቀባይነት የለው የሒሳብ አሠራር እንዲዘረጋ ጳጳሱ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ለSocial Development እንዲሁም ለአራት ዓመታት ለSouth African Revenue Service ሪፖርቶች ያልቀረቡ ሲኾን በቅርቡ የሚያስፈልገው ወሳኝ ሥራ ካልተሠራ የተሰጠን ዕውቅና እንደሚነጠቅና ሕዝበ ክርስቲያኑም እንደሚበተን አጠያያቂ አይደለም፡፡
እንግዲህ ይህን የሚያህል ሐላፊነት አደጋ ላይ ጥለው ነው አቡነ ያዕቆብ ለግል ጥቅማቸው/ስማቸው ብቻ ላይ ታች የሚሉት፡፡ የሚገርመው መንግሥት ለኦዲት ቢመጣ ሌላው ይቅርና ላለፉት አምስት ዓመታት ከ50,000 ራንድ በላይ በግል የታክስ ዕዳ የመጀመሪያ ተጠያቂ የሚሆኑት አቡነ ያዕቆብ እና እንደማንኛውም ግለሰብ በሥራ የመንግሥት ፈቃድ እየታደሰላቸው የተመደቡት መሰሎቻቸው የየደብሩ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡
ይህ ነገር በግልጽ ቢነገራቸውም አቡነ ያዕቆብ አሻፈረኝ ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስትበደል አይቶ ዝም ማለት ባለብን ጉድፍ ላይ ተጨማሪ ጉድፍ የመበተን ያህል ነው!
እግዚአብሔር ተሰባስቦ ከመበተን ይጠብቀን!!!